የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ለዘጠነኛ ጊዜ እያከበረ የሚገኘውን የቱሪዝም ሳምንት ፌስቲቫል መታሰቢያነት ለልዑል ራስ መንገሻ ስዩም አደረገ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀውና ከታህሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እየተከበረ ያለው የቱሪዝም ፌስቲቫል፣ መታሰቢያነቱ ለልዑል ራስ መንገሻ የተደረገው፣ ራስ መንገሻ ለአገሪቱ ልማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም በኢትዮጵያ ልማት ዘርፍ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ልዑልነታቸው የሐዋሳ፣ የሽሬና የሸከት ከተሞች መሥራችና ቀያሽ ሲሆኑ፣ መቐለን በመከተም ባህር ዳርን ደግሞ የማስተር ፕላን ባለቤት በማድረግ ታላቅ ሚና የተጫወቱ የቱሪዝም ከተሞች አባት ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ትምህርት ክፍልም የ89 ዓመቱን ልዑል ራስ መንገሻ ጐንደር ድረስ ጋብዞ፣ በዋናው ካምፓስ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ዕውቅናውን ቸሯቸዋል፡፡
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለኤርፖርቶች መስፋፋትና ለቱሪዝም ድርጅት መቋቋም ላበረከቱት ታሪካዊ ሥራም፣ የዘንድሮውን ዓመታዊ ኩነት ለእሳቸው መታሰቢያ እንዲሆን ማድረጉን የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም ፌስቲቫሉ፣ ዓርብ ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የባህል ትዕይንቶች፣ የሆቴሎች ውድድር፣ የቱሪዝም ዐውደ ርዕይ፣ የፓናል ውይይትና የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች የተካተቱበት ነው፡፡ በዓሉ በጐንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በየዓመቱ የሚዘጋጅ ነው፡፡