Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የህዳሴውን ግድብ በሚያጠናው ድርጅት ላይ ተስማማች

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የህዳሴውን ግድብ በሚያጠናው ድርጅት ላይ ተስማማች

ቀን:

– የኔዘርላንዱ ኩባንያ አርቴሊያ በተባለ የፈረንሣይ ኩባንያ ተተክቷል

በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተመከሩ ሁለት ተፅዕኖ ጥናቶችን ለማካሄድ የተመረጡ ኩባንያዎችን አለመግባባት በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት የተጠራው የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ አርቴሊያ የተባለ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ኩባንያን በስምምነት በመተካት ተጠናቀቀ፡፡

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ የመረጣቸው ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለ የፈረንሣይ ኩባንያና ዴልታሬዝ የተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ ነበሩ፡፡ ቢአርኤል ሕጋዊ የጥናቱ ተዋዋይ ሆኖ የጥናቱን 30 በመቶ ሥራ ለዴልታሬዝ እንዲሰጥ፣ ነገር ግን የዴልታሬዝ የጥናት ውጤት ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ዋና የኮንትራቱ ባለቤት የሆነው ቢአርኤል ኢንጂነርስ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ዝርዝር መሪ ዕቅዱ በቢአርኤል በኩል በቀረበበት ወቅት የኔዘርላንዱ ኩባንያ መቃወሙ ይታወሳል፡፡

ዴልታሬዝ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መግለጫ መሪ ዕቅዱ ሙያዊ ነፃነቱን የሚገፋበት እንደሆነ በመግለጽ ራሱን ከጥናቱ ማግለሉን ገልጾ ነበር፡፡ ሦስቱ አገሮች መተማመንን ለመፍጠር የጀመሩት ውይይት በዚህ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ፣ ግብፅ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጠራ ከወር በፊት ጥያቄ አቅርባለች፡፡  በዚህ መሠረትም የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳዮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለተኛ ዙር ስብሰባ ለሁለት ቀናት በሱዳን ካርቱም ያደረጉት ውይይት ታኅሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በስምምነት ተጠናቋል፡፡

በስምምነቱ መሠረትም የጥናቱ ሁለተኛ አጥኚ ሆኖ በተመረጠውና ራሱን ባገለለው ዴልታሬዝ የተባለው የኔዘርላንድ ኩባንያ ምትክ፣ አርቴሊያ የተባለ ዋና መቀመጫውን በፈረንሣይ ያደረገ ኩባንያ እንዲተካ በስምምነት መወሰናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም አርቴሊያ ከዋናው የጥናቱ ኮንትራክተር ቢአርኤል ኢንጂነርስ ጋር በመሆን ጥናቱን በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ውስጥ በማካሄድ እንደሚያጠናቅቁ በመርህ ደረጃ ተስማምተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጥናቱ መጓተትና የግድቡ መፋጠን በግብፅ ላይ የፈጠረውን ሥጋት ለማስወገድ፣ የሦስቱ አገሮች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ የግንባታውን ሥፍራ ለመጎብኘት ተስማምቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት ውስጥ የዓባይ ወንዝን ወደ ቀድሞ የተፈጥሮ ፍሰቱ በመመለስ 50 በመቶ በደረሰው የግድብ አካል ውስጥ እንዲያልፍ አድርጋለች፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የግድቡን ውኃ መያዝ መጀመር የሚያስችላት በመሆኑ በግብፅ ላይ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ስትጠይቅ ሰንብታለች፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል መሆኑ እንደተገለጸ፣ ነገር ግን የግብፅ ሥጋትን ለማስወገድ የግድቡን የውኃ ሙሌት ለተወሰነ ጊዜ ለማዘግየት ኢትዮጵያ መስማማቷን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...