ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት በብራዚል በሚካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ በሚኒማ ከምትሳተፍባቸው ስፖርቶች በተጨማሪ በውኃ ዋና በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት ተወዳዳሪዎች የምትወከልበት ዕድል ማግኘቷ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዕድል ያገኘችው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ)፣ በዝቅተኛ የተሳትፎ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች በውኃ ዋና ያለሚኒማ ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተገኘ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ ተሳትፎን አስመልክቶ ከሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ በአራት የስፖርት ዓይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በወርልድ ቴኳንዶና በቦክስ እንደምትወከል፣ በተሳትፎዋም አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን መናገሩ ይታወሳል፡፡