Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተቀናጀ ደጂታል የሕክምና አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጀመረ

የተቀናጀ ደጂታል የሕክምና አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጀመረ

ቀን:

የታካሚዎችን ሙሉ መረጃ አያያዝና መስተንግዶ ወደ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ሥርዓት የሚያስገባ የተቀናጀ ዲጂታል የሕክምና አገልግሎት ሥርዓት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በትግበራ ላይ ዋለ፡፡ ቴክኖሎጂው በካርድ ላይ የተመሠረተ የሕክምና አሠራርን የሚያስቀር፣ ሐኪሞች አጠቃላይ የሕክምና ሒደትና የታካሚዎችን ሙሉ መረጃ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያስገቡበት፣ የሚቀባበሉበት እንደሚሆን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ገልፀዋል፡፡

     የታካሚዎችን የምርመራ ሒደት፣ የሕክምና ክትትል ሥርዓት መዝግቦ የሚይዝ ሲሆን፣ የታካሚዎችን የሕክምና ታሪክን ያለ ውጣ ውረድ ማግኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነም ተነግሮለታል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ታካሚዎች በሚሰጣቸው ኤሌክትሮኒክ የታካሚ መለያ ካርድ (RFID) በመታገዝ ከመድኃኒት ቤቶች መድኃኒት መግዛት፣ የላቦራቶሪ ውጤታቸውን ማየትና ክፍያን መፈፀም ይችላሉ፡፡

     ‹‹ቴክኖሎጂው ለሁሉም መፍትሔ አለው፡፡ ታካሚዎች ከሕመማቸው ውጪ ያሉ ነገሮች ሊያስጨንቃቸው አይገባም፣ ሐኪሞችን እንደዚሁ ከሕክምናው ውጪ ያሉ ነገሮች አያስጨንቃቸውም፡፡ ቴክኖሎጂው ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ያሉ ሌሎች ሒደቶችን ምንም ሳያስቀር መረጃ ስለሚይዝ ነገሮችን ያቀላጥፋል፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

     ሐኪሞች የታካሚዎቻቸውን መረጃ በእጅ ጽሑፍ መልክ የሚያሰፍሩበት በኢትዮጵያውያን ወጣት ባለሙያዎች ዲዛይን የተደረገ ታብሌት መኖሩን ይህም በኮምፒውተር ላይ በፍጥነት ለመፃፍ ለሚቸገሩት እንደሚያግዝ ታውቋል፡፡
ቴክኖሎጂው የታካሚዎችን እንግልት እንደሚያስቀር፣ የሐኪሞችን ድካም የሚቀንስ ነው ተብሎለታል፡፡

    ሆስፒታሉ በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ (በየቀኑ 1,500) ሰዎችን እንደሚያስተናግድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ አክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ ዳዊት ወንድማገኝ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

     ‹‹በየቀኑ የ1,500 ሰዎች ካርድ ሲወጣ ሲገባ ይውላል፡፡ ለ50 ዓመታት ያህል በዚህ መልኩ ነው የሠራነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ካርድ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሕመምተኞች ብዙ ጊዜ ካርዳቸው ጠፍቶ ይጉላላሉ፡፡ የምርመራ ውጤታቸው ጠፍቶ እንደገና እንዲመረመሩም ይደረጋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የሕክምና ካርዶች ከካርድ ክፍል ወጥተው ሐኪሙ ጋ እስኪደርሱ ባለው ሒደት ውስጥ ጠዋት እንዲታከም የተቀጠረ ሰው ሳይታከም 4 ሰዓት ያልፍበታል፡፡ አዲስ የተዘረጋው ቴክኖሎጂ ግን እነኚህን ሁሉ ችግሮች ይቀርፋል፤›› በማለት ቴክኖሎጂው በጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

     ይህ በኤሌክትሮኒክ ካርድ ላይ የተመሠረተው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀጣይነት ባለው መልኩ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በተቀናጀ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ሕክምና መከታተል ያስችላል፣ የተቀናጀ የመልዕክት መላላኪያ ዓምድ አለው፣ እንደ ኤምአርአይ ካሉ የሕክምና መሣሪያዎች የሚገናኝና በእነዚህ መሣሪያዎች የሚታከሙ ሕሙማንን መረጃ ይይዛል፣ መድኃኒት ቤቶችን ከቤተሙከራዎች፣ ከሆስፒታሎች ጋር በማገናኘት የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ይፈጥራል፣ የታካሚውን መረጃ በቀላሉ መጋራት የሚያስችል ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ሆኖም ያገለግላል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት የታካሚዎችን ውጤት ከነትንታኔያቸው አካቶ የሚይዝ እንደሚሆን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

         ከዚህ ባሻገርም በሐኪሞች መካከል ባሉበት ሆነው ቴሌኮንፈረንስ ማካሄድ የሚያስችላቸው መሆኑም የሕክምና ሒደቱ ቀላልና የታካሚዎችን እንግልት የሚቀንስ ነው፡፡ ‹‹የታካሚውን የራጅ ውጤት አይቼው መረዳት ቢያቅተኝ የራጅ ባለሙያውን እዚያው በቴሌኮንፈረንስ አናግረዋለሁ፡፡ በነበረው አሠራር ግን ታካሚውን ለሌላ ጊዜ እቀጥረውና ባለሙያውን አማክራለሁ፤›› በማለት አዲሱ አሠራር ታካሚውን ከመጉላላት፣ ባለሙያውም ጊዜው ከመባከን የሚታደገው እንደሆነ ዶ/ር ዳዊት ተናግረዋል፡፡

ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በይፋ ሥራው በተጀመረበት ዕለት ቴክኖሎጂው በአገሪቱ ወደሚገኙ ሌሎች ሆስፒታሎች ለመዘርጋት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከክልል የጤና ቢሮዎች ጋር የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

     ሥርዓቱ የተዘረጋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ትብብር ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪውን የሸፈነው ሚኒስቴሩ ነው፡፡ በዕለቱ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፣ ‹‹የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ይህ የኔ ችግር ነው፤ ያ ደግሞ የእገሌ ነው ሳይባባሉ ችግሮች ሁሉ የጋራችን ናቸው፣ የምንወጣቸውም አንድ ላይ ተቀናጅተን ነው በሚል መርህ ተጣምረው እንደዚህ መሥራቸው በምሳሌነት የሚወሰድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

     ለሌሎች የሕክምና ተቋማትም አሠራሩ በቅርብ ጊዜ ተዘርግቶላቸውና በመረጃ መረብ ተሳስረው የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ የሆነ የተቀላጠፈ ሕክምና የማግኘት ችግር መቅረፍ እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በየጤና ተቋማቱ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት መንግሥት በግንባር ቀደምነት እንደሚደግፈውም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...