የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ሕገወጥ የመሬት ወረራ አካሂደዋል” በማለት ያፈናቀላቸው የወረገኑ አባወራዎች ጠቅላይ ሚኒስተር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መፍትሔ እንዲሰጧቸው አቤቱታ አቀረቡ፡፡
የወረገኑ ተፈናቃዮች ያቋቋሙት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማክሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በላከው ደብዳቤ፣ በአጠቃላይ የተፈናቀሉት ከ25 ሺሕ በላይ ናቸው ብሏል፡፡
“ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚገፋ ነዋሪ መኖሪያ ቤቱ ፈርሶ ጎዳና ላይ ወድቋል፤” በማለት የሚገልጸው የአቤቱታ ደብዳቤው፣ “ተማሪዎችም ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል፤” ይላል፡፡
‹‹ቤት የፈረሰብን ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት ከአርሶ አደሮች በሕጋዊ ውል ቤት የገዛን ብንሆንም፣ የአርሶ አደሮችን ቤት በመተው ከአርሶ አደር የገዛነውን ቤት በማፍረስ ማፈናቀል አግባብ አይደለም፡፡ ሆን ተብሎ እኛን ብቻ ለማፈናቀል ታስቦ የተደረገ ከፋፋይ ሴራ ነው፤” በማለት ኮሚቴው ገልጾ፣ በ2005 ዓ.ም. የኮንዶሚንየም ምዝገባ በሚካሄድበት ወቅት ሕጋዊ ስለምትደረጉ አትመዝገቡ በመባላቸው ተደራራቢ በደል እንደደረሰባቸው ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው አቤቱታ አስረድቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮች ኑሮ እንደ ከበዳቸው፣ ሕፃናት፣ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና ነፍሰ ጡሮች ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት መጠለያ እንዲሰጣቸው ተፈናቃዮቹ በኮሚቴያቸው አማካይነት ጠይቀዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም. ክረምት መባቻ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ መዋቅሮችን አስተባብሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑ አካባቢ፣ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ ወረዳ 1 አካባቢ ሕገወጥ የመሬት ወረራ አካሂደዋል ያላቸውን ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች በኃይል ማፍረሱ አይዘነጋም፡፡
ከዚያ ጊዜ ወዲህ በተለይ የወረገኑ ተፈናቃዮች ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡምና ለቅሬታቸው ምላሽ እንደሚሰጥ ቢገለጽላቸውም፣ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡