የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የሚመለከቱ ጥናቶች እንዴት እንደሚቀጥሉ በአዲስ አበባ ተገናኝተው ተወያዩ፡፡
በአዲስ አበባ በተካሄደው ስብሰባ የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረጉት ሁለት ጥናቶች በሚቀጥሉበትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ አመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሱዳን ወገን በኩል በቀረበ ሐሳብ መሠረት የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች ስብሰባ በቀጣይ ከመካሄዱ በፊት የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴው የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት ስብሰባ ይደረጋል፡፡ በስብሰባው ጥናቶቹን ለሚያከናውነው አማካሪ ድርጅት ረቂቅ የጥናት ማስጀመርያ ሪፖርቱን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት፣ ማብራሪያና ጥያቄዎች በማቀናጀት ለማቅረብ እንደመከሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት በሦስቱ አገሮች መካከል በተደረጉ የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች በተደረሰው መግባባት መሠረት፣ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መክሮ ውጤቱን በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ለታቀደው ሁለተኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች ለሚያካሂዱት የሦስትዮሽ ስብሰባ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለግብፅ አህራም ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የአዲስ አበባው የሦስትዮሽ ስብሰባ እንዳይሳካ አድርገዋል በማለት ወቅሰዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በግብፅ በጉብኝት ላይ ከሚገኙት ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኩቴሳ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡
ምንም እንኳ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሦስትዮሽ ስብሰባው እንዳይሳካ አድርገዋል ቢሉም፣ የጋራ ኮሚቴው ግን ቀጣይ ስብሰባውን ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ግብፅ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጹ ተቃውሞ እያሰማች የምትገኝ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ድርድሩን ለማስቀጠል በትኩረት እየሠራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል፡፡