Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የምርምር ውጤቶች አለመነገር ተመራማሪዎችን የጋን ውስጥ መብራት ያደርጋቸዋል›› አቶ ጨመዳ ፈይሳ፣ የሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1954 በአሜሪካውያን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው መጀመርያ ጅማ ላይ ሜካኒካል አርት በሚል ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፣ በኋላም ወደ ሐሮማያ ተዘዋውሯል፡፡ ሲመሠረት የነበሩት ዲፓርትመንቶች እፅዋት ሳይንስ፣ የእንስሳት ሳይንስ፣ ግብርና ሳይንስ እንዲሁም ኢኮኖሚክስ ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ዩኒቨርሲቲው ዲፓርትመንቶቹንም አስፋፍቷል፣ የቅበላ አቅሙንም አሳድጓል፡፡ አቶ ጨመዳ ፈይሳ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዘርፍ ምን ያህል ተስፋፍቷል?

አቶ ጨመዳ፡- ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እየሰጠ ያለው በመደበኛ፣ በክረምትና በማታ ሲሆን 11 ኮሌጆችንም ከፍቷል፡፡ ዲፓርትመንቶች ተስፋፍተዋል፡፡ ለምሳሌ በግብርና አካባቢ ሳይንስ ዲፓርትመንት ውስጥ፤ የእንስሳት ሳይንስ፣ ዕፅዋት ሣይንስ አካባቢ ሣይንስ፣ የተፈጥሮ ሣይንስ እንዲሁም ኢኮኖሚክስና ሌሎችም አሉ፡፡ በ11 ኮሌጆች ውስጥም ከአምስት እስከ ስድስት በሚሆኑ የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ትምህርት ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚሠራው በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ምን እየሠራ ይገኛል? ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረትስ ምን ይመስላል?

አቶ ጨመዳ፡- የትምህርት ጥራት ትኩረት የምንሰጠው ሥራ ነው፡፡ ለዚህም የምንሰጠውን የንድፈ ሐሳብ ትምህርት በተግባር በማስደገፍ እየሠራን ነው፡፡ የምንሰጠው ትምህርት ራሱ የቴክኖሎጂ፣ የጤና፣ የግብርና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ዓይነቶች ስለሆኑ፣ ከክፍል በተጨማሪ የተግባር ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ይህንን ለመተግበር ያሉንን ቤተ ሙከራዎችና ወርክሾፖች እየተጠቀምን ነው፡፡ ተማሪዎችን የተለያዩ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የልማት ድርጅቶችን የሚጎበኙበት ፕሮግራምም አለን፡፡ እዚህ አካባቢ የሌለንን ሌላ ቦታ በመውሰድ ንድፈ ሐሳብን በተግባር እንዲለማመዱ እናደርጋለን፡፡ የመጀመርያው ሥራ ይኼ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የትምህርት ጊዜ ብክነትን መቀነስ ነው፡፡ አንድ ትምህርት ተጀምሮ እስከሚጨረስ አንድ ደቂቃ እንዳይባክን ክትትል በማድረግ ተማሪዎችም የመጡበትን ዓላማ በትክክል እንዲጠቀሙበት እየሠራን ነው፡፡ ሦስተኛውና የትምህርት ጥራትን የምናስጠብቅበት መንገድ ተከታታይ የምዘና ፈተና በመስጠት ነው፡፡ ኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማደራጀት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራን ነው፡፡ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን በተመለከተ ለምሳሌ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በዓመት በዓመት እየቀነሰ መጥቶ በአሁኑ ደረጃ ሁለት በመቶ ሆኗል፡፡ ቁጥሩን ለመቀነስ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገናል፡፡ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ትምህርት እንሰጣለን፡፡ ውጤት አሰጣጡ ስለተቀየረም አንዱ ከፍ ያለ ውጤት ቢያመጣም ሌላው ተማሪ ስለማይጎዳ ተማሪዎች ተደጋግፈው እንዲያልፉና አብረው እንዲያጠኑ ዕድል ከፍቷል፡፡ በዘንድሮው ዓመት 36 ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው የአንድ ሰው ዕድሜ ያህል አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ዕድሜው ካፈራቸው ሰዎች በአገሪቱ ታዋቂ የሆኑትንና ችግር ፊቺ የሆኑ ምርምሮችን ቢገልጹልን?

አቶ ጨመዳ፡- ዩኒቨርሲቲው በርካታ ከአገራችን አልፎ ለዓለም ጠቃሚ የሆኑ አንቱ የተባሉ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ በአገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ በመምራት ላይ ከሚገኙት አቶ ተፈራ ደርበው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር እንደዚሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን እየመሩ ያሉት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የወጡ ሲሆኑ፣ በፌዴራልና በክልል ከተሞች የሚገኙ የግብርና ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች የሐሮማያ ምሩቃን ናቸው፡፡ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ምርምር ቀዳሚ ነው፡፡ በአገራችን አሁን ለሚታየው የግብርና ዕድገት ዩኒቨርሲቲው ጉልዕ ሚና አለው እንላለን፡፡ በትምህርት ቤታችን ሁሌም ምርምር እናደርጋለን፡፡ ካካሄድናቸው ምርምሮችም ውስጥ ጉልዕ ሚና አለው የምንለው በድንች ላይ የተሠራው ነው፡፡ ድንች በመላው አገሪቱ እንዲስፋፋ ያደረግነው እኛ ነን፡፡ ሐረርም በድንች ምርት ትታወቃለች፡፡ ወደ ጂቡቲም በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ እኛ ያለንበት ወረዳ ሐሮማያ፣ ኮምቦልቻና ቀርሳ ወረዳዎች በድንች ምርታቸው የታወቁ ሆነዋል፡፡ የተሻሻሉ የቦሎቄ ዝርያዎችን በማፍራትና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በማስረፅ ለምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ ያለው ምርምር አድርጓል፡፡ በአትክልት ላይ ያደረገው ምርምርም ይጠቀሳል፡፡ የሽንኩርትና ካሮት ዝርያዎች በቴክኖሎጂ እንዲሻሻሉ አድርገናል፡፡ ስለማዳበሪያ፣ የአፈር ጥናት፣ ምርት አሰባሰብ የውኃ እቀባ ላይ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን በማቋቋም ለምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላችሁ ይነገራል፡፡ የተቋቋሙትን ዩኒቨርሲቲዎችና የወደፊት ዕቅድ ቢገልጹልን?

አቶ ጨመዳ፡- በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ለተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለበት፡፡ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲን በማቋቋም እንደዚሁም ሐሮማያ፣ ድሬዳዋ ላይ የነበሩትን የሕግና የቴክኖሎጂ ኮሌጆች አሳልፎ በመስጠትና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በማገዝ መሠረት ጥሏል፡፡ ጭሮ ላይ ካምፓስ ያለን ሲሆን፣ የአግሮ ኢንዱስትሪና የመሬት ሀብት ኮሌጅ ነው የሚባለው፡፡ ይህ ኮሌጅ ወደ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከመምጣቱ በፊት የኦሮሚያ ቲቪቲ ኮሌጅ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተረከበው በኋላ ሰፊ ማስፋፊያ በማድረግና ብዙ ፕሮግራሞችን በመክፈት በአሁኑ ሰዓት በመንግሥት ውሳኔ ሰጭነት ኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ በሚል አሳድጎታል፡፡ ኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በምሥራቁ ኢትዮጵያ ለተገነቡት ዩኒቨርሲቲዎች መሠረቱ ሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ አካባቢውን ወይም ኅብረተሰቡን በምርምሬ ቀይሬያለሁ ብሎ ያምናል?

አቶ ጨመዳ፡- ኅብረተሰቡ የሚቀየረው በአንድ ተቋም ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኅብረተሰቡን ሊቀይረው የሚችለው የብዙ ተቋሞች አስተዋጽኦ ነው፡፡ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ለአካባቢው ኅብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጥም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በትምህርት ረገድ ከመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ዕርዳታና ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በጤና ረገድ ደግሞ ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለውና ተደራሽ እንዲሆን የቁሳቁስና ቴክኒካዊ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ለመስተዳድሮችና ለጤና ጣቢያዎችም የምርምር ውጤቶችን በመስጠት አብረን እንሠራለን፡፡ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል፡፡ ጠበቃ በመቅጠርና ለሴትና ለሕፃናት እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች ከክስ መፃፍ እስከ ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከር ድረስ እናግዛለን፡፡ ኅብረተሰቡ የሚጠይቃቸው በተለይ በመሠረተ ልማት በኩል ያሉ የመንገድ፣ የውኃ ችግሮች እንዲፈቱ አቅማችን በፈቀደ እናግዛለን፡፡ በአጠቃላይ ከኅብረተሰቡ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በምትሰጡት አገልግሎት የኅብረተሰቡ ምላሽ ምን ይመስላል?

አቶ ጨመዳ፡- ኅብረተሰቡ ብዙ ጥያቄዎችን ነው የሚያቀርበው፡፡ በተቻለን መጠን ያለንን ሀብት አብረን እንካፈላለን፡፡ በ2007 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን አገልግሎት በሚመለከት ጥናት አድርገን ነበር፡፡ በዚህም ውጤት መሠረት 71 በመቶው ኅብረተሰብ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው አገልግሎት እርካታ እንዳለው ገልጿል፡፡ ይህ በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡ በቀጣይም እየተወያየን የበለጠ ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የመምህራን ፍልሰት በተለይ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንንም ክፍተት ለመሙላት መንግሥት በከፍተኛ ወጪ የውጭ መምህራንን እየቀጠረ ነው፡፡ የእናንተ ዩኒቨርሲቲ ይህን ፍልሰት ለመግታትና አሁን ያለው የኑሮ ውድነት መምህራን ላይ ያደረሰውን ጫና ለመቅረፍ ምን አይሠራ ነው?

አቶ ጨመዳ፡- ይህ እንዳልከው አገራዊ ችግር ነው፡፡ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን እዚህ ግቢ ውስጥ ለሚያስተምሩ መምህራን የመኖሪያ ቤት እናቀርባለን፡፡ ይህንን ላላገኙ ደግሞ ተጨማሪ ኮንዶሚኒየም ለመግዛት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ተጨማሪ ሕንፃዎችን በመሥራት መምህራን ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ መንገድ እየቀየስን እንገናኛለን፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከከተማው የራቀ እንደመሆኑ ከሰባት እስከ ስምንት የሚደርሱ ሰርቪሶችን በመመደብ፣ በግቢው ውስጥ የቁርስና የምሣ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በግቢው ውስጥ ቅናሽ መደብሮችን በማዘጋጀት አገልግሎቱን ከከተማ በግማሽ ባነሰ ዋጋ እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ሌላው የአስተማሪውን ፍልሰት ለመግታት የሚያስችል ዕቅድ ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ አቅርበናል፡፡ ዕቅዱ ሲፀድቅ ችግሮች የሚፈቱ ይሆናል፡፡ ይሄ እንግዲህ በተቋሙ የሚሠራ ማትጊያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለባችሁ ችግር ምንድን ነው?

አቶ ጨመዳ፡- ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ ችግር አለ፡፡ ይህ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ ግቢው ውስጥ ከ40 ሺሕ በላይ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ ምግብ የሚዘጋጀው በኤሌክትሪክ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠፋ ምን እንደሚፈጠር ማሰብ ነው፡፡ የንፁሕ ውኃ መጠጥ አቅርቦት መጓደል ሌላው ችግር ነው፡፡ እኛ ያለነው ገጠር ስለሆነ ውኃ በራሳችን ነው ከጉድጓድ የምናወጣው፡፡ ይህ ደግሞ ለአካባቢውም ኅብረተሰብ ጥቅም ይሰጣል፡፡ አሁን አሁን ግን አካባቢው እየሰፋና የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ስለመጣ ውኃው እየቀነሰ በመሄዱ ከፍተኛ የውኃ እጥረት እየተፈታተነን ነው፡፡ ሦስተኛ የሚፈታተን የመምህራን ፍልሰት ነው፡፡ በተለይ በቴክኖሎጂ ኮሌጅ ውስጥ ችግሩ አለ፡፡ ለቴክኖሎጂ ኮሌጁ መምህራን ለማግኘት ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ሪፖርተር፡- ራዕያችሁ ምንድን ነው?

አቶ ጨመዳ፡- ራዕያችንም እ.ኤ.አ. በ2025 አፍሪካ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ላቅ ብሎ መገኘትና በዓለምም ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ መሆን ነው፡፡ ራዕያችንን ለማሳካት የአምስት ዓመት ዕቅድ አስቀምጠን በዩኒቨርሲቲው ቦርድ አፅድቀን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ አድርገናል፡፡ ይህም ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር የተጣጣመ ሲሆን ወደ ራዕያችንም ለመጓዝ በመማር ማስተማር፣ በምርምሩ፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ልቆ በመሥራት፣ ከሁሉም በላይ የድኅረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በመትጋት ላይ ነን፡፡ ይህን ለማድረግ ከ900 አልጋ በላይ ያለው ሆስፒታል መገንባትን ጨምሮ ግዙፍ ግንባታዎችን በሁሉም ዘርፎች እያካሄድን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቢቀረፍ የሚሉት ችግር ምንድነው?

አቶ ጨመዳ፡- ችግር ፈቺ ጥናቶችን ያበረከቱ ግለሰቦችና ሥራዎቻቸው ሲነገር አይስተዋልም፡፡ ይህ ደግሞ ተመራማሪዎች የጋን ውስጥ መብራት ሆነው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል፡፡ የሠሩትም ሥራ ዋጋ እንዲያጣ፣ የምርምራቸው ውጤት ጥቅም ላይ በአግባቡና በትክክል ሳይውል ሜዳ ላይ እንዲቀር እያደረገ ነው፡፡ ይህ መቀየር አለበት እላለሁ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች