ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ዓ.ም. ከጂቡቲና ከሱዳን ቀጥለው ባደረጉት ሦስተኛው የውጭ አገር የሥራ ጉብኝት ከሚያዝያ 28 እስከ 29 ቀን 2010 ወደ ኬንያ በማቅናት፣ በጂቡቲና በሱዳን ከተደረጉት መግባባቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ስምምነቶች ላይ ደርሰው ሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ተመልሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ከተሰየሙ በኋላ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ይዘው የመጡትን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሞኒካ ጁማ (ዶ/ር) የጉብኝት ግብዣ ተቀብለው ኬንያ ሲገቡ አምባሳደሯ፣ የማኅበራዊና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ኡኩር ያታኒና የናይሮቢ ከተማ ገዥ ማይክ ምቡቪ ሶንኮ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በነጋታው በኬንያ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለክብራቸው 19 ጊዜ መድፍ ሲተኮስ፣ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቤተ መንግሥታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኬንያታ፣ ‹‹ኬንያ ሁሌም ኢትዮጵያን እንደ ወንድም ነው የምታየው፡፡ ከነፃነታችን በፊት ጀምሮ በትብብር ስንሠራ ነበር፡፡ ኬንያ ነፃነቷን እንድታገኝም ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች፤›› ብለዋል፡፡
ከኬንያ ፕሬዚዳንት ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ቀላል የሁለትዮሽ ጉዳዮችን ወደ ጎን በማለት፣ ‹‹ታሪካችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ ተስማምተናል፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ልናፈርሰው የማይቻለንን መሠረት አኑረውልናል፡፡ ይልቁንም እኛ በላዩ ላይ ልንገነባ ነው የሚገባው፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ኬንያታ ጋር በደኅንነት፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን በማድረግ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
‹‹ኬንያ በብቸኝነት የመከላከያ ትብብር ስምምነት ያላት ከኢትዮጵያ ጋር ሲሆን፣ ምንም እንኳን ሁለታችንም ብጥብጥ በነገሠበት አካባቢ ብንኖርም፣ አንዳችን ለአንዳችን ከመቆምና ከመተባበር ቦዝነን አናውቅም፤›› ያሉት ኬንያታ፣ ‹‹ሁሌም አብረን ነበርን፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራና ጥላሸት ሊያጠላበት የቻለ ምንም ክፉ ታሪክ የማይጋሩ መሆናቸው፣ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ከኬንያ ጋር ባለን ግንኙነት እጅግ አስደሳቹ ነገር በሁለታችን መካከል በክፋት መተያየት፣ ምንም ዓይነት ቂም፣ ምንም ዓይነት የጦርነት ታሪክ የሌለን መሆናችንና በደም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ ብሎም በበርካታ እሴቶች የተሳሰርን ስለሆንን ያንን ማጎልበት፣ ማጠናከርና ለልጆቻችን ማስተላለፍ አለብን፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱን አገሮች ግንኙነቶች አሞካሽተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን ጉዟቸው እንዳደረጉት በኬንያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ኬንያውያን ተለቀው ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
የእስረኞች መፈታትና ወደ አገራቸው መመለስ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ከመሪዎቹ ግንኙነት በኋላ የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ በኬንያና በኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጋራ የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ለማድረግ ተባብረው እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ‹የሞያሌ የጋራ ከተማና የኢኮኖሚ ዞን› ፕሮጀክትን በጋራ ለማልማት ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች የጋራ የውትድርና ልምምድና በግብርና ዘርፍ ትብብር ለማድረግም በመሪዎቹ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢትዮጵያ በሞምባሳ ላሙ ወደብ ኢትዮጵያ የራሷ ልማት እንዲኖራትና መሬት በኬንያ መንግሥት እንዲሰጣት የሚያስችል ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፣ ከላሙ አንስቶ በሞያሌ ሐዋሳን አቋርጦ አዲስ አበባ የሚገባው የባቡር መስመር ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲፈጸም ሁለቱ አገሮች ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸው ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሞምባሳ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚያደርገው በረራ ወደ ሁለት እንዲያድግም የሁለቱ አገሮች መሪዎች ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች አየር መንገዶች ማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኬንያ አየር መንገድ፣ በኬንያና በኢትዮጵያ ያለገደብ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እንዲቻል ቅድመ ስምምነትም ተደርጓል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የተወያዩበት ሌላው ጉዳይ ደኅንነት ሲሆን፣ በተለይ አልሸባብ በሶማሊያ አሳሳቢነቱ አሁንም ከፍተኛ እንደሆነና ይኼንንም ለመግታት በጋራ ከአሚሶም ጋር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአሚሶም የሚያደርገው የተቀዛቀዘና ተገማች ያልሆነ ድጋፍ እንደሚያሳስባቸው፣ ይህም የአሚሶምን ሰላም የማስከበር አቅም ሊጎዳው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይኼንንም ችግር ለመቅረፍ ሁለቱ አገሮች ዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፋቸውን አበራተው እንዲቀጥሉ የመገፋፋት፣ ለሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች የሥልጠና ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
መሪዎቹ ይበልጡኑ ከሶማሊያውያን ይልቅ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉዋቸው የውጭ ኃይሎች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በእጅጉ እንደሚያሳስብ ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ተመሳሳይ የጋራ አቋሞችን ለማንፀባረቅ የተስማሙት ሁለቱ መሪዎች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ጠንካራ ለውጥ እንዲመጣ በጋራ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ኬንያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቀጣዩ ተተኪ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ እንደምትደግፍ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ ለሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ የሆነውን የጋራ ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ የመጀመርያው ስብሰባ እ.ኤ.አ. በ2016 በኬንያ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ቀጣዩ በኢትዮጵያ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ ይህም የልዩ ሥፍራ ስምምነት (Special Status Agreement) በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባም ያግዛል ተብሏል፡፡
ኬንያ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የ400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አፈጻጸምም ዋነኛ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኬንያ ቆይታቸው የኡሁሩ ኬንያታን የተማሪዎች ማሠልጠኛ ተቋም የጎበኙ ሲሆን፣ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው በዚህ ተቋም የሚሠለጥኑ ተማሪዎችን አበረታትተዋል፡፡
‹‹ምንም ብትሠሩ ምርጥ አድርጋችሁ ለመሥራት ታትሩ፡፡ ምንም ብትሆኑ ከዚያ ውስጥ ምርጥ የሆነውን ለመውሰድ ጣሩ፡፡ ፕሬዚዳንትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትርም፣ ኢንጂነርም ሆነ መምህር ብትሆኑ፣ ለምትሆኑት ነገር ምርጥ ሁኑ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሪዎችን መክረዋል፡፡
የወደፊት የአፍሪካ መሪዎችን ለማፍራትም እንዲህ ዓይነት ማዕከላት ለአፍሪካ ያስፈልጓታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዚዳንት ኬንያታ እየሠሩ ባሉት ነገር እንደኮሩና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ሊኮርጁት የሚገባ ተሞክሮ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ምንም እንኳን ኬንያና ኢትዮጵያ የልዩ ሥፍራ ስምምነት ቢኖራቸውም፣ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ግን የአፈጻጸሙ መዘግየት እንደሚያስቆጫቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹አጠቃላይ የስምምነቱ አፈጻጸም እጅግ ዘገምተኛና የታለሙለትን ግቦች ያልመታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለስምምነቱ ውጤታማ ትግበራ ግልጽ የጊዜ ሰሌዳና የሚጠበቁ ውጤቶችን በማስቀመጥ የታደሰ ግፊት እንድናደርግ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ፕሬዚዳንቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ይበልጡን እንዲጠናከር ስምምነቱ እንደሚጠቅም ቢያጎሉም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የዕቃና የሰዎች ዝውውር እንዲኖር የተከናወነው ሥራ ውጤት ማሳየት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም እንደማሳያ ፕሬዚዳንቱ በሞያሌ የተገነባው የአንድ መስኮት የድንበር ጣቢያ ግንባታ በኬንያ በኩል ሙሉ በሙሉ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 95 በመቶ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የሰዎችንና የዕቃ እንቅስቃሴን ይበልጡኑ ቀላል ለማድረግ ያለሙ ከሞምባሳ እስከ ሞያሌ ጠረፍ የተዘረጉ እንደ መንገድና የባቡር መስመር ያሉ መሠረተ ልማቶች ማሻሻያ ፕሮጀክት እንደተጠናቀቀ ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፡፡ ይህም እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቅ ይሆናል፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የጋራ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡ በተለይ የኦሞ ወንዝ፣ የቱርካና ሐይቅና የዱዋ ወንዝን ጉዳይ አንስተው እንደተወያዩ ተገልጿል፡፡
የኬንያ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ሰኞ ማምሻውን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ፕሬዚዳንት ኬንያታ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዘዋቸዋል፡፡ ኬንያታ ኢትዮጵያን መቼ እንደሚጎበኙ በዲፕሎማቲክ መስመር ውይይት ተደርጎበት እንደሚገለጽ ተነግሯል፡፡