Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት እሱ ለእሷ ዘመቻ ይፋ ሆነ

  የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት እሱ ለእሷ ዘመቻ ይፋ ሆነ

  ቀን:

  የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል ረገድ ዓለም ላይ ሁለት ቢሊዮን ሰዎችን አባል አድርጎ መንቀሳቀስን ያለመው የተመድ የሴቶች ድርጅት (UN women) እሱ ለእሷ ዘመቻ (HeForshe Movement) ሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በይፋ ተጀመረ፡፡ ላለፉት ረዥም ዓመታት ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል፤ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥም ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በብዛት በሴቶች የሚመሩ ነበሩ፡፡ ጉዳዩም የማኅበረሰብ ጉዳይ ሳይሆን የሴቶች ተደርጎ ስለሚታይ የወንዶች ተሳትፎ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም እንቅስቃሴው የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስገኝ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ስሙ እንደሚያመለክተውም እሱ ለእሷ ዘመቻ በዋነኝነት የወንዶች ሚና ላይ ያተኩራል፡፡

  ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጾታ እኩልነትን የማረጋገጥ ዘመቻ በተመረጡ አገሮች የሚደረግ ሲሆን በኢትዮጵያ ዘመቻው በካፒታል ሆቴል ይፋ በሆነበት መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቪዲዮ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ ረገድ የወንዶች ሚና ወሳኝ መሆኑን ሲገልጹ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና የሕፃናት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡመድና በኢትዮጵያ የተመድ የሴቶች ድርጅት ተወካይ ሊቲ ቺዋራም ይህንኑ ሐሳብ ደግመው አንፀባርቀዋል፡፡

  ይህ ዘመቻ ወንዶች ጾታዊ እኩልነትን በማረጋገጥ ረገድ የተቀናጀ መድረክ እንዲያኙ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን እንቅስቃሴው በመጀመሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋ የሆነው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን ነበር፡፡ እንቅስቃሴው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለት ቢሊዮን ወንዶችን ተሳትፊ ማድረግን ያለመ ነው፡፡

  እሱ ለእሷ እንቅስቃሴ ወንዶች የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ በኢንተርኔት፣ የሞባይል ቴክኖሎጂንና ሌሎችንም አማራጮች እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡ በኢንተርኔት የሴቶች ጉዳይ የመብት ጉዳይ መሆኑን ከማረጋገጥ የሚጀመረው ተሳትፎ ወደ ተግባርም እንዲሸጋገር ይጠየቃል፡፡

  የእንቅስቃሴው ይፋ መሆንን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ 597,614 ወንዶች እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉ ሲሆን ዘመቻው ይፋ በሆነበት ዕለት እንደተገለጸው በኢትዮጵያ የዘመቻው አባል የሆኑ ወንዶች ቁጥር 200 ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሐፊ መጋቤ ዘሪሁን ደጉና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...