እነሆ መንገድ! ከሜክሲኮ ወደ አብነት ልንጓዝ ነው። ሆድ ምሱን ፍለጋ፣ ተጓዥ እግሩን እያማታ፣ ነግነቶ ባልነጋ ሰማይ ሥር እንርመሰመሳለን። ይኼም ጎዳና እንደቀደሙት ታሪክ አለው። ትርክት አለው። ምሳሌ፣ ኑሮና ተረት ተሰባጥረው ህያው መልካችንን ለዛ ይሰጡታል። “ፍየሉን ትተን ቅዝምዝሙን እንመታለን፤” እያለ ያለው ማን ነበር ሰሞኑን? አዎ! ከሰሞነኛ ትርክቶች አንሸሽም። ዕይታችን ሚዛን አልደፋ፣ አረጋገጣችን በድፍረት የተሞላ ዒላማ ቢስ መስሏል። “ግን? . . .፤” ይላል ተሳፋሪው “. . . ይኼ ሁሉ ዩኒቨርሲቲ፣ መረጃ፣ ተናጋሪና ተንታኝ ባልታጣበት ጎዳና እንዴት የቆሻሻ ገንዳችን ክምር አድማሱን ከለለን?” ብሎ ይጠይቃል። መልስ “የቆሻሻ ክምር መብዛት የአንድን አገር ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገትና የሥልጣኔ ይዞታ ይጠቁማል፤” ይሉናል። ‘እናምናለን’ ብሏል ገጣሚው። አምነንም ከቆሻሻ ገንዳዎቻችን በህልውናችን ካርታ ላይ የመገኛችን አቅጣጫ መጠቋቆሚያ አድርገናቸው እንኖራለን።
እናስ? ተውሳክ አላስቀምጥ ሲለን፣ ድፍን ዓመት ጉንፋን እንደ ውስጥ ልብስ ቢቀያይረን ጤና ማጣትን ለልማት የሚከፈል መስዕዋትነት አድርገን ቆጥረን እንጓዛለን። የቀን ዕርምጃችን በፀሐይ እሳት ተለብልቦ ሲያርብን አመሻሽ ላይ ከሻማ ብርሃን በማይሻሉ የመንገድ መብራቶች ምሪት በሠልፍ ወደ ዝለት እንቻኮላለን። ደግሞ ሊነጋ፣ ደግሞ የትናንቱን ዛሬ እንደ አዲስ ልንደግመው እንቅልፍ የጠገብን መስለን፣ ሐሳብ የሌለብን መስለን፣ ጫንቃ ሰፊ መስለን ማልደን እየተነሳን ጎዳናውን እናውካለን። የመኪና ጭስ ስንምግ፣ የመንገድ ቱቦ ሽታ ስናነፈንፍ፣ ያም አልበቃን ብሎ ተሳፍረን በምንወርድበት ታክሲ ሁሉ ሽሙጥና አሽሙር ስናከር እንውላለን። የሆነው ሁሉ ሆኖ ቀርቶ ጭው ያለው ህዋም የታሪክ ባለቤት ነው። የቀረው ቀርቶብን ቢደላም ባይደላም ቢያንስ ስለታሪክ፣ ስለትውስታ ስንል መጫን መራገፍ አላቆምንም። ነገም ዛሬም ወደፊት!
“የፈረስ ስምህ ማን ነው?” ይላሉ በጠራራ ፀሐይ፣ ከፀሐይም ኑሮ እንደ እኛ ያንገሸገሻት የምትመስል ጋቢያቸውን ክንብንብ ብለው ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት። “ምን አሉኝ አባት?” ሬዲዮኑን እየቀነሰ ሾፌሩ ወደ አዛውንቱ ይዞራል። “ወቸው ጉድ! ሲሆን ታክሲህን ዙሪያዋን በለጠፍከው። ወንበሩን መሪውን በስያሜህ ባሸበረቅከው ነበር፤” ብለው እግራቸው ሥር ያጋደሙዋትን ሽመል አንስተው ይደገፋሉ። “ምኑን ነው የሚሉኝ?” ሾፌሩ እንቆቅልሽ ሆኖበታል ወሬያቸው። “የፈረስ ስምህን ነዋ! ይኼን የመሰለ ክንፈ ሥውር ንስር ስታበር መለያ፣ መታፈሪያ፣ መከበሪያ የልጓም ስም የለህም? እንደ አባዳኘው እንደ መቻል፤” ሲሉት ፈገግ አለ። ቀልድ አርጎታል። አዛውንቱ ቀጠሉ።
“ለነገሩ የዛሬ ዘመን ሰው ግብሩና ስሙ አይገጥም። ይሰጣችሁስ ቢባል በየትኛው ብቁነታችሁና ሙያዊ ችሎታችሁ ነው የፈረስ ስም የምንሰጣችሁ? ሾፌር ተብዬው መንጃ ፈቃድ የለው፣ ቢኖረውም ጥቂቱ ነው በብቃቱና በችሎታው ያገኘው። ቀበሌ ብንሄድ ያው ነው። ኮምፒዩተር ነው የምትሉት? እ . . . እሱ ፊት ተቀምጦ በቀደም . . . አለባበሱ ብቻ ነው ከኮምፒዩተሩ ጋር የሚስማማው ስልህ? ይኼው ልማልልህ ዛሬ የዓመቱ ገብሬል ነው . . . ሙት ሙት! . . . ‘ስም ማን ልበል?’ አለኝ። ነገርኩት። ስሜን እዚያ ኮምፒዩተር ላይ ለመጻፍ በአማካይ ለአንድ ፊደል አንድ አንድ ደቂቃ ፈጀበት። ጉድ እኮ ነው. . .” ብለው ሲያበቁ ፋታ ወሰዱ። አጠገባቸው የተቀመጠች አንዷ፣ “ይኼው ሆኗል ዘመኑ። ዕውቀትና አዋቂ ወደ ደጅ ከተባለ ቆይቷል። የገዛ ቆሻሻችን ሳናራግፍ ባላዋቂ ሳሚ . . . ስንለቀለቅ እንውላለን፤” ብትላቸው ሳብ አድርገው ግንባሩዋን ሳሙዋት። በተግባር የልባችን አልደርስ ቢል በአፍ የልባችንን ከደረሰልንማ ስንሳሳም ብንውል ይገርማል እንዴ?
“እስከመቼ በስም አልባ ፈረሰኞች በብቃት የለሽ ጋላቢዎች እንደምንታሽ ብቻ . . .” ብሎ ከአዛውንቱ ጀርባ የተቀመጠ ጎልማሳ በእንጥልጥል ተወው። ጉዟችን ተጀምሯል። ወያላው “ሒሳብ!” እያለ ያዋክበናል። “እስኪ ወሬ አታቋርጥ፣ ቀስ በል የት ይሄድብሃል?” አዛውንቱ ወያላውን በዓይናቸው ገረፉት። ወያላው ሲረጋጋ “ይኼውልህ፣ አባ መቻል፣ አባ ይርጋ፣ አባ ዳኘው በአስተዳደርና በዳኝነት ችሎታቸው ሕዝቡ ላወቃቸው ጎበዛዝት የሰጣቸው የፈረስ ስም ነበር። አዳምጥ። ከነበር ብዙ ቁም ነገር አለ። ሕዝብ ያላመነበትን ችሎታህን አያሞካሽም። ምን ፍፁም ብትሆን ለሕዝብ እንከን እንጂ መልካም ሥራ አይደምቅም።
እንዳሁኑ ልብ የጠፋበት ዘመን ከሆነ ማለቴ ነው። ደግሞ መጽሐፉም የሚለው ይኼንኑ ነው። ‘ከብዙ ባለፀግነት መልካም ስም ይበልጣል’ ብሎ ይኼው እኮ ይኼ ብላቴና (ወደ ወያላው እየጠቆሙ) ለጥፎልናል። እውነቴን ነው!” አዛውንቱ አንዴ ከተለኮሱ ቶሎ አይበርዱም። “የነበሩስ በነበር ይቀመጥ። ዛሬስ?” አላቸው ከጎልማሳው ጎን የተቀመጠ አጭር አፍንጫ ደፍጣጣ ወጣት። አዛውንቱ ጋቢያቸውን ነጠል እጥፍ እያደረጉ፣ “ዛሬስ ይለኛል እንዴ ሊያስደፈጥጠኝ?” ሲሉ ተሳፋሪውን አስፈገጉት። “አሁን አንተ እነ አባ ብላውን፣ እነ አባ ሞጭልፈውን፣ እነ አባ ተቀራመተውንና እነ አባ . . . ማነው . . . ጆሮ ዳባ ልበስን አሰኝተሃቸው ነው በአሁንና በነበር መሀል ብርድ የምታስመታኝ?” አሉት። ያው ወጣት እየሳቀ፣ “እንዴ በዚህ በፀሐይ ሃጫ በመሰለ ጋቢ ተጀቡነው የምን ብርድ ነው?” ቢላቸው፣ “ሆሆ! አይታወቅም ልጄ። ዘንድሮ ሰው ያለቀው ከፊል ደመናማ ትንቢት እያመነ ከፊሉን ሳይመረምር የወጣ ነው። በትናንትና በዛሬ መሀል ደግሞ ከባድ የአየር ግጭት አለ። ካላመንክ ድራፍት በሚባለው ብርድ የጨረሳቸውን ቁጠር፤” ብለውት አላስቻለቸውም ራሳቸው ከት ከት ብለው ሳቁ። ‘ብሶት ባይብስ ኖሮ ሰው ራሱን ኮርኩሮ መሳቅ ባልጀመረ’ ነበረ የሚል ጥቅስ ይታየናል!
ወያላችን ሒሳቡን እየተቀበለ ነው። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ወጣቶች ማንቸስተር ዩናይትድ ሞሪንሆን ሊያስፈርም ነው በተባለው ወሬ የተሰማቸውን ስሜት ያወጋሉ። “በቃ የምወደውን የማንቸስተርን ፉትቦል ልጠላው ነው፤” ይላል አንደኛው። “መጀመርያ ራስህን ውደድ ወንድሜ። ከዚያ ወዲያ ምን ጠላህ ምን ወደድክ ለውጥ አያመጣም፤” ይለዋል ወዳጁ። “አንተ ደግሞ አሁን ‘ፉትቦል’ መሀል ምን ትፈላሰፍብናለህ? አንተ ጨረቃ በመሰለች እንቁ ልጅ ‘ስፖንሰርነት’ የቤት ኪራይህ ይሸፈንልሃልና እኛን የደላን መሰለህ? ሰው ሳይደላውና ሳይኖረው እንዴት ነው ራሱን የሚወደው?” ይመልሳል አፍጥጦ። “ነገርኩህ! ቢያንስ ስንቀብርህ በኳስ ፍቅር አብዶ ሞተ ከምንል፣ በራሱ ፍቅር ተነክቶ አረፈ ብለን ማዘን እንፈልጋለን። ሞት ካልቀረልን ለቋሚ እናስብ እንጂ። እንዴ! ኑሮውን ተወውና ቢያንስ አሟሟትህን አሳምረው ምን ነክቶሃል?” ወዳጁ እያላገጠ ነው።
“ተውኝ ባክህ። ይኼው መቶ ብር ስንት ዓመት ከትውልድ ትውልድ አዕዋፍት ቀዝፈውት የማያውቀቱን አየር እየቀዘፈ ሳናየው ከመቅዝበት ብን ብሎ ብን እያደረገን፣ አሟሟታችንስ እንዴት ይመር? አይደል እንዴ?” አጠገቡ ወደተቀመጡት ተሳፋሪዎች ዓይኑን ወረወረ። “አሟሟትን ለማሳመርም እኮ ገንዘቡን ተውትና ጥሩ ጸሎት ያስፈልጋል። ከራሳችን ጋር በቅጡ ማውራት የተውን ሰዎች እንዴት ብለንስ ከፈጣሪ እንግባባ?” ሲል ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ለግላጋ ኩሩ ሴት፣ “አሁን እውነት የተናገርክ ይመስለኛል። ፈጣሪም የቸገረው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ምን እንደምንለውም ለማወቅ እንጃ የቸገረው ይመስለኛል፤” አለችው። ይኼኔ ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “የባቢሎን ዘመን ተደገመ ብላችሁ ባልሆነ። ምንድነው ይኼን ያህል ፈጣሪን ማደንቆር?” ብሎ ደህና ጨዋታ የጀመሩትን ተሳፋሪዎች ንስሐ ማስገባት ሲጀምር ፀጥታ ሰፈነ። ንስሐ ባይኖር በቃ ፅሞና ታሪክ ሆኖ ሊቀር ነበር ማለት ነው ጎበዝ? በጫጫታ ተደነቋቆርን እኮ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “የሩሲያ ፀረ አይኤስ ጥቃት በሳተላይት መታገዝ ጀመረ’ የሚሉን ነገር አልገባኝም፤” ይላል ጋቢና የተቀመጠው ወደ ፍቅር አጋሩ ዞሮ። “እኛ ምን አገባን? ይልቅ ያ ጓደኛህ ሠርጉ ደርሷል። ሙሉ ልብስ መግዛት አለብህ፤” አለችው። “በምኔ ነው የምገዛው? ሳተላይት የለኝ! ማን ያጋዛኛል?” ይላል። “እንዴ? ጦርነት ሆነ እንዴ?” አለ ሾፌሩ አላስችለው ብሎ። ‘’ነውና። በጨበጣ ከመኖር የበለጠ ጦርነት አለ? የጦር መሣሪያ ባንታጠቅም እኮ አወዳደቃችንና አነሳሳችን የወታደር ከሆነ ሰነበተ፤” አለው በባዶ ኪስ ድግስ እንዲያደምቅ በክብር የተጠራው ተሳፋሪ። “ወይ ጣጣ! እኔ ምለው ግን መቼም ሳተላይት ማምጠቅ ከባድ ወጪ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ የሚደረግበት ነገር ነው አይደል?” ሁሉም በመስማማት አንገቱን ወዘወዘላቸው ለአዛውንቱ። “ታዲያ ምን አለበት አንዳንዴ ብቻ ለብቻ ለሺሕ አስጨናቂ የኑሮ ጥያቄ የተፋጠጥነውንም ቢያግዙን?” አሉ። አጠያየቃቸው ከልባቸው እንደሆነ ያሳብቃል።
“እኛ ሳተላይት አላመጠቅንማ!” መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ባለቢጫ ቦርሳ መለሰች። “እኛ ያመጠቅነው ሙሰኛ፣ ሥልጣንን መከታ አድርጎ ፍትሕ የሚያዛባ፣ የደካሞችን ጉሮሮ እየዘጋ በልማት ስም ብሎኬት ደርድሮ ሕንፃውን በስሙ የሚያስጠራ ነው ያመጠቅነው። ምናልባት ወደፊት . . .” ብላ ሳትጨርስ፣ “ኧረ የረሳሻቸው አሉ። የፌስቡክ አካውንት አለኝ ብሎ ያለማመዛዘንና ያለዕውቀት ያሻውን የሚለጥፍ፣ በየካፌና በየባሩ ቀንና ሌሊቱን በከንቱ የሚገብር፣ የማኪያቶ ሒሳብ 15 ብር ሆነ እያለ መንግሥት የሚያማርር፣ ብዙ ባለዲግሪ ሥራ ፈላጊ የቤተሰብ ሸክም፣ ወዘተረፈ፤. . .” ብሎ ጎልማሳው ቀጠለላት። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍትል አዛውንቱ “ከነበር ካልተማርን ገና ብዙ አልባሌና የዕድገት ማነቆ የሆኑ እኩይ ተግባሮች እናመጥቃለን፤” እያሉ ወረዱ። ሰሚ ሲኖር አይደል? ሁሉ ተናጋሪ፣ ሁሉ ፈራጅ፣ ሁሉ ቆራጭ፣ ሁሉም እኔ ብቻ ልክ በሚልበት መድረክ ማን ይሆን ምሳሌ? ኑሮና ተረት እያጤነ ከትናንት ስህተት የሚማረው ማን ይሆን? ለካ ይኼንን ሁሉ ለመናገር ሰሚ ያስፈልግ አይደል? መልካም ጉዞ!