Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመቶ ያላነሱ የአውሮፓና የቻይና ኩባንያዎችን በአንድ ቦታ ያገናኙ ሁለት የንግድ ዓውደ ርዕዮች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ሁለት የንግድ ዓውደ ርዕዮች በተመሳሳይ ቀናት ተካሂደዋል፡፡ ከመቶ ያላነሱ የውጭ ኩባንያዎችም ተሳትፈዋል፡፡

ከሐሙስ ሚያዝያ 25 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄዱት ሁለቱ የንግድ ዓውደ ርዕዮች የየራሳቸው ይዘትና ኩነቶችን የያዙ ቢሆኑም፣ በአንድ ቦታና ተመሳሳይ ቀናት ውስጥ እንዲካሄዱ ተደርገዋል፡፡

አንደኛው የንግድ ዓውደ ርዕይ ከ60 በላይ የአውሮፓ፣ የእስያ፣ የአፍሪካ፣ እንዲሁም የአሜሪካ ኩባንያዎችን ያገናኘውና ‹‹ኢትዮጵያ አግሮፉድ››፣ ‹‹ኢትዮጵያ ፕላስት-ፕሪንት-ፓክ›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ ነው፡፡ ፌርትሬድ የተሰኘው የጀርመኑ ኩባንያ ከአገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ዓውደ ርዕይ የፕላስቲክ ምርቶች፣ የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎችና ሌሎችም አውሮፓ ሠራሽ ምርቶች የቀረቡበት ነበር፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃ ለማምረት የሚያስችላት ኢንዱስትሪ ባይኖራትም፣ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃዎችና የፕላስቲክ ውጤቶችን ከውጭ እያስገባች ትገኛለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ እየተስፋፋ በመጣው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ዘርፍ ሳቢያ ብዛት ያላቸው የማቀነባበሪያ ማሽነሪዎች ወደ አገር ውስጥ በመግባት ላይ እንደሚገኙ የጀርመን አምራቾች ፌዴሬሽን ጥናት በዓውደ ርዕዩ መክፈቻ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

ማርቲና ክላውስ በጀርመን የኢንጂነሪንግ ኩባንያዎች ፌዴሬሽን የአፍሪካ ገበያ ልማት ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ማርቲና ከሆነ፣ በኢትዮጵያ የምግብ ማሸጊያና የመጠጥ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ታይቷል፡፡ ይህ ዘርፍ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአሥር እጥፍ አድጓል፡፡ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የምግብና የመጠጥ ምርቶች በአሥር እጅ ጨምሮ እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 2.4 ቢሊዮን ዩሮ አድጓል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የ128 ሚሊዮን ዩሮ የምግብ ማነቀባበሪያና የማሸጊያ ማሽነሪዎች ግዥ ፈጽማለች፡፡ የ31 ሚሊዮን ዩሮ የግብርና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ግዥም መፈጸሟን የፌዴሬሽኑ ጥናት ጠቁሞ፣ አገሪቱ ያካሄደቻቸው ግዥዎች ከምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች ይልቅ ከፍተኛውን ግዥ ያከናወነች አገር ለመሆን እንዳበቃት ይጠቅሳል፡፡ከመቶ ያላነሱ የአውሮፓና የቻይና ኩባንያዎችን በአንድ ቦታ ያገናኙ ሁለት የንግድ ዓውደ ርዕዮች

 

ከ60 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው በዚህ የንግድ ዓውደ ርዕይ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ የፕላስቲክ ውጤቶች፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያዎችና ልዩ ልዩ ማምረቻዎች ይተዋወቃሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከ14 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን የገለጹት፣ የፌርትሬድ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፖል ማርዝ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶች ፍጆታ በከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ በመጣበት ወቅት የሚካሄደው ይህ ዓውደ ርዕይ ላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ይሳተፉበታል፡፡ በኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት የነፍስ ወከፍ የፕላስቲክ ፍጆታ እያደገ መጥቷል፡፡ ከውጭ የሚገቡ የምግብ ውጤቶች በ21 በመቶ መጨመራቸውንና ከእነዚህም ውስጥ የወተት ምርቶችና የጣፋጭ ምግቦች የገቢ ንግድ ከፍተኛውን ደረጃ እንደያዘም ማርዝ ይጠቅሳሉ፡፡ በምግብ ሸቀጦች ረገድ፣ እ.ኤ.አ. በ2009 የኢትዮጵያ የምግብ ምርቶች የገቢ ንግድ መጠን 866 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ሲጠቀስ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በነበረው መረጃ መሠረት የገቢ ንግድ መጠኑ ወደ 2.74 ቢሊዮን ዶላር ማደጉ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአማካይ የ21 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደመጣም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት በቀረበው ዘገባ እንደተጠቀሰውም፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚታየው የፕላስቲክ ምርቶች ፍጆታ አማካይ በ15 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ባለፈው ዓመት የነበረው ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታም 2.4 ኪሎ ግራም እንደነበር ተወስቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020ም የነፍስ ወከፍ ፍጆታው ወደ 3.2 ኪሎ ግራም እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ በአገር ደረጃም የፍጆታው መጠን ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረበት የ44 ኪሎ ቶን ወይም የ44 ሺሕ ቶን የፕላስቲክ ፍጆታ ወደ 220 ኪሎ ቶን ወይም ወደ 220 ሺሕ ቶን አሻቅቧል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ወደ 308 ኪሎ ቶን ወይም ወደ 308 ሺሕ ቶን እንደሚያድግ ትንበያዎች ይጠቁማሉ በማለት ማርዝ አብራርተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ፕላስቲክ ባታመርትም፣ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማቀነባበርና ከውጭ በማስገባት ግን በትልቁ ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ ተጠቃሽ ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርት ለማምረት የሚያስችላት ደረጃ ላይ ባትገኝም፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዬሳ ለታ እንደሚያምኑት፣ በቅርቡ ዕውን እንደሚሆን የሚጠበቀው የፔትሮኬሚካል ኢንዱስትሪ ግን ይህንን ችግር እንደሚቀርፈው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በሌላ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ በተሰናዳው የቻይና የንግድ ሳምንት ‹‹ቻይና ትሬድ ዊክ›› ዓውደ ርዕይ ላይ እንደሚሳተፉ ከሚጠበቁት 50 የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ 37ቱ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ዝግጅት ተሳትፈዋል፡፡ የዓምናው ዓውደ ርዕይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል መሰናዳቱ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያና በቻይና መካከል የሚካሄደውን የንግድ ልውውጥ ከ5.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ባመስመዘገው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ውስጥ ኩባንያዎች በተለይም የቻይና ኩባንያዎች ድርሻ ጎልቶ ይታያል፡፡ በአዲስ አበባ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የኮሜርስ ጉዳዮች ቆንስላዋ ሊዩ ዩ እንደጠቀሱትም፣ የቻይና መንግሥት በዲፕሎማሲ ግንኙነቱ ውስጥ ትኩረት ከሚያደርግባቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ ሁለቱ አገሮች የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ካደሱ ወዲህ በነበሩት 48 ዓመታት ውስጥ የቻይና መንግሥት በርካታ ገንዘብ በማበደር በኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ አግዟል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እንደ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና ሌሎችም ላይ ትልቅ ተሳትፎ ማድረጉን የጠቀሱት ቆንስላ ዩ፣ የቻይና መንግሥት እየሰጠ በሚገኘው የትምህርት ዕድልም እስካሁን 5,500 ኢትዮጵያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው በተለያዩ የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

አቶ ተስፋ ኪሮስ ኃይሉ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደእሳቸው ማብራሪያ ከሆነም በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል 60 የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡ ከተደራራቢ ታክስ ማስቀረት ጀምሮ፣ ዲፕሎማቶች ነፃ ቪዛ የሚያገኙበት፣ የአየር ትራንስፖርትና የመሳሰሉት በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ከተፈረሙት ስምምነቶች ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሰባት ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የቻይና ኩባንያዎች የሚገነቧቸው ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ እየተካሄዱ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ተስፋኪሮስ፣ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ ከ940 በላይ የቻይና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ሲተገበሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችም ከ30 ሺሕ በላይ ቋሚና ከ40 ሺሕ በላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን እንደፈጠሩም ዲፕሎማቱ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና የቻይና ኩባንያዎች የሠራተኞችን የመደራጀት መብት በመጣስ፣ የክፍያና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን ባለማክበር ከሚጠቀሱ የውጭ ኩባንያዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በየጊዜው ከሚያሰማው አቤቱታ መረዳት ይቻላል፡፡

በጠቅላላው ሁለቱ ዓውደ ርዕዮች በቋሚነት መካሄዳቸው እንደሚቀጥል የሁለቱም ዓውደ ርዕዮች የአገር ውስጥ አዘጋጅ የሆነው ፕራና ኩነቶች አዘጋጅ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች