Thursday, June 1, 2023

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያዎቹ የውጭ አገር ጉዞዎችና ውጤታቸው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ ረቡዕ ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አንድ ወር አስቆጥረዋል፡፡ በዚህ አንድ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ካሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ከመወያየት ባለፈ፣ ሥልጣን ከያዙ በጂቡቲ የመጀመርያቸውን፣ በሱዳን ደግሞ ሁለተኛቸው የሆነውን የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ከመጀመርያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግራቸው ጀምሮ በአካባቢያዊ አንድነት፣ ሰላም፣ ደኅንነትና የንግድ ትስስር ላይ ትኩረት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በሁለቱ አገሮች ያደረጉት ጉዞ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያው የውጭ አገር መዳረሻ የነበረችው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድን 90 በመቶ የምታስተናግደው ጂቡቲ ስትሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ በተለይ ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ ልማት ላይ ድርሻ እንዲኖራት መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ የጂቡቲን ወደብ በጋራ ለማልማት ወደፊት የሚደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ ካሏት ትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ጂቡቲ ድርሻ እንዲኖራት በማድረግ፣ የድርሻ ልውውጥ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

ከጂቡቲ መንግሥት ጋር የድርሻ ልውውጥ እንደሚካሄድባቸው የተገለጹት መንግሥታዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆኑ፣ እነዚህ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገቡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015-16 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስድስት ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ አየር መንገዱ በአጠቃላይ 55 ቢሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል፡፡ አየር መንገዱ ያስመዘገበው ትርፍ ከቀዳሚው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ70 በመቶ ዕድገት ሲኖረው፣ ገቢው ደግሞ የ10.3 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የወጪ ንግዷን በጂቡቲ ወደቦች በኩል የምታስተናግደው ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 ለጂቡቲ መንግሥት በቀን እስከ ሁለት ሺሕ ዶላር ትከፍል እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያው የውጭ ጉዟቸው መዳረሻ ያደረጓት ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እንድትተሳሰር፣ በሁለቱም መንግሥታት ጥረቶች ሲደረጉ ነበር፡፡

ጂቡቲ ኢትዮጵያን ትኩረት በማድረግ በዋናነት ለገቢና ለወጪ ንግዶቿ አገልግሎት ለመስጠት ያለመውን የዶራሌህ ወደብን በ660 ሚሊዮን ዶላር ገንብታ ለአገልግሎት አብቅታለች፡፡ በዚህ ወደብ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የ45 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኘው በኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የሚሠራው የሰውና የዕቃ ማጓጓዣ ባቡር ለሁለቱ ጎረቤት አገሮች ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት፣ የባቡር መስመሩ በተመረቀበት ወቅት በስፋት ተገልጿል፡፡

አሁን በኢትዮጵያና በጂቡቲ መንግሥት መካከል ይሁንታ የተሰጠው፣ የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ድጋፍ አንዱ አካል እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በዚህም ስምምነት ውስጥ በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎቶች ሰጪ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምም ሊካተት እንደሚችል፣ የጂቡቲ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ደዋሌህ ለብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡

ልክ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም ከፍተኛ ገቢ ለአገሪቱ የሚያስገባ መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡ ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ2014-15 ኢትዮ ቴሌኮም 21.5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም እ.ኤ.አ. በ2017 ግማሽ ዓመት 18 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ አስመዝግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጂቡቲ በነበራቸው ጉብኝት ለጂቡቲ ፓርላማ አባላት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ተወካዮች አቅም መጠናከር ያለውን ጥቅም አጉልተው ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ባለፈም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ምን ያክል ጠንካራና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ ለመሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁላችሁም እንደምታውቁት ታሪካዊ ግንኙነታችን ተምሳሌትነቱ ለኢጋድ አባል አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አገሮችም ጭምር ነው፡፡ ግንኙነታችን የተለየ ነው፡፡ አንድ ዓይነት ሕዝብ ግን በሁለት ሉዓላዊ አገርነት የምንኖር ነን፡፡ የኢኮኖሚ ውህደቱን ይበልጥ ለማሳደግና ለማጠናከር እንሠራለን፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጂቡቲ ፓርላማ አባላት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሁለቱ አገሮች የእርስ በርስ በመረዳዳት፣ አገራዊና ቀጣናዊ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት እንደሚተባበሩም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጂቡቲ በነበራቸው የሁለት ቀናት ጉብኝት በዋናነት ለኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባውን የዶራሌህ ወደብን ጎብኝተዋል፡፡

የጂቡቲ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ደዋሌህ ካሁን ቀደም ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ ኢንቨስትመንት ለማድረግ ብትፈልግ ዕድሉ ይኖራታል ወይ ተብለው በሪፖርተር ለተጠየቁት ጥያቄ፤ ‹‹እኛ ቢሊዮን ዶላሮችን አውጥተን ወደቦችን በገነባንበት ወቅት ኢትዮጵያ አዲስ ወደብ ለመገንባት ኢንቨስት ማድረጓ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው? ያካሄድነው ኢንቨስትመንት እኮ ለጂቡቲ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለቀጣናው አገልግሎት ለመስጠት ነው፤›› ሲሉ መልስ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጂቡቲ ጉብኝታቸውን አጠናቀው በሁለተኛው የውጭ አገር ጉዟቸው ያመሩት ወደ ሱዳን ሲሆን፣ የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ሲደርሱ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የሁለት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ሐሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሱዳን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በጂቡቲ ካደረጉት ጋር የሚመሳሰል ከሱዳን መንግሥት ጋር የሱዳን ወደብን አብሮ ለማልማት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችውና በሱዳን ወደብ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችላት ፍላጎት፣ በወደብ አገልግሎቶች ላይ የሚከፈለው ዋጋ ተመን ላይ የውሳኔ ድምፅ እንዲኖራት ያስችላልም ተብሏል፡፡

ይህ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችው ስምምነት ቱርክና ኳታር በሱዳን ወደቦችን ለማልማት ከሱዳን መንግሥት ጋር ስምምነት በፈጸሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ቱርክ የፈራረሰችውን ሱዳን የምትገኘውን የኦቶማን ቱርክ ወደብ ሱዋኪንን ለመገንባት የተስማማች ሲሆን፣ ኳታር ደግሞ የሱዳንን ወደብ በአራት ቢሊዮን ዶላር ለማልማት ስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡

ከጂቡቲ ጋር የሚደረገው ስምምነት ሁለቱ አገሮች በድርጅቶች ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በመቀያየር እንሆነ የተገለጸ ቢሆንም፣ ከሱዳን ጋር የሚኖረው ስምምነት ግን በምን ሁኔታ ሊፈጸም እንደሚችል የተሰማ ነገር የለም፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካሁን ቀደም ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጋራ ያለሙት የኢትዮ – ጂቡቲ የባቡር መስመር ሁለቱ አገሮች መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለማልማት ያላቸውን ልምድና አቅም ማሳያ ነው፡፡

‹‹ይህ አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ስለሆነ መቼ ሊሆን እንደሚችልና በምን ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል የተገለጸ ስላልሆነ፣ በአፈጻጸሙ ላይ ብዙም መናገር አይቻልም፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ ተናግረዋል፡፡

የጋራ ድርሻ ያላቸውን ድርጅቶችና መሠረተ ልማቶች የሚያስተዳድር ልክ እንደ ኢትዮ – ጂቡቲ የባቡር መስመር አስተዳደር ያለ ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ አካል እንደ አማራጭ ሊሰየም እንደሚችል አቶ ወንዳፍራሽ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዛት በጂቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ የሆነ የወደብ ተጠቃሚነት  ሲኖራት፣ ይኼንን ከፍተኛ የሆነ የጂቡቲ ወደብ ጥገኝነት ለማቃለል የሱዳን ወደብ እንደ አማራጭ መቅረቡ ጠቃሚ እንደሚሆን በርካቶች ይገልጻሉ፡፡ የጂቡቲ መንግሥትም ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ ተቃውሞ እንደሌለው፣ የጂቡቲ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትሩ የዶራሌህ ወደብ በተመረቀበት ወቅት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ተጨማሪ አማራጭ ወደብ ለማልማት መፈለግ ምክንያታዊ ነው፡፡ እኔ የኢትዮጵያ መሪ ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን ብሆን ኖሮ እነሱ አሁን እያደረጉት እንዳለው ሁሉ፣ እኔም አማራጭ ወደብ ፍለጋ ውስጥ መግባቴ አይቀርም ነበር፡፡ ይህ በመደረጉ ግን አንዳችን ሌላችንን አንፈልግም ወይም አንዳችን ሌላችንን በክፉ እናያለን ማለት አይደለም፡፡ አንድ መሪ ለአገሩ የሚጠቅሙ አማራጮችን ማፈላለጉ የተለመደ ነገር ነው፡፡ በዚሁ አግባብ እኔም ወደቦቼን ያለማሁት መቶ በመቶ የኢትዮጵያ የገቢና የወጪ ዕቃዎች ፍሰትን ብቻ ለማስተናገድ አይደለም፡፡ ሌሎች አማራጮቼን ማየት ያስፈልገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ንፅፅራዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያስገኝልኝ ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህን ከመገንባት አላቅማማም ነበር፡፡ በአንዱ አገር ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ስለማይታወቅ አማራጭ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ‹ሁሉንም እንቁላሎችህን በአንድ ቅርጫት አታስቀምጥ› እንደሚባለው ሁሉ፣ እኛም ስለአማራጭ ወደብ አስፈላጊነት የጠራ ግንዛቤ አለን፡፡ ይኼም ቢባል ግን ኢትዮጵያን ቢያንስ ለመጪዎቹ 20 ዓመታት ለማገለገል የሚያስችል የአንበሳው ድርሻ እንደሚኖረን ግንዛቤው አለን፤›› ሲሉ ነበር የፋይናንስ ሚኒስትሩ ኢሊያስ ሙሳ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ያስረዱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ውይይቶቹ የታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ስለሚካሄዱ የንግድ እንቅስቃሴዎችና በጋራ የወደብ ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በምታደርገው የሁለትዮሽ ውይይት ማንም ሳይጎዳ የጋራ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ላይ እንደምታተኩር ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በእርግጥም ዕጣ ፈንታችን በዓባይ ወንዝ ለዘለዓለሙ የተገመደ ነው፤›› በማለት፣ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በሦስትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የናይልን ውኃ እንዴት በፍትሐዊነትና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚቻል እየተነጋገሩ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም ማድነቅ እወዳለሁ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተናግረዋል፡፡

የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር በበኩላቸው፣ ሁለቱ አገሮች ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት የምንሠራውን ይበልጥ ማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ በተለይ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በኢጋድና በሁለትዮሽ መንገዶች እየሠራን ነው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተስማማንባቸውና የሱዳን አቋም የሆኑ ጉዳዮች አሁንም እንዲጠበቁ፣ ሱዳን ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤›› ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች መዘርጋታቸው ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛው 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና ሁለቱን አገሮች የሚያገናኘው የአውቶቡስ ትራንስፖርት ከዓመት በፈት መጀመሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በድንበር ላይ ያለውን ንግድ በተመለከተ፣ በተለይ በአሶሳ በኩል ያለውን ንግድ ፈር ለማስያዝ ብዙ ጊዜ ተሞክሮ ያልተሳካና አሁን ግን ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን፣ ከውይይቱና ከስምምነቱ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለመንግሥታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሱዳን በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር እስረኞቹ የሚፈቱበትን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -