Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአዲስ አበባ ግዙፍ የመዋቅር ለውጥ ለማካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንታ ይጠበቃል

በአዲስ አበባ ግዙፍ የመዋቅር ለውጥ ለማካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንታ ይጠበቃል

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በፖለቲከኞችና በባለሙያዎች የሚሠራውን ሥራ ለመለየት፣ ካቢኔውንም በአንድ ከንቲባና በአምስት ምክትል ከንቲባዎች ብቻ ለማዋቀር የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑ ታወቀ፡፡

በ1995 ዓ.ም. በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ አሥር ክፍላተ ከተሞችን የፈጠረ ግዙፍ የመዋቅር ለውጥ ከተካሄደ ከ15 ዓመታት በኋላ፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በሚሰናበቱበት ዓመት አዲስ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ዕቅድ ይዘዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓመት ይካሄድ የነበረው ማሟያ ምርጫ ወደሚቀጥለው ዓመት በመሸጋገሩ የከተማው አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ቀጥሏል፡፡

በእርግጥ በከንቲባ ድሪባ በሚመራው ካቢኔ ይህን ግዙፍ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው በ2009 በጀት ዓመት ቢሆንም፣ በአገሪቱ በተነሳው መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ አመቺ ጊዜ እንዳልሆነ በመታመኑ በይደር መቆየቱን ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ካቢኔው በተያዘው በጀት ዓመት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ቢያቅድም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዕቅዱ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንፃራዊነት የአገሪቱ ሰላም ወደ ቀድሞው በመመለሱና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሰየሙ የመዋቅር ለውጥ ዕቅዱ በድጋሚ አዲስ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው እየተባባሰ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና እያደገ የመጣውን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ፣ ግዙፍ መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረትት ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመዋቅር ለውጥ ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት›› የሚሰኝ ተቋም አቋቁሞ ጥናት የተካሄደ ሲሆን፣ በጥናቱ ላይ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው የከተማው ፖለቲከኞች ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ ሥራዎቹም ክትትልና ግምገማ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በአንፃሩ ባለሙያዎች ደግሞ ማዘጋጃ ቤታዊ ሥራዎች ላይ ያተኩራሉ ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት ከተማው አንድ ከንቲባና አምስት ምክትል ከንቲባዎች እንደሚኖሩት፣ ምክትል ከንቲባዎቹ የኢኮኖሚ፣ የመሬት፣ የቤቶችና የኮንስትራክሽን፣ የትራንስፖርትና አካባቢ ጥበቃ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና ደኅንነት ዘርፎችን ይመራሉ ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማው አስተዳደር ሥር የሚገኙ ቢሮዎች የካቢኔ አባላት ሲሆኑ፣ በቅርቡ ወደ አስተዳደሩ ለተመለሰው ገቢዎች ባለሥልጣን አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመሾማቸው የካቢኔ አባል ሆነዋል፡፡

ይህ አሠራር በአዲሱ መዋቅር ቦታ የሌለው ሲሆን፣ ከንቲባውና አምስቱ ምክትል ከንቲባዎች ብቻ የካቢኔ አባላት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ ይህንን ግዙፍ ዕቅድ የከተማው አስተዳደር ተግባራዊ ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ይሁንታ ማግኘት የሚፈልግ በመሆኑ፣ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በከተማው አስተዳደር መካከል ውይይት እንደሚደረግ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...