Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥትን የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት የሚመራ ስትራቴጂ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የልማት አጋሮች ለግልጽነትና ለሁሉ አቀፍ የበጀት አስተዳደር ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቁ
  • የግዥ ሥርዓቱ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ይመራል ተብሏል

መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲተገብራቸው የቆዩትን የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስ አስተዳደር ዘዴዎችን በአዲስ በማቀናጀት የሚመራ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ፡፡ ስትራቴጂው ከትልልቅ ፕሮጀክቶች እስከ አነስተኞቹ ድረስ ያለውን የመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት የሚያስተዳደር እንደሆነም፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በየመንፈቀ ዓመቱ የሚካሄደው የመንግሥትና የልማት አጋሮች ቡድን በጋራ በመሠረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ሒደት ላይ የሚያካሂዱት የግምገማና የትግበራ ድጋፍን የተመለከተ ውይይት፣ ከማክሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት መካሄድ ጀምሯል፡፡ በዚህ ስብሰባም የመንግሥትን ወቅታዊ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ከአዳዲስ አሠራሮችና ማሻሻያዎች አኳያ እየተቃኘ፣ የመንግሥት ወጪ፣ ገቢ፣ ግዥና ንብረት አስተዳደርና ሌሎችም መሠረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ መስኮች በውጭ አካላትና በመንግሥት ኃላፊዎች ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ይፋ እንዳደረጉት፣ መንግሥት የአምስት ዓመት የፋይናንስ አስተዳደር ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅቶ ለልማት ዕርዳታና ድጋፍ ከሚሰጡት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር ተነጋግሯል፡፡ መንግሥት የነደፈው አዲሱ ስትራቴጂ በከፍተኛ ደረጃ ወጪ የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ የሚደረጉበትንና ተግባራዊ የሚደረጉበትን ሒደት ጭምር ይቃኛል፡፡ ይህ ስትራቴጂ ማሻሻዎችን አካቶ በቅርቡ ዕውን እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሌላዓለም ዮሐንስ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ መንግሥት የሚተገብረው የፋይናንስ ስትራቴጂ ከዚህ ቀደም የተጀማመሩትንና እንደ የተቀናጀ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደርና የኢንፎርሜሽን ሲስተም፣ የተቀናጀ የበጀትና የወጪ ሥርዓት (ኢንተግሬትድ በጀት ኤንድ ኤክስፔንዲቸር ሲስተም አይቤክስ)፣ የግዥ ሥርዓትና ሌሎችም አገልግሎቶች ግልጽና ተዓማኒነት፣ እንዲሁም ተጠያቂነት በሚያስከትሉ አሠራሮች ታግዘው እንደሚተገበሩ አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና የተቀናጀ መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደርና የኢንፎርሜሽን ሲስተም (ኢንተግሬትድ ፋይናንሻል ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም) ለመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ዘመናዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ዝግጅት ሲደረግበት ቢቆይም፣ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ ግን አልተቻለም፡፡

ይኸውም ከቴክኖሎጂው ግዥና ትግበራ እስከ አስፈጻሚ አካላት በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙት በመቆየቱ ምክንያት እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ዓለማየሁ ጉጆ ከዚሁ ሥርዓት ግዥና መሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወሳል፡፡ እሳቸውን ተክተው በቦታቸው የተሾሙት አምባሳደር ሌላዓለም ችግሮቹ በሙሉ ተስተካክለው ሥርዓቱ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ሊተገበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በፋይናንስ አስተዳደርና በወጪ በኩል ለውጥ እንደሚያመጣባቸው ካስታወቃቸው አዳዲስ አሠራሮች መካከል፣ የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክ ዘዴ ለማሻገር መነሳቱ ነው፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ እንደገለጹት፣ በ2.8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የአሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ትግበራ ተጀምሯል፡፡ በሙከራ ደረጃም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች፣ እንዲሁም በሰባት የፌዴራል ተቋማት ውስጥ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ የመንግሥት ተቋማት ግዥ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ አማካይነት እንደሚካሄድ፣ ይህም ከዚህ ቀደም ሲያጋጥሙ የነበሩ የግዥ ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም በግዥ ሥርዓት ውስጥ የሰዎች ጣልቃ ገብነትን፣ ሙስናን፣ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ማጭበርበርንና መሰል ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ አቶ ጆንሴ አብራርተዋል፡፡ አዲሱ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (ኢ-ፕሮኪውርመንት) የመንግሥትን የተንዛዛ የግዥ ወጪን መቀነስና ግልጽነትን ማስፈን፣ ያስገኛቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ዕፎይታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

አዲሱ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን የሚመራው ስትራቴጂ እንዲህ ያሉ አዳዲስ የግዥና የመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጦችን የሚያመላክቱ ሥርዓቶች ቢተዋወቁም፣ ለጋሾች ግን ሥጋት ያሏቸውን ነጥቦች ከማንፀባረቅ አልቦዘኑም፡፡ የዓለም ባንክን ጨምሮ እንደ አየርላንድ፣ ኦስትሪያና ሌሎች አገሮችን የወከሉ ተሳታፊዎች ሥጋታቸውን ከገለጹባቸው ነጥቦች አንዱ፣ መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት በማሻሻል በራሱ በጀት የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንዲጀምር ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡

ትምህርት፣ ጤና፣ ሴፍቲኔት፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ፋይናንስ የሚያደርጉት በአብዛኛው የውጭ ለጋሾች በመሆናቸውና በእነሱ የተደገፈ የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትም እየተተገበረ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ መንግሥት ያስተዋወቀውን ስትራቴጂ በራሱ በጀትና አቅም በመደገፍ ዘላቂ የማድረግ ብቃቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም አዲሱ የፋይናንስ አስተዳደር ስትራቴጂ አብዛኛው ትኩረቱ በወጪ አስተዳደር ላይ ያጠነጠነ በመሆኑ፣ ከዚህ ይልቅ በበጀት ዑደት ላይ እንዲያተኩር መደረግ አለበት ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር በየክልሉ የመስክ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በየጤና ማዕከላቱና ጣቢያዎች የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እንደሚታይ መታዘባቸውን የጠቀሱት የልማት አጋር ተወካዮች፣ የመድኃኒት እጥረቱ በግዥ ወይም በአቅርቦት ችግር መፈጠሩን ጠይቀዋል፡፡ የመድኃኒት ፈንድና አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ በዓመት ከ6.6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን መድኃኒቶች ግዥ እንደሚፈጽም፣ እስከ 15 ቢሊዮን ብር የሚጠጉ መድኃኒቶችንም እንደሚያሠራጭ በማስታወቅ፣ የመንግሥት የበጀትና የወጪ ሥርዓትን እንዲሁም የተቀናጀ የመንግሥት የፋይናንስ ኢንፎርሜሽን ሲስተምን በመተግበር ለውጥ እየታየበት ስለመምጣቱ አብራርቷል፡፡    

ስለዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ማሻሻያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ደምሱ ለማ፣ መንግሥት የነደፈው ስትራቴጂ የተሟላ እንጂ ወጪ አስተዳደር ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም ብለዋል፡፡ ስትራቴጂው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር መርሆዎችን መሠረት በማድረግ እንደተዘጋጀም ጠቁመዋል፡፡ ላለፉት 14 ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ በቆየው የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት አማካይነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአራት ወይም አምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምዘና መሠረት፣ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም አገሮች ተርታ የሚያስቀምጣት ደረጃ እያገኘች መምጣቷን የገለጹት አቶ ደምሱ፣ ይኸው ምዘና ለአራተኛ ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በጠቅላላው መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ደረጃ (የልማት ድርጅቶችን በጀት ሳይጨምር) ከ450 ቢሊዮን ብር በላይ እያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከአነስተኛ ጀምሮ እንደ ስኳር ልማትና ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ያሉትን ትልልቅ ፕሮጀክቶች አካቶ በመንግሥት የሚተዳደሩ ከ2,000 በላይ ፕሮጀክቶች በአገሪቱ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህን ፕሮጀክቶች ፋይናንስ በሚገባ የማስተዳደር ኃላፊነትም የመንግሥት በመሆኑ፣ የተጠያቂነትና የግልጽነት ሥርዓትን መዘርጋትና ለሁሉም ዜጋ የማሳወቅ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል አዲስ የፋይናንስ አስተዳደር ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳቱን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች