የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች ከወራት በፊት ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔና የምርጫ ሥነ ሥርዓት መሠረት ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ተመርጠው ውጤታቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቢላክም፣ ሹመታቸው ሳይፀድቅ ከግማሽ ዓመት በላይ መዘግየቱ እያነጋገረ ነው፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ከሌሎች ባንክች በተለየ አኳኋን የንብ ባንክ የቦርድ አመራሮች ምርጫ እስካሁን በብሔራዊ ባንክ በኩል አለመፅደቁ ያልተለመደ ሆኗል፡፡ በሕጉ መሠረት የምርጫው ውጤት ለብሔራዊ ባንክ በተላከ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የተቀባይነት አሊያም የውጤት መሠረዝ ውሳኔ በገዥው ባንክ በኩል መላክ ነበረበት፡፡ ይህ ሳይሆን ለወራት የዘገየበት ምክንያት ግራ አጋብቷል እየተባለ ነው፡፡
በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. በተከናወነ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ውጤት ተገልጾ፣ በዚሁ መሠረትም ውጤቱን እንዲያፀድቅ የባንኩ አስመራጭ ኮሚቴ ለብሔራዊ ባንክ የላከው ምርጫው ከተደረገ 15 ቀናት ሳይሞላ እንደነበር ታውቋል፡፡ ሕጉም ይህ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ውጤት ሳይፀድቅ በመቆየቱ ሳቢያ፣ የሥራ ጊዜው የተጠናቀቀው ቦርድ ለአዲሱ ቦርድ ኃላፊነቱን ማስረከብ አልቻለም፡፡ እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ፣ ብሔራዊ ባንክ የንብ ባንክ ተመራጮችን ሹመት ሳያፀድቅ ለምን ያህን ያህል ጊዜ መቆየት እንዳስፈለገው ግልጽ አይደለም፡፡ የሹመት ይፀደቅልኝ ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በተለያዩ ጊዜያት ማብራሪያ በፈለገባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች እያቀረበ ንብ ባንክም ምላሽ እየሰጠ ቢቆይም፣ ሹመቱን መቀበሉን አሊያም ውድቅ ማድረጉን ማሳወቅ አልቻለም፡፡ ከሌሎች ባንኮች በተለየ አኳኋን የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሹመትን የተመለከተ ውሳኔ ከብሔራዊ ባንክ ባይሰጥም፣ በተመሳሳይ መንገድ ምርጫ ያካሄዱ ባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርድ ሹመት መፅደቁ ግን ‹‹ለምን የእኛ ብቻ?›› የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡
በብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ምርጫ ያፀደቀላቸው የሌሎች ባንኮች የቦርድ አባላት የባንኩን ይሁንታ ካገኙ በኋላ የቦርድ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመሰየም ሥራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የምርጫ ውጤታቸው ከፀደቀላቸው ባንኮች መካከል እናት ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ብርሃን ባንክና ዘመን ባንክ አዳዲስ የቦርድ ሊቀመንበር መርጠዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ የቀደመውን የቦርድ አባላት በድጋሚ የመረጠው አቢሲኒያ ባንክም እነዚህን ተመራጮች በብሔራዊ ባንክ ካፀደቀ በኋላ ነባሩ የቦርድ ሊቀመንበር በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የንብ ባንክ ኃላፊዎች ሹመት ይፅደቅልን ለሚለው ጥያቄያቸው ምላሹ ቢዘገየም፣ በቅርቡ መፍትሔ እናገኛለን የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡