Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ፀደቀ

የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

– የአገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበር ጥያቄዎች አልተመለሱም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በታኅሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሎው በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ጥቂት ማሻሻያዎች በማድረግ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡

የፓርላማው ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ በመሆን ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ፣ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ ሕጋዊ በሚመስል ሽፋን ሲደረግ የነበረውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚከላከል ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሥራ ላይ ባሉ አዋጆችና መመርያዎች ምክንያት በአፈጻጸም ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በውሳኔ ሐሳባቸው ለምክር ቤቱ አረጋግጠዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎቹ የሕጉ አመንጪ ከሆነው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በዕግድ ላይ ከሚገኙት የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ምክክሮችን ካካሄዱ በኋላ የተለያዩ የቃላትና የይዘት ማሻሻያዎችን አድርገዋል፡፡

የይዘት ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንቀጾች መካከል የሠራተኞች የጤና ምርመራ የሚደረገው በተቀባይ አገር የጤና ጉዳይ ተቋምና በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጋራ በሚመረጡ የኢትዮጵያ የጤና ተቋማት ይሆናል የሚለው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ ይገኝበታል፡፡

ይህ አሠራር ቀድሞ የነበረ ቢሆንም ዜጐችን ለችግር የሚዳርግና የኪራይ መሰብሰቢያ ምንጭ በመሆኑ፣ እንዲሁም በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ የሌላ አገርን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት ‹‹የሠራተኛ የጤና ምርመራ የሚደረገው የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚመርጠው የጤና ተቋማት ብቻ ይሆናል፤›› በሚል ተስተካክሏል፡፡

በሌላ በኩል የሥራ ሥምሪትና አገናኝ ኤጀንሲ ለመመሥረት በግል ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከሆነ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ በረቂቁ የተደነገገ ሲሆን፣ ኤጀንሲዎች በማኅበራቸው አማካይነት በንግድ ሕጉ መሠረት እንዲሆንላቸው ሲጠይቁ ነበር፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎቹ ይህንን የረቂቁን ድንጋጌ በማሻሻል፣ ‹‹አመልካቹ የንግድ ማኅበር ከሆነ የተቋቋመበት ዓላማ በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ የተቋቋመ የንግድ ማኅበር አባላት በሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸውና ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ የተዋጣ የአክሲዮን ወይም መዋጮ፤›› በሚል አስተካክሎታል፡፡

አገናኝ ኤጀንሲዎች በማኅበራቸው በኩል ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ለሥራ ፈላጊዎች የሚያስቀምጠው 8ኛ ክፍል ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ይገኝበታል፡፡ ይኼው ጥያቄ ፓርላማው ረቂቁን ለማፅደቅ በተወያየበት ወቅትም በድጋሚ ተነስቷል፡፡ አስገዳጅ የትምህርት ደረጃ ማስቀመጡ የዜጐችን የመንቀሳቀስ መብት አይገድብም ወይ የሚል ጥያቄ በተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት ቀርቧል፡፡

የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በሰጡት ምላሽ፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው የዜጐች የመዘዋወር መብት ገደብ የማይጣልበት ሙሉ ነፃነት አይደለም ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው፣ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት በመንግሥት የሚደገፍ አይደለም ብለዋል፡፡ የሚቀመጠውን ገደብ አልፈው የሚወጡ ዜጐች ክብርና መብታቸውን መንግሥት የማስከበር ግዴታ ስላለበት፣ ይህንኑ በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል አዋጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...