Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያገባናል!

የዛሬው ጉዟችን ከፒያሳ ካዛንቺስ ነው፡፡ ውድ ታታሪ የታክሲ ደንበኞች እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ፡፡ መኪና ልግዛ ብዬ ከወር ደመወዜ ላይ አንድ ሳንቲም ሳልቀንስ ብቆጥብ እንኳን፣ ቢያንስ ከሃያ እስከ ሰላሳ ዓመት መቆጠብ ይጠበቅብኛል፡፡ ቪትዝ ዋጋዋ አሁን አሁን ጣሪያ ነክቶ የቅብጠት ዕቃ እንደ መሆን እየዳዳት ነው፡፡ ይህንን ስል ያው ‘ለእንደኔ ዓይነቱ’ የሚለውን  ልብ በሉልኝ፡፡

ታታሪ የታክሲ ደንበኞች የሆናችሁ ተጠማዞ ‘ሰለሜ ሰለሜ’ የሠራ የታክሲ ሠልፍ ውስጥ በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ መገኘት የግድ ነው፡፡ መቼም ተራ ላይ የሚፈጠር ስንት ጉድ አለ? አንዳንዱ በጠራራ ፀሐይ የቆመው ሰው ግድ የማይለው፣ ባገኘው አጋጣሚ ዘሎ አንደኛ ሆኖ ለመግባት ሲጋፋ ለተመለከተው ተደባደበው፣ ተደባደበው ያሰኛል፡፡ ማንም ቶሎ ቤቱ ቢደርስ ጠልቶ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ሰውን አክብሮ፣ ራሱንም አክብሮ ነው ተሠልፎ የቆመው፡፡ አራዳ የሆኑ የሚመስሉ ሰዎች ሠልፍ ሰብረው በመግባት ያቆስሉናል፡፡ ኑሮና የዘመኑ ፖለቲካ ያቆሰለን አልበቃ ብሎ በእነዚህም ስንቆስል እንውላለን፡፡

ረጅሙ ሠልፍ እንደ ምንም አልቆ እኛም ወግ ደርሶን ተሳፍረናል፡፡  ወያላው ድንገት ሳናስበው፣ ‹‹መቼም ከዓብይ በኋላ ዘርዘር ብሎ ተበታትኖ ታክሲ ይጠብቅ የነበረው ተሳፍፋሪ ሁሉ፣ አሁን ምንም ሳይፈራ ችምችም ብሎ በኩራት ታክሲ መጠበቅ ጀምሯል፤›› በማለት ወሬውን ጀመረ፡፡ የታክሲ ወሬአችን ሊደራ ነው፡፡

‹‹ዘመነ ዓብይ ማለት እኮ ክልክል ራሱ የተከለከለበት ነው፤›› በማለት ሾፌሩ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ ወዲያው ‹‹ክልክል ተከልክሏል›› የሚል ርዕስ የያዘ ወግ ተጀመረ፡፡ ታዲያ ይህ የወያላውና የሾሬሩ ንግግር የጣመው ወጣት፣ ‹‹እኔማ እንዲያውም መንግሥት የተመሠረተው ለመከልከል ይመስለኝ ነበር፤›› በማለት ሳቀ፡፡ ወጣቱ በዚህ አላበቃም፡፡  “ፖሊሶችን ሳስብ ለመከልከል ወይም ለመቀጥቀጥ የተፈጠሩ እንጂ፣ ሕዝብን ለመጠበቅና የሕዝብ አለኝታ ለመሆን የተሰማሩ አይመስለኝም ነበር፤›› በማለት ደግሞ ቅሬታውን ተናገረ፡፡ በዚህ ሐሳብ የተደሰተው ወያላ፣ ‹‹እውነትህን እኮ ነው፡፡ ያደላቸው አውሮፓውያን ችግር ሲያጋጥማቸው ወዲያው ወደ 911 ደውለው ፖሊሶቻቸው በአስቸኳይ ደርሰው ይታደጓቸዋል፡፡ እኛ ዘንድ ደግሞ በተቃራኒው ሰው ፖሊስ ሲያይ ደንብሮ ሊሮጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ችግር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ነበር የነበረው፤›› በማለት ብሶቱን ተነፈሰ፡፡ ይኼን ጊዜ ነበር አንድ ጎልማሳ ወሬውን የተቀላቀለው፡፡ ‹‹እንግዲህ ሕዝቡን ይጠብቃሉ ተብለው የታሰቡት ለሕዝብ ማስደንገጫ ሲውሉ፣ ያኔ አገር ለመውደቅ እያዘመመች መሆኑን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል፤›› አለ፡፡

ቀልደኛው ወያላ፣ ‹‹መቼም ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ሕዝቡንና ፖሊስን ማስታረቅ መሆን ይኖርበታል፤›› በማለት ፈገግ አለ፡፡ ይህን የሰማው ሾፌር፣ ‹‹ወይ አንተ? እሳቸው ወጣ ወጣ ማለት ጀምረዋል፡፡ የውስጥ ችግራችንን በመጠኑም ቢሆን አርግበው ወደ ውጭ ማየት ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ አሁን የውጭ ጉዳይ ላይ ነው የሚገኙት…..›› በማለት መለሰ፡፡ ወሬያችን እየጦፈ ነው፡፡ ወረፋ ሳይጠብቅ ታክሲያችን ውስጥ የገባው ጎረምሳ ከአንዲት ቆንጆ ብርቱ ሙግት አጋጥሞታል፡፡ ልጅቷ እስኪፀፅተው ድረስ አስጨነቀችው፡፡ ‹‹ለስሙ ሲያዩህ ዘመናዊ ትመስላለህ ዳሩ ግን ፀጉር ብቻ ነህ፡፡ ምንም ጭንቅላት የለህም፤›› እያለች አበሳውን አሳየችው፡፡ ልጁም እየተሳቀቀ፣ ‹‹ረፍዶብኝ ነው፡፡ ምናለበት ብትረጂኝ? አይገባሽም እንዴ የሰው ችግር?›› አላት፡፡ ይኼኔ ባሰባት፡፡ ‹‹እዚያ ታክሲ ተራ ተሠልፈን ያየኸን የሥራ ፈቶች ማኅበር አባላት መስለንሃል እንዴ? ተከባብረን እኮ ነው የተሠለፍነው፤›› በማለት ወረደችበት፡፡ ድንገት ሳይታሰብ፣ ‹‹ወራጅ አለ! በቃ አውርዱኝ!›› በማለት በምሬት ተናገረ፡፡ ይኼኔ ፀፀቱ ምን ያህል ዘልቆት እንደገባ ተገነዘብን፡፡

ወያላውም፣ ‹‹በቃ ዋናው በድጋሚ ሠልፍ አለመስበርህ ነው፡፡ አሁን ዝም በልና እንሂድ፤›› አለው፡፡ ወጣቱም፣ ‹‹ምነው ይኼን ያህል ሕገ መንግሥቱን የተላለፍኩት አስመሰለችው እኮ? ኧረ እኔ እወርድላታለሁ ይስፋት፤›› በማለት አለቃቀሰ፡፡ ሌላ ሰው መናገር ጀመረ፣ ‹‹ዋናው መውረድህ አይደለም፣ ዋናው ነገር ለሚቀጥለው ጊዜ ይህንን አጉል ልማድህን መተውህ ነው፡፡ እዚህ ወርደህ ሌላ ታክሲ ውስጥ ያለ ወረፋህ ብትገባ ምንም ጥቅም የለውም፤›› በማለት አሁንም ሌላ ተግሳፅ አወረደበት፡፡

ልጅቷ በቀደደችለት ቦይ ላይ እየፈሰሰ አብዛኛው ሰው ወጣቱን በሐሳብ ኮረኮመው፡፡ ይኼኔ ቤተ መንግሥት ደርሰን ነበር፡፡ “መቼም ስህተት ሲሠራ ሲያይ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ ሆ ብሎ ቢነሳ ኖሮ የት በደረስን ነበር ያስብላል፡፡ ያው ሁሉም ሰው ምን አገባኝ እያለ ስለሚያይ ነው ይህ የእኔ ጉዳይ አይደለም ማለትና አያገባኝምን ትቶ ወደ ያገባኛል አስተሳሰብ ውስጥ ከገባ ለመለወጥ 30 ዓመት ይበቃናል፤›› ያለችን ወጣቱን ቁም ስቅሉን ያሳየችው ቆንጆ ናት፡፡

ይህች በታክሲያችን ውስጥ ነግሳ የቆየችው ወጣት አሁንም ኃይሏን አደራጅታ መጣች፡፡ አንድ የታሸገ ውኃ ይጠጣ የነበረ ሰው የፕላስቲክ ጠርሙሱን ታክሲው መቀመጫ ሥር ሲጥል ተመልክታ ድጋሚ መናገር ጀመረች፡፡ ይህም ሳያንሳት ከሥር የፕላስቲክ ጠርሙሱን አውጥታ ለሰውዬው አስያዘችው፣ ‹‹ይህ ያንተ ቆሻሻ ነው፡፡ ስለዚህ ራስህ ያዘውና ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጣለው፡፡ ቢያንስ የራስህን ቆሻሻ ቻል፤›› በማለት የፕላስቲክ ጠርሙስን ሰጠችው፡፡ ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹መቼም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላዩሽም እንጂ እንዳንቺ ዓይነት ሰው ሲፈልጉ እንደነበር ሰምቻለሁ፤›› በማለት ተበሳጭታ ስትናገር የነበረችውን ቆንጆ ረገብ አደረጋት፡፡

በዚህ መሀል አንዱ፣ “እስቲ ኑረዲን ኢሳ የተባለ ገጣሚ ‘ምን አገባኝ’ በማለት የጻፉትን ግጥም ስሙ፤” ሲለን ጆሮአችንን ቀና አደረግን፡፡

“እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ፣

እርሱ ነው አገሬን ያረዳት እንደ በግ፤

የሚል ግጥም ልጽፍ ብድግ አልኩኝና

ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና፤”

የልጅቷን ተቆርቋሪነት ሁሉም ተሳፋሪዎች አደነቁላት፡፡ ይኼኔ አንድ በወጣቷ ሁኔታ ያልተደሰተ ሰው፣ “አሁን እስቲ ማን ይሙት አዲስ አበባ ውስጥ በየመንገድ ዳር የወደቁትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች በሙሉ ባለቤቶቻቸውን እያፈላለግሽ ልታከፋፍይ ነው?›› በማለት እንደ መሳለቅ አለ፡፡ እሷስ ቢሆን መቼ መልስ አጥታ? ‹‹ቢያንስ የራስህን ቆሻሻ ቻል!›› የሚል አጭር መልስ ሰጠችው፡፡ እርሱም፣ ‹‹ምነው አንቺ ያገባኛል፣ ያገባኛል አልሽሳ?›› በማለት አሁንም ሌላ ጥያቄ አቀረበላት፡፡

ልጅት አሁንም እሳት ጎርሳ እሳት ለብሳ ተነሳች፣ ‹‹የምንኖርባት አዲስ አበባ ንፅህና ጉዳይ ያገባኛል፡፡ የአገሬ ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ያገባኛል፡፡ ሰዎች ያልተገባቸውን ሲያደርጉ ዓይቼ እንዳላየ ሆኜ አላልፍም፣ ምክንያቱም ያገባኛል፡፡ ይህች አገሬ ናት፣ የሚኖሩባትም የምወዳቸው ኢትዮጵያዊያን እህቶችና ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የሚደረገው ማንኛውም በጎም ሆነ ክፉ ነገር ያገባኛል፡፡ ስለዚህ ዝም አልልም፡፡ እውነት ነው ብዬ የማምንበትን ሁሉ በነፃነት እናገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ያገባኛል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በዙሪያችን ያለው ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ጉዳይ በሙሉ ያገባናል ማለት አለብን…..›› በማለት የሚገርም የንግግር ብልጫ አሳየች፡፡ እኛም ካዛንቺስ ደርሰን “መጨረሻ” ተብለን በየፊናችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት