Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተምሳሌታዊ ጅምር

አቶ አበበ ድንቁ በንግድ ሥራ ሙያ የካበተ ልምድ ያላቸው ወጣት ባለሀብት ናቸው፡፡ ከሰሞኑ የታሸገ የማዕድን ውኃ ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ለሥራ ማዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ‹‹አበበ ድንቁ የውኃና ከአልኮል ነፃ መጠጦች ማምረቻ ፋብሪካ›› የተሰኘው ድርጅታቸው ቶፕ ውኃ የተባለ የማዕድን ውኃ ለገበያ ለማቅረብ ሲነሳ፣ ይዟቸው የተነሳቸው ዓላማዎች ግምት የሚሰጣቸው ሆነዋል፡፡ አንደኛው ጥቅም ላይ የዋሉትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች መሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከውኃ ሽያጩ ከሚገኝ ዓመታዊ ገቢ ታሳቢ ተደርጎ በየዓመቱ ስምንት የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶችን በማስቆፈር የንጹህ ውኃ አቅርቦት ችግር ያለባቸውን አካባቢዎችና ነዋሪዎችን ለማገዝ መነሳቱ የአቶ አበበ ድንቁን የውኃ ፋብሪካ የተለየ አድርጎታል፡፡ በቅርቡ በሪፖርተር ዘገባ በተስተናገደው መሠረት፣ የአቶ አበበ ድንቁ የውኃ ፋብሪካ በዓመት ከ66 ሚሊዮን በላይ ፕላስቲክ የውኃ መያዣ ጠርሙሶችን በየዓመቱ እንደሚሰበስብ ማስታወቁን መጥቀሳችን አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ያሉትንና ሌሎችም ጉዳዮችን በማንሳት ብርሃኑ ፈቃደ ከአቶ አበበ ድንቁ ጋር ያደረገው አጭር ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡– ቶፕ ውኃ ማምረቻን ዕውን ከመድረግዎ በፊት ሌሎች ሥራዎችን እንደሚሠሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የውኃ ማምረት ሥራውን እንዴት እንደጀመሩት በማብራራት ብንጀምር፡፡

አቶ አበበ፡ ሌሎች ሥራዎች ነበሩን፤ አሁንም ይኖሩናል፡፡ ብዙ የለፋንበት በብዙ አገሮች ዞረን ልምድ ያገኘንበት ይህ የቶፕ ውኃ ፕሮጀክት ስለሆነ በአሁኑ ወቅት ትኩረት የምንሰጠው ለውኃው ምርት ነው፡፡ ከጎረቤት ኬንያ ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ፣ በዱባይ፣ በቻይና፣ በጀርመን፣ በኦስትሪያ፣ በአሜሪካና ሌሎችም አገሮችን በመጎብኘት የውኃ አመራረት ሒደትና የጥራት አሠራርን ለማጥናት ሞክረናል፡፡ በሌላው አገር ውኃ የቅንጦት ሳይሆን የጤንነት መጠጥ ነው፡፡ በእኛ አገር እንደ ቅንጦት የሚታይበት ወቅት ነበር፡፡ አሁን ግን ማኅበረሰባችን እየተረዳው መጥቷል፡፡ በብዛት እየተጠቀመበት ነው፡፡ ውኃው እስካለ ድረስ ያለማቋረጥ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ እንግዲህ በዘላቂነት ጥቅም ላይ የሚውልና ለጤና አስፈላጊ የሆነ ነገር ደግሞ ንጽህናውና ጥራቱ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ንጹህና ጥሩ ነገር ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ሰው ሁልጊዜ በምትሰጠው መጠን ይለካሃል፡፡ ቶፕ ውኃ ምንድን ነው የሚለውን እኔ መናገር አይጠበቅብኝም፡፡ ሥራዬ ነው መናገር ያለበት፡፡ የተሻለ፣ ጥራት ያለውና ጥሩ ነገር ለሕዝብ ማሳየት ይኖርብናል፡፡ የቶፕ ውኃ ማምረቻን ስንሠራ ማምረቻ ቦታውን ከውጭም ጭምር ነው ያሰብንበት፡፡ መጠጥ ነክ ምርት ከአካባቢ ንጽህና አኳያ ማሟላት የሚጠበቅበትን አካሄድ ለመከተል ሞክረናል፡፡ ከግቢ ውጪ ያለውን የፋብሪካውን ዙሪያ በተቻለን መጠን በኮብል ስቶን ደልድለናል፡፡ ይህም ብናኝ ነገሮችንና አቧራን ለመቀነስ በማሰብ ጭምር ያደረግነው ነው፡፡ ፋብሪካው ውስጡና ውጪው በሙሉ ዘመናዊ አሠራርን የሚከተል፣ አንድ የምግብና የመጠጥ ፋብሪካ ማሟላት የሚጠበቅበትን ደረጃ አሟልቶ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ ፋብሪካውን ለመጎብኘት የሚሔድ ሰው በቀጥታ ወደ ምርት ሥፍራው መግባት አይችልም፡፡ ይህም ንክኪና አለስፈላጊ ብክለትን ለመከላከል በማሰብ የተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ ወደ ታች ሆኖ የምርት ሒደቱን የሚከታተልበት ሥፍራ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰው ሲገባ የአየር እጥበት ወይም ‹‹ኤር ሻወር›› ይደረግለታል፡፡ ይህ ባክቴሪያና ሌሎችም በካይ ነገሮችን ለመከላከል ሲባል የተደረገ ቅድመ ጥንቃቄ ነው፡፡ የላቦራቶሪ ዕቃዎቻችን የጣልያን ሥሪት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰዓት 18 ሺሕ ትንንሽ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን፣ ትልልቁን ባለ 20 ሊትር በሰዓት 900 ጠርሙሶች የማምረት አቅም ያለው ማምረቻ ተክለናል፡፡ በ12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ተጨማሪ ማስፋፊያ እያካሄድን ሲሆን፣ በሰዓት 24 ሺሕ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚያመርት ማሽን ለመትከል ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ በጠቅላላው በሰዓት 42 ሺሕ ሊትር የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ይኖረናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በርካታ አገሮችን ጎብኝተናል ብለዋል፡፡ ከጉብኝታችሁ በመነሳት እኛ ውኃ በፋብሪካ በብዛት እንደመመረቱ በእኛ በኩል ምን እንደሚጎድል፣ ምንስ የተሻለ ነገር እንዳለ ያያችሁበት አጋጣሚ አለ?

አቶ አበበ፡ እኛ አገር ውስጥ በተለይ በምግብ አመራረት ረገድ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ታዝበናል፡፡ ፋብሪካ ጉብኝት የሚመጣ ሰው ወደ ምግብ ማቀነባበሪያዎች የሚገባበት መንገድ መሻሻል አለበት፡፡ የማምረቻ መሣሪዎቹን ለማየትና ለመጎብኘት ሲባል ወደ ምርት ክፍል የመግባት ሥርዓቱ መቀየር አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብክለትና ንክኪን ማስቀረት ይቻላል፡፡ እኛ ይኼንን የሚያረጋግጥ አሠራር ለመከተል ሞክረናል፡፡

ሪፖርተር፡– ከንግግርዎ በአገራችን የምርት ሒደት በተለይ የምግብ ነክ አመራረት ሥርዓት ውስጥ የንጽህና አሠራር ትኩረት ይሻል እያሉ ነው?

አቶ አበበ፡በሌሎች አገሮችም የሚደረገው እኮ ከምርት ክፍል ባለሙያዎች በስተቀር ወደዚያ ክፍል መግባት ክልክል ነው፡፡ ከውጭ ወደ ማምረቻው አካባቢ የሚገባ ሰው ይዞ የሚገባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ የሚመረተውን ምግብም ሆነ መጠጥ ደህንነት ሥጋት ውስጥ ይከቱታል፡፡ በመሆኑም ወደ ፋብሪካ የሚመጡ ጎብኚዎች ከንክኪ በራቀና ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ሥፍራ ሆነው መጎብኘት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡– ፋብሪካው ከመነሻው በትልቁ ነው የጀመረው፡፡ ፋብሪካውን ዕውን ለማድረግ ሁለት ዓመት እንደፈጀ ታውቋል፡፡ ግንባታው አንድ ዓመት ቢፈጅም ተጨማሪ አንድ ዓመት ግን ከጥራት ጋር በተያያዙ ሥራዎች ምክንያት እንደሆነ ሲገልጹ ተደምጠዋልና ስለዚህ ቢያብራሩልን?

አቶ አበበ፡ የተሻለውን ለመሥራት በርካታ አማራጮችን ለማየትም የፈለግነው አካባቢያችን ላይ ባለው ብቻ ተወስነን ሳይሆን፣ ሌላው ዓለም እንዴት እንደሚሠራበት፣ ኢንዱስትሪው ምን እንደሚመስል ለማየትም ነው በየአገሩ መዞር ያስፈለገን፡፡ የተሻለ ለመሥራት ጊዜ መስጠታችን ተገቢ ነበር፡፡ እንደተሳካልንም አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– በአገሪቱ 67 ያህል የውኃ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ውኃ በማምረት ሒደት ከእነዚህ ሁሉ የጨመራችሁት የተለየ ነገር ምንድን ነው?

አቶ አበበ፡ ጥራት ምንጊዜም አዲስ ነገር ነው፡፡ ተመሳሳይ ነገር ልትሠራ ትችላለህ፡፡ ጥራትን ግን ለዘለቄታው ከጠበቅህ ይኼንን ማደረግ መቻልህ የተለየ ነገር ነው፡፡ ልዩነቱም የጥራት ልዩነት ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– እስካሁን ከታየው በተሻለ መንገድ እናንተ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንደምትሰጡ አስታውቃችኋል፡፡ የምርት ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን መልሳችሁ በመሰብሰብ ብክለትን እንደምትቀንሱ አስታውቃችኋል፡፡ እንዴት ልትተገብሩት ተነስታችኋል? የዚህን ሥራ ዘላቂነትስ እንዴት ነው የምታረጋግጡት?

አቶ አበበ፡ በፕላስቲክስ ሥራ ውስጥ ልምድ አለን፡፡ ከአራት ዓመት በፊትም በዚህ ሥራ ውስጥ ነበር፡፡ ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ወይም ሪሳይክል በማድረጉ በኩል ጀማሪ አይደለንም፡፡ በሌሎች አገር ውስጥ እንዳየነው ለዚህ ሥራ የሚረዳንን ማሽን በመግዛት ጥቅም ላይ የዋለውን የራሳችንን የምርት ማሸጊያ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን አሠራር ዘርግተናል፡፡ ብራንዳችንን ለመጠበቅና ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋፅኦ ለማድረግ ሲባል የራሳችን ምርት የቀረቡባቸውን ፕላስቲክ ጠርሙሶች በጥሩ ዋጋ መልሰን እንሰበስባለን፡፡ እርግጥ የሌሎችንም ምርቶች ማሸጊያዎች እንሰበስባለን፡፡ ቅድሚያ ግን ለእኛው ምርት እንሰጣለን፡፡ የውኃ ማሸጊያዎቹን ጠርሙሶች ለሚሰበስቡ ሰዎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር እናግዛለን፡፡ 

ሪፖርተር፡– መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለው የፕላስቲክ ጠርሙስ ወደ ውጭ እንደሚላክ ሲነገር ሰምተናል፡፡ ይህ እንዴት ነው የሚሆነው?

አቶ አበበ፡ አገር ውስጥም ሒደቱ ተጀምሯል፡፡ በዱከም ከተማ ትልቅ ፋብሪካ እየተቋቋመ ነው፡፡ ፋብሪካው መልሶ ጥቅም ለማዋል የሚያስችል የፕላስቲክ ውጤት በብዛት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ፋብሪካ ጋር ስምምነት አድርገናል፡፡ እኛ መልሶ ጥቅም ላይ መዋል የሚችለውን ፕላስቲክ በሚፈለገው መሠረት በማሽን ተዘጋጅቶ እናቀርብላቸዋለን፡፡ ውጭ የሚላከውም በርካታ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሰው ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ፋብሪካዎች ግብዓት እንዲሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ጥቅም ላይ የዋለውን ፕላስቲክ መሰብሰብ አንዱ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ግን በኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት መስክም የምትሠሩት ሥራ እንዳለ አስታውቃችኋል፡፡ ከሽያጭ ገቢያችሁ ተሳቢ የሚደረግ፣ በዓመት እስከ አምስት የውኃ ጉድጓዶች በማስቆፈር የመጠጥ ውኃ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች አስተዋፅኦ የማድረግ ሐሳብ እንዳላችሁም ይፋ አድርጋችኋልና ስለዚህ ሐሳብ ቢያብራሩልን?

አቶ አበበ፡ በጣም የሚያስደስተኝ፣ ማውራትም የምፈልገው ስለዚህ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ተግባር ያለ ጥርጥር የማደርገው ነው፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ከሽያጫችን በመቶኛ እየሰበሰብን የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች እየሔድን ውኃ ለማቅረብ የምንሠራበትን ሥልት አዘጋጅተናል፡፡ ጉድጓድ ቆፍረን ውኃ በማውጣት የመጠጥ ውኃ ለሌላቸው የማዳረስ ሥራ እንሠራለን፡፡ ፋብሪካው እስካለ ድረስ ይህ ተግባር ይቀጥላል፡፡ አይቆምም፡፡ የውኃ ችግር ተቃሏል የሚባልበት አካባቢ ብንደርስ እንኳ ወደ ጤና ጣቢያ፣ ወደ ትናንሽ የገጠር መሥራቱ ትህምርት ቤት እንቀጥላለን እንጂ አናቆምም፡፡ ያገኘነውም ከወገን ነው፡፡ ለምናካፍለውም ለወገን በመሆኑ ይህ ዓይነቱ ሥራ የሚቀር ነገር አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡– በሰዓት 42 ሺሕ ጠርሙስ ውኃ ለማምረት እየተዘጋጅሁ ነው፡፡ ይህ መጠን ቶፕ ውኃ ወደ ገበያ ሲገባ ምን ያህል የሽያጭና የምርት ድርሻ መያዝ ይችላል ማለት ነው?

አቶ አበበ፡ የምናመርተው ለመሸጥ ብቻ ሳይሆን፣ ጥራትንም በሚገባ ለማስተዋወቅ ጭምር ነው፡፡ ጥራት ዋስትናችን በመሆኑ የገበያ ችግር አይኖርብንም፡፡

ሪፖርተር፡- እግረ መንገዳችንን ከሰሞኑ በማኅበራዊ ድረገጽ ስለ ታሸገ ውኃ ከተሰጡ ሐሳቦች አንዱን ላንሳ፡፡ ‹የታሸገ ውኃ መጠጣት ምንም የተለየ ፋይዳ የለውም፡፡ እንደውም ውኃ በመያዣ ታሽጎ ያለ እንቅስቃሴ መቀመጡ ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲራቡበት የሚያመች መንገድ ይፈጥራል እንጂ ውኃው ብዙም ጥቅም የለውም፡፡ የላስቲክ ውኃ አልጠጣሁም ብላችሁ አትዘኑ ይልቁንም የቧንቧ ውኃ ጠጡ፡፡ ከተጠራጠራችሁት ግን አፍሉት፤› የሚል ሐሳብ ተጽፎ አይቼ ነበር፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ? 

አቶ አበበ፡ እኔ የውኃ ወይም በውኃ ላይ የሚሠራ ባለሙያም ባልሆን በሥራው ካገኘሁት ልምድና መረጃ አኳያ ግን ለሰው ልጅ የሚጠቅመው የውኃና የማዕድናት ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት፣ ውኃው ውስጥ መገኘት ስለሚገባው የማዕድን ይዘትና ምጣኔ በጥልቀት የሚያውቁ ባለሙያ አብረውን እየሠሩ ነው፡፡ ከእኔ ይልቅ በዚህ መስክ ልምድም ከፍተኛ የሙያ ዕውቀትም ያላቸው ናቸው፡፡ እንዲህ ላለው ጥያቄ እሳቸው ሳይንሳዊ ምላሽ አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ውኃው ገበያ ላይ የሚውለው መቼ ነው? ወደ ውጭ የመላክ ሐሳብስ አላችሁ?

አቶ አበበ፡ ውኃውን በተገቢው መንገድ ለማምረት በሙሉ አቅም ለመግባት እየተዘጋጀን ነው፡፡ በቂ የምርት ክምችት መያዝ እንፈልጋለን፡፡ ምርቱ ሳይቋረጥ ገበያ ላይ እንዲውል የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለገበያ ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡– ወደ ውጭ ገበያዎችስ ምን አስባችኋል? እንደ ጂቡቲ ያሉ ጎረቤት አገሮች ሰፊ የገበያ አድማስ እንደሆኑ ይታመናል፡፡

አቶ አበበ፡ ሱዳን፣ ጂቡቲና ኬንያም ጭምር የመሔድ አቅም አለን፡፡ የምናመርትበት ጥራት በኬንያ አንዳንድ አምራቾች ዘንድ እንዳየነው ውኃ መሙላት ላይ ያተኮረ ብቻ አይደለም፡፡ ጥራታችን ከውጭ አመራቾችም ጋር ለመወዳደር ያስችለናል፡፡ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያግደን ነገር አይኖርም፡፡ እስከ 80 በመቶ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስቸለን አቅም ስላለ ገፍተን እንደሔድበታለን፡፡

ሪፖርተር፡– ከጥሬ ዕቃ አኳያም ለማሸጊያ የሚያስፈልገውን አብዛኛውን ነገር በራሳችሁ እንደምታመርቱም ገልጻችኋልና ከዚህ አኳያ ያላችሁ አሠራር ምን ይመስላል?

አቶ አበበ፡ ሁሉንም ለማሸጊያነት የሚውለውን ምርት በራሳችን ፋብሪካ እናመርታለን፡፡ ለገበያ እንደሚቀርበው ምርት ሁሉ ለማሸጊያውና ለጥሬ ዕቃውም አመራረት ጥንቃቄ አድርገናል፡፡ ውኃው ሲሞላ የምናደርገውን የአመራርት ጥንቃቄና የጥራት ደረጃ በዚህም በኩል እንተገብራለን፡፡ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሚውልን አገላለጽ ማንም ወደ እኛ መጥቶ ቢያይ የሚያረጋግጠው ይመስለኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡– ቶፕ ውኃ የዛሬ ሦስት ዓመት የት ደርሶ ልናየው እንችላለን?

አቶ አበበ፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ከውኃው ጎን ለጎን የጭማቂና የለስላሳ መጠጦችን እያመረትን እንሔዳለን ብለናል፡፡ የኢንቨስትመንትና የንግድ ፈቃዳችንም በዚሁ አግባብ የወጣ በመሆኑ ውኃውን፣ ከጭማቂና ከለስላሳ መጠጦች ጋር አብረን እናስኬዳለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...