Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ኩባንያዎች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን አስታወቁ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የጂቡቲ የነዳጅ ተርሚናል አቅም ማነስና ነዳጅ በባቡር ማመላለስ አለመጀመሩ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሯል

በነዳጅ ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለሚሰጡት አገልግሎት የሚከፈላቸው የትርፍ ህዳግ በጣም አነስተኛ መሆን፣ ለዘርፉ መቀጨጭ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታወቁ፡፡

ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢሊሊ ሆቴል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመገምገም ባሰናዳው የምክክር መድረክ ላይ፣ የነዳጅ ኩባንያዎች ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት ለነዳጅ ኩባንያዎች የፈቀደው የትርፍ ህዳግ በጣም አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ ኩባንያቸው ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በነዳጅ ማደያዎችና በነዳጅ ዲፖዎች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ ቢሆንም፣ አሁን ያለው አነስተኛ የትርፍ ህዳግ የእሳቸውንም ኩባንያ ሆነ ሌሎች ኩባንያዎች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ጎረቤት ኬንያ 2,000 ያህል የነዳጅ ማደያዎች ሲኖሩዋት 100 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ 800 ያህል ማደያዎች ብቻ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ የትርፍ ህዳጉ አነስተኛ መሆን ለዘርፉ መዳከም ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የቶታል ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ላሲና ቱሬ በኢትዮጵያ ለነዳጅ ኩባንያዎች የሚከፈለው የትርፍ ህዳግ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሲነፃፀር እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ኢንቨስት እንዳያደርጉ ማነቆ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡ አዳዲስ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ እንደማያበረታታ የገለጹት ሚስተር ላሲና ቱሬ፣ ያሉትም ኩባንያዎች ተስፋ እያስቆረጠ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የነዳጅ ኩባንያዎቹ የትርፍ ህዳጉ አነስተኛ መሆን በነዳጅ ማከፋፈል ሥራ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በማስረዳት፣ መንግሥት ችግሩን ተመልክቶ እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም የማሻሻያ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሥት ለጥያቄያቸው በጎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አንድ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያ በሊትር ስምንት ሳንቲም፣ የነዳጅ ማደያ ባለቤት ደግሞ በሊትር ሰባት ሳንቲም የትርፍ ህዳግ እንደሚከፍላቸው ታውቋል፡፡ የነዳጅ ኩባንያዎችና የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ከሚያወጡት ኢንቨስትመንት አንፃር የሚያገኙት የአገልግሎት ክፍያ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ፣ የኩባንያ ተወካዮች በምሬት ገልጸዋል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ ኮኦንግ ቱትላም (ዶ/ር) የነዳጅ ኩባንያዎች ያቀረቡትን አቤቱታ መንግሥት እንደሚያውቀው ገልጸው የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርና ንግድ ሚኒስቴር በጋራ ለኩባንያዎች በሚከፈለው የትርፍ ህዳግ ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡ የትርፍ ህዳግ ጉዳይ ጊዜ እንደሚፈልግ፣ መንግሥት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ በነዳጅ ግዥና አቅርቦት በኩል የተሳካ ሥራ መከናወኑን አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ተገዝቶ ያለምንም ችግር ወደ አገር ውስጥ መግባቱን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የስምንት በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በዘጠኝ ወራት ጊዜ የቀረበው ነዳጅ በገንዘብ ሲሰላ 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ግልጽ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጨረታዎችን በማውጣት፣ በወቅቱ የነዳጅ ውጤቶች ለአከፋፋይ ኩባንያዎች እንዲቀርቡ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡ የጂቡቲ ወደብ ሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናል አቅም እያደገ ከመጣው ከኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት ጋር አለመስፋቱ፣ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ትልቅ ፈተና እንደሆነበት ገልጸዋል፡፡ የሆራይዘን ተርሚናል ከመርከቦች የሚራገፈውን ነዳጅ መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ ነዳጅ የማራገፍ ሥራውን ፈታኝ እንዳደረገው አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ድርጅታቸው ከነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ የተቀላጠፈ አሠራር በመዘርጋትና በሦስት ፈረቃ በመሥራት፣ የነዳጅ ሥርጭቱ ላይ የጎላ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ነዳጅ በባቡር ማመላለስ አለመጀመሩ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ እንዳሳደረ በስብሰባው ወቅት ተነግሯል፡፡ የጂቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል አቅም ማነስ ችግር ነዳጁን በባቡር ማመላለስ ቢቻል በተሰወነ መጠን ሊቀርፈው እንደሚቻል ተነግሯል፡፡

የሆራይዘን ተርሚናል አቅም ውስን በመሆኑ በነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ብቻ ችግሩን ማቃለል የማይቻል በመሆኑ፣ ነዳጁን በብዛት ማንሳት የሚቻለው በባቡር በማመላለስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የተዘረጋውን አዲሱ የባቡር መስመር በመጠቀም ነዳጅ ማመላለስ የሚጀመረው መቼ እንደሆነ አልተገለጸም፡፡

በስብሰባው ላይ የተካፈሉ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተወካይ ነዳጅ የማመላለስ አገልግሎት ያልተጀመረው፣ የባቡር ሐዲዱ ከጂቡቲ ሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናልና አዋሽ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ዲፖ ጋር ባለመገናኘቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባቡር ሐዲዱን ከአዋሽ ዲፖና ከጂቡቲ የነዳጅ ተርሚናል ጋር ለማገናኘት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዲዛይን ሥራው እንደተጠናቀቀ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሆራይዘን ተርሚናል አቅም ውስንነት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ በጂቡቲ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት መነሳቱ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በነዳጅ ተርሚናሉ ላይ ድርሻ ኖሯት በጋር በሚሠራበት ሁኔታ ላይ ጥናት እንደሚደረግ ተነግሯል፡፡

ሌላው በስብሰባው ላይ የተነሳው ዋና ችግር በጂቡቲ ክልል ውስጥ ያለው መንገድ ክፉኛ በመጎዳቱ ምክንያት፣ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ነው፡፡ በመንገዱ ብልሽት ምክንያት በሁለት ሰዓት የሚሸፈን ጉዞ ግማሽ ቀን እየፈጀባቸው እንደሆነና ተሽከርካሪዎች ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሆነ ነዳጅ አመላላሽ ኩባንያዎችና ባለንብረቶች ተናግረዋል፡፡ በስብሰባው ላይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች ባለመገኘታቸው ለጥያቄው ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች