Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የምዕራባውያንን ገና አስመልክቶ በብርሃኔ አደሬ ሕንጻ በሚገኘው የእንቁ ዲዛይን ሱቅ የተሰቀለው ከክሪስማርስ ቁሳቁሶች የተሰራ ቀሚስ

ትኩስ ፅሁፎች

ዓይኔን መጽውቱልኝ

ችግሩ ፍዳዬ – ደስታው ፌሽታዬ

ሆነን እንኖራለን – እንዘልቃለን ብዬ

ስቼረው ስቼረው …

በርኖሴን፣ ኩታዬን፣

ጋቢ፣ ቡሉኮዬን

ቁምጣ፣ መጫሚያዬን

          ስለግሰው ኖሬ

እጅ አጠረኝና – ስሄድ በባዶ እግሬ

            ብሶበት አየሁት፡፡

“በሉ ብሶብኛል፤ እኔም ርቃኔን ነኝ” – በሉና ንገሩት

እንደያ ተቸግሮ – ሲሄድ እንዳየሁት

                እኔንም እንዲያየኝ

               አይቶም እንዲያዝንልኝ

በዘመናት ችግር – በንባ ጎርፍ ሞጭሙጮ

ለታወረው ዓይኑ – ዓይኔን መጽውቱልኝ፡፡

በአካል ንጉሴ፣ ፍላሎት፣ 2006 ዓ.ም

******

በውሸት አትመረዝ

ለማዳን እሚዋሽ፣ ለመግደል ያድናል፡፡ ከቶም እማይገድልና ሌሎችም እንዲገድሉ እማይፈቅድ፣ የሁለንተናዊ ፍቅር ፍፁም አማኝ የሆነ ሞሂስት፣ አንድ የቆሰለ ተኩላን ዋሽቶ ከአዳኞቹ ይታደገዋል፡፡

ሁዋላ፣ በሞሂስቱ ውሸት ከሞት የዳነው ተኩላ፣ የጎረሱትን እጅ ነካሽ እንዲሉ፣ መልሶ ራሱኑ ሊበላው ተነሳና፣ ሞሂስቱ ራሱ ተኩላውን ይገድለዋል፡፡

ያ ምስኪን ሞሂስት አንድ ነፍስ አድን ብሎ ሁለት ነፍስ በእጁ አጠፋ፡፡ አንደኛው እውነቱን መግደሉ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ተኩላውን መግደሉ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ በእርግጥ የሚሆነው ይህ ነው፡፡ እርሱ፣ አድናለሁ ብሎ የሚዋሽ፣ ለመሞት ብቻ ይኖራል፡፡

እውነትህን መግደል፣ አካልህን ከመግደልም እጅግ የከፋ ጥፋት ነው፡፡ እውነተኛነት የመልካም ምግባሮች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ይህ፣ ጥንታዊው ውበትና ብቸኛው መንገድ ነው፡፡

አትዋሽ፡፡ ለማዳንም ሆነ ለመግደል፤ አትዋሽ፡፡ እውነተኛነትን ብርሃንህና መርሄ-ጉዞህ አድርጋት፤ መንገድህ ከምንም ዓይነት ጨለማም ሆነ ዱር ሊያደርስህ ቢችልም እንኳ፡፡ አልያ፣ እምትራመድበት ጎዳና በእግርህ ስር ሲርድና ሲሰነጣጠቅ ታገኛለህ-ሊውጥህ፡፡ መንገድህ መልሶ አንተኑ ሊበላ!

እነዚያ በእውነት የሚያምኑ፣ ከውሸታቸው ይልቅ እውነታቸው ይሰዋቸው ዘንድ ይመርጣሉ፡፡ (እኚህ፣ እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር፣ እንደሚሉ ቀጥተኞች ናቸው፡፡ የለም፣ ዋሽቶ ማስታረቅን እንደሚተርቱ የዋሃን አይደሉም፡፡)

አታም ፑልዩ፣ የፈላሱ መንገድ፣ 2006 ዓ.ም.

******

አንድ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሕንፃ ሊገነባ ነው

የዱባዩ ታዋቂው ቡርጅ ካሊፋ ሕንጻ በዓለም በርዝመቱ ከቀዳሚዎቹ የሚመደብና በጊነስም የሰፈረ ነው፡፡ ሰሞኑን ሲኤንኤን ይዞት የወጣው ዜና ግን የዱባዩ ቡርጅ ካሊፋ፣ ሳዑዲ አረቢያ ልትገነባ ባሰበችውና አንድ ኪሎ ሜትር በሚረዝመው ሕንጻ ሊተካ ነው፡፡

በዓለም በርዝመቱ የመጀመሪያ ሕንጻ ይሆናል የተባለው ሕንጻ በ2020 የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ከቡርጅ ካሊፋ ሕንጻም የ173 ሜትር ርዝመት ልዩነት ይኖረዋል፡፡

የሳዑዲ መንግሥት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የጂዳ ኢኮኖሚክ ኩባንያ እና የሳዑዲ ዓረቢያ አሊንማ ኢንቨስትመንት አንድ ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ጨምሮ የጅዳ ከተማን በሪል ስቴቶች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ለነዋሪና ለቱሪስት ምቹ ከተማ ለማድረግ የ2.2 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡  

******

አንድ ዜማን 24 ጊዜ ያጫወተው ጋዜጠኛ ተቀጣ

የኦስትሪያ ሬዲዮ ጣቢያ በተከታታይ አንድ የገና ዘፈንን 24 ጊዜ የለቀቀ ጋዜጠኛ መቀጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በጋዜጠኛው እንዲህ ይለቀቅ የነበረው “ላስት ክሪስማስ” የተሰኘው የእንግሊዙ ዋም ባንድ ዜማ አድማጮችን በጣም አሰልችቶ ነበር፡፡ በስልክ ደውለው መሰልቸታቸውን ከገለፁና ዘፈኑ እንዲቋረጥ ከለመኑ መካከል የጋዜጠኛው ሴት ልጅ አንዷ ነበረች፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው የፕሮግራም ኃላፊ ኢንቴኒ ኤሬንቲን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ጋዜጠኛው ይህን ያደረገው የፕሮግራሙን አድማጮች ፕራንክ ለማድረግ ሲሆን ማንም ወደ ስቱዲዮ እንዳይገባ አድርጎም ነበር፡፡ ነገሩ በተወሰነ መልኩ ዘና የሚያደርግ ቢሆንም ጋዜጠኛው ይቀጣል ያሉት የፕሮግራሙ ኃላፊ የገናን ዕለት እንዲሁም የአዲስ ዓመት ዋዜማን እንዲሠራ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

******

በኮንዶም ማሽን ሕይወቱ ያለፈው ሰው

በፈረንጆች ገና ዕለት ጀርመን በርሊን ውስጥ ተገንጥሎ በበረረ የኮንዶም ማሽን ክፍል የተመታ አንድ ሰው ሕይወቱ ማለፉ ተዘገበ፡፡ ፖሊስ እንዳስታወቀው ከኮንዶም ማሽኑ ስርቆት ለመፈጸም ሲሞክሩ ከሦስቱ ጓደኛሞች አንደኛው ሊሞት ችሏል፡፡ ጉዳት የደረሰበት የ29 ዓመት ጓደኛቸውን ወዲያው ወደ ሆስፒታል ቢወስዱም ሁለቱ ጓደኞቹ ግን ከገነጣጠሉት ማሽን ወጥቶ የተበታተነውን ኮንዶምና ገንዘብ ጥለው መሄድን መርጠዋል፡፡ ሆስፒታል ወስደው ጓደኛቸውን ከደረጃ ላይ መውደቁን ቢገልፁም ሐኪሞች ነገሩን በመጠራጠራቸው ለፖሊስ ተደውሎ በመጨረሻ የኮንዶም ማሽን ላይ ስርቆት መፈፀማቸው ሊታወቅ ችሏል፡፡ የማሽኑን ክፍል እንዲበር ያደረገው ማሽኑ ላይ የደረሰ መጠነኛ ፍንዳታ መሆኑም ታውቋል፡፡

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች