Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያ ባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ክፍያችን ዘገየብን እያሉ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2007 በጀት ዓመት ካገኙት ትርፍ ለባለአክሲዮኖቻቸው መክፈል የሚገባቸውን የትርፍ ክፍፍል እንዳዘገዩባቸው ባለአክሲዮኖች እየገለጹ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ያገኙትን ዓመታዊ ትርፍ ያወጁና በበጀት ዓመቱ ከተገኘው ትርፍ ባለአክሲዮኖች ምን ያህል እንደሚደርሳቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ የትርፍ ድርሻቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሳይከፈላቸው እንደዘገየባቸው ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የኩባንያዎቹ ጠቅላላ ጉባዔ ከተደረገ በኋላ በጥቂት ቀናት ልዩነት፣ እንዲያውም በማግሥቱ ጭምር የትርፍ ድርሻቸው በአካውንታቸው ይገባ እንደነበር፣ ወይም በግንባር ቀርበው ይወስዱ እንደነበረ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለአክሲዮኖች ይገልጻሉ፡፡ ዘንድሮ ግን የትርፍ ክፍፍሉን ሳያገኙ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው አስረድተዋል፡፡

ከባንክና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን፣ የትርፍ ክፍፍሉ ሊዘገይ የቻለው በአዲሱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ክፍያውን ለመፈጸም በቅድሚያ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡

በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የትርፍ ክፍፍል የሚፈጸመው፣ የጠቅላላ ጉባዔው ቃለ ጉባዔ በሰነዶችና ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤትና በብሔራዊ ባንክ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ቀደም ባለው አሠራር ግን የባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ይፈጸም የነበረው የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት ምዝገባ ወይም የብሔራዊ ባንክን ማረጋገጫ ሳይጠበቅ እንደነበር ነው፡፡

ከአንዳንድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች የተገኘው መረጃ ግን የ2007 በጀት ዓመት ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔው በጽሕፈት ቤቱ ከተረጋገጠና ከፀደቀ በኋላ በተለመደው አሠራር የትርፍ ክፍፍሉ እንደሚፈጸም ያመለክታል፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎችም የማረጋገጡ ሥራ በቶሎ ስለሚያልቅ የትርፍ ክፍፍሉ ክፍያ ይጀመራል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ከበፊቱ አሠራር የተለየ እንዲሆን ያደረገው ይኼው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ቢሆንም፣ የክፍያ ጊዜ ይህንን ያህል ዘገየ የሚያስብል ያለመሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

የ2007 በጀት ዓመት የሥራ ክንውናቸውና የትርፍ ክፍፍላቸውን ካስታወቁት ባንኮች መካከል አዋሽ፣ ዳሸን፣ አቢሲኒያ፣ ኅብረት፣ ቡናና ወጋገን ባንኮች ይጠቀሳሉ፡፡

ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ መካከል እንደ ኅብረት፣ ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀኔራል ኢንሹራንስ ያሉት ይገኙበታል፡፡ መጠባበቂያና ሌሎች ወጪዎች ተቀንሰው ለበጀት ዓመቱ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፈል ውሳኔ ካሳለፉት ውጪ አንዳንዶቹ በበጀት ዓመቱ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል የተወሰነውን ትርፍ ለኩባንያዎቻቸው ካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል የወሰኑም አሉ፡፡

የትርፍ ድርሻቸው በቀጥታ ለካፒታል ማሳደጊያነት ካዋሉት መካከል ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀኔራል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበርና ደቡብ ግሎባል ባንክ ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ 34 የግል ባንኮችና የኢንሹራስ ኩባንያዎች በሥራ ላይ ሲሆኑ፣ እነዚህ ኩባንያዎች ከ110 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች አሏቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች