Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በኦሮሚያና በአማራ የተከሰቱ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል አለ

መንግሥት በኦሮሚያና በአማራ የተከሰቱ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል አለ

ቀን:

  •  በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል በድንበር ዙሪያ የተለየ ውይይት የለም ብሏል
  •  በኦሮሚያ የተከሰተው ሁከት በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ አለው አለ
  •  የድርቁ ተጎጂዎች በፍትሐዊነት እንዲረዱ ክትትል መደረጉን ገልጿል

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባሠራጨው ሳምንታዊ መልዕክት፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታወቀ፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን አጥፊዎችን የማጋለጥና ለፍትሕ የማቅረብ ሥራ እያካሄደ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች በማስተር ፕላኑና በቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ መነሻነት የተከሰቱት ግጭቶች በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የሚስተናገዱበት ሕጋዊ መሠረት ቢኖርም፣ ሕይወትና ንብረት የሚያጠፉ ሁከት ለመፍጠር የሚያስችል ምንም መነሻ እንዳልነበረ አስገንዝቧል፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልል በግጭቱ ዙሪያ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ‹‹የተማሪውንና የሕዝቡን ሰላማዊ ጥያቄ ወደ ሁከት የቀየሩ ወገኖች የየአካባቢውን ንብረትና አቅም በማስገደድና በማደናበር ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ የሕዝብና የአስተዳደር ተቋማትን አውድመዋል፡፡ ነፍሰጡር የጫኑ አምቡላንሶችን ሰባብረዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች ሰብረው ገብተው ለዘመናት ክርክር የተደረገባቸውና ውሳኔ የተሰጠባቸው፣ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ዕቅዳችን መፍትሔ የሚጠብቁ ፋይሎችን አቃጥለዋል፡፡ የከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤቶችን፣ የማዘጋጃ ተቋማትን፣ ፖሊስ ጣቢያዎችን፣ ጤና ተቋማትን አቃጥለዋል፡፡ የከተማውን አመራሮችና ነዋሪዎች ቤትና ንብረት ዘርፈዋል፣ አቃጥለዋል፡፡ በከተሞቹ ውስጥ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶችን ንብረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዘርፈዋል፣ አውድመዋል፡፡ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ያለሙ ግድያዎችን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ፈጽመዋል፤›› በማለት መግለጫው የደረሰውን ጉዳት ዘርዝሯል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ እንዳሉ ያስታወሰው መግለጫው፣ ‹‹የአክራሪነት፣ የጥበት፣ የትምክህትና የሙስና መፈልፈያ የሆነው የመልካም አስተዳደር ችግርን ከሥር መሠረቱ መፍታት የማይታለፍና ለነገ የማይባል ተግባር ነው፤›› ሲልም አስፍሯል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች ከተከሰተው ግጭት በስተጀርባ እጃቸው አለበት ያላቸው ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ቡድኖች የሕዝብን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሊፈቱ እንደማይችሉም መንግሥት አስታውቋል፡፡ ‹‹የሕዝብ ሀብት የፈሰሰባቸው መሠረተ ልማቶችንና የመገልገያ ተቋማትን በማውደም ልማት አይመጣም፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ከተሞቹ ዳግም እንዳይደርሱ በማድረግ ሕዝቡ አይጠቀምም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር በዚህ ዓይነት በተበተነና ከየአቅጣጫው እየተጠራራ በተሰባሰበ ኃይልና ታጣቂ ቡድን ሊፈታ አይችልም፤›› ሲልም መግለጫው ያብራራል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የተለያዩ የሕዝብ ጉዳዮችን እያራገቡ ኑሯቸውን የሚገፉ፣ በየአጋጣሚው ሰላማዊ የሆነውን ሕይወት በመበጥበጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ሕዝብ ያነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈቱ እንዳልሆኑም አክሎ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር በተመለከተም፣ ድንበር መካለሉ ተገቢና ጠቃሚ ቢሆንም ድንበር ለማካለል አሁን ምንም የተደረገ ስምምነት እንደሌለ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም የተለየ ውይይት እየተደረገ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡ ‹‹የኢፌዴሪ መንግሥት የድንበር ማካለል ሥራ ሲኖር በድንበሮቹ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎቻችንን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲሆን ጽኑ አቋም አለው፤›› ሲልም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ አረጋግጧል፡፡

መግለጫው በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ግጭት አገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እያደገች ባለው ጥረት ላይ ጉዳት ማስከተሉንም ጠቁሟል፡፡ በድርቅ ምክንያት የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ርብርብ በሚደረግበት ወቅት፣ በግጭቱ የሰላማዊ ዜጎች ሕይወትና ንብረት መጥፋቱ አሳዛኝ እንደሆነም ገልጿል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል ባለፉት ተከታታይ ዓመታት አገሪቱ ያስመዘገበችው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉንም አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ይህ ዕድገቷ ዓለምን ያሳመነ፣ የዜጎችንም ሕይወት በእጅጉ ያሻሻለ ነው፤›› ብሎ፣ የኤልኒኖ ተፅዕኖ ያስከተለው ድርቅ ማሳዎችን በማድረቁ በርካታ ዜጎችን ወደ ተረጂነት መመለሱን አስታውሷል፡፡

ለሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ሲል የድርቁን ጉዳይ ቸል እንዳለው፣ እንዲሁም ለፖለቲካዊ ፍጆታ እንደተጠቀመበት የሚተቸው መንግሥት በዚሁ መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት ሥጋቱ መኖሩን ቀድሞ በመገመት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቋል፡፡ የራሱንም ዝግጅት አድርጓል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜም በራሱ አቅም በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ዕርዳታ ማቅረብ ችሏል፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች ለሳምንታት ሁከት ተፈጥሮ በቆየ ጊዜ እንኳ መንግሥት ለአንድ ደቂቃም ከድርቁ ላይ ትኩረቱን ሳያነሳ መከታተል ችሏል፡፡ የዝናቡ ሁኔታ መሻሻል አለማሳየት በቀጣይ ወራት የተረጂዎችን ቁጥር በምን ያህል ሊያሳድገው እንደሚችል በማጥናት፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅና የራስን ዝግጅት ማድረግም ቀጥሏል፤›› ሲል የሚቀርብበትን ወቀሳ አጣጥሏል፡፡ ለተረጂዎች ፍትሐዊ ዕርዳታ ለማድረግም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

መንግሥት በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት በተከሰተው ግጭት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችንና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን እስካሁን ይፋ አላደረገም፡፡ በግጭቱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተጠቀሙት ኃይል ያልተመጣጠነ ነው በሚልም ይወቀሳል፡፡ ከአምስት ሳምንታት በላይ በቆዩት በእነዚህ ግጭቶች ሌሎች ኃይሎች ባስከተሉት ጉዳትና ፕሮፓጋንዳ የተከሰቱ ችግሮች ላይ በማተኮር፣ በራሱ በመንግሥት መዋቅርና ኃይሎች ክፍተት ላይ መንግሥት ምንም ለማለት ባለመፍቀዱ እየተተቸ ይገኛል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...