በገብረ እግዚአብሔር ወንዳፈረው (ሌ/ኮሎኔል)
ኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ነፃነቷንና አንድነቷን አስጠብቃ የኖረችው በጀግኖች አባቶቻችንና በጠንካራ ሕዝቧ አትንኩኝ ባይነት፣ ከየአቅጣጫው የተነሱባትን ጠላቶች ድል በማድረግ መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ይህ ዕውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም ላይ እየተከሰተ የመጣውን የሥልጣኔ ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያም የምድር፣ የአየርና የባህር ክልሎቿን ለማስከበር የሚያስችል ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል ካቋቋመች ረጅም ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ይህ የመከላከያ ሠራዊት እንደ ጥንቱ ሁሉ በሕዝቧ ደጀንነት በመታገዝ፣ በየወቅቱ ከተነሱባት ጠላቶች ጋር በመፋለም የአገር ዳር ድንበር በሚገባ ሲያስከብር ኖሯል እያስከበረም ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ በገባችው ዓለም አቀፋዊ ግዴታ መሠረት በተለያዩ አገሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ሠራዊቱ በመዝመት፣ ከፍተኛ ድሎችን በመቀዳጀት የሙያ ብቃቱን አስመስክሯል።
ይህን ሁሉ የሠራ ሠራዊት ግን ታሪኩ በአግባቡ ሳይመዘገብ ጊዜ እያለፈና ታሪክ የሠሩት አባላቱም በዕድሜና በተለያዩ ምክንያቶች በሕይወት የሉም፡፡ ያሉትም አስታዋሽ አጥተው እየደከሙ በመሄዳቸው፣ በጥቂት ያልተሟሉ የጽሑፍ ሰነዶች ብቻ ታሪኩ ተወስኖ እንደሚቀር እየታየ ነው፡፡ ይህም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛውን ክፍተት እንደሚፈጥር ግልጽ ነው።
በኢትዮጵያ የመከላከያ ተቋም ተመዝግበው የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በውትድርና ሙያ ያገለገሉና በማገልገል ላይ ለሚገኙ አባላት፣ በዕድሜ ጣሪያና በተለያዩ ምክንያቶች ከሠራዊቱ በክብር የተሰናበቱትን በማሰባሰብና በማደራጀት ተገቢውን ክብርና የጤና አገልግሎት እያገኙ፣ ቀሪው ዘመናቸውን ለተመቻቸ ኑሮ ማብቃት አስፈላጊም ተገቢም ነው፡፡ ስለዚህ የሠራዊቱም አኩሪ ታሪክ በተግባር ከተሳተፉ አባላት ምስክርነት በመመዝገብና በተለያየ ሁኔታ ተበታትነው የሚገኙትን ሰነዶች በማሰባሰብ ትክክለኛና ያልተዛባ ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማቆየት፣ ሒደቱ ሳይቋረጥ የሚቀጥል የአገር መከላከያ ሠራዊት ቬተራንስ አሶሴሽን እንዲኖር ማድረግ ነው። ዓላማው በመተዳደሪያ ደንቡ በዝርዝር የተመለከተ ሲሆን፣ ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ በጠቅላላ ጉባዔው ሲፀድቅ ይቀርባል፡፡
የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ቢያንስ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት መመሥረት እንደነበረበት ቢታመንም፣ ይህ አለመደረጉ ያለፉት ሁለት መንግሥታት በተለይም የደርግ ድክመት እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ መሰል ማኅበራት ጋር ለመገናኘትና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ለመከላከያ ዕድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ አሁንም ከታሪክና ከመጪው ትውልድ ወቀሳ ለመዳን “ቢዘገይም ጭርሱኑ ከሚቀር መጀመር ይበጃልና” መጪው ትውልድ ይቀጥልበታል በሚል ዕምነት፣ ይህን በጎ ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ጥረት ላይ እንገኛለን።
በአገራችን የቬተራንስ አሶሴሽን አለመኖሩ በርካታ ሁነኛ ታሪኮች ሳይመዘገቡ ተቀብረው ቀርተዋል። ሆኖም በ1998 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በጦር ኃይሎች መኮንኖች ክበብ ባደረጉት ንግግር፣ “የተለያዩ ማኅበራት ከምታቋቁሙ አንድ ማዕከላዊ የሆነ የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ብትመሠርቱ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል፤” ብለው ባሳሰቡት መሠረት በወቅቱ ከምድር ጦር፣ ከአየር ኃይልና ከባህር ኃይል የተገኙ መኮንኖች በመነጋገር ስብሰባ አደረጉ፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመምረጥ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሊቀመንበር ሆኑ (በሕይወት የሚገኙት ብቸኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባልም ናቸው)፡፡ እሳቸውም ለሦስት ዓመታት ያህል በማደራጀት ከቆዩ በኋላ በጤና ችግር ምክንያት ኃላፊነታቸውን አስረከቡ፡፡ ሆኖም በአባልነት ቀጥለዋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ ምርጫ ተደርጎ ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡ ሜጀር ጄኔራል አበበ ወልደ ማርያም ሊቀመንበር፣ ኮሎኔል አበራ ኃይለ ማርያም ምክትል ሊቀመንበር ሆኑ (ሁለቱም በሕይውት የሉም)፡፡
ከሦስቱም ኃይሎች 20 አባላት ከአዲስ አበባ ከአምስት፣ ክልሎች ከእያንዳንዱ ሦስት አባላት፣ በአጠቃላይ 35 መሥራች አባላትን በማስመዝገብ የመተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀት፣ ከሁለት ዓመት ከፍተኛ ጥረትና ድካም በኋላ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ቁጥሩ 2048 የሆነ የኢትዮጵያ ማኅበር ሆኖ፣ ከጥቅምት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. የምዝገባ ሰርተፊኬት አግኝቷል።
የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽንም ይህን በጎ ዓላማ ይዞ ተነስቷል፡፡ የአገሪቱ ዜጎችም ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ማድረግ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ይህም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በቀጥታ የሚመለከተው በመሆኑ የመደገፍና የማስተዋወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሶሴሽኑ መሥራች አባላት የሆኑት በሕመምና በእርጅና ከዚህ ዓለም እየተለዩ ነው፡፡ ቀሪዎቹም ዕድሜያቸው እየገፋ በመሆኑ በሌሎች አባላት ይተካሉ፡፡ የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ግን የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት እስካለ ድረስ ይኖራል። ትውልድ እየተተካ ስለሚቀጥል ማቋረጫ የሌለው የዓባይ ወንዝ ማለት ነው። የአገር መከላከያ ቬተራንሰ አሶሴሽን የበላይ ጠባቂም የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወይም ፕሬዚዳንት በመሆናቸው፣ አሶሴሽኑ ጥንካሬ እንዲያገኝ ከአሶሴሽኑ አመራር አባላት ጋር በመገናኘት ሊያግዙት ይገባል።
ኅዳር 1 ቀን (November 11) የአሜሪካ ቬተራንስ ቀን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በቅርቡ በዓሉን አስመልክተው ፕሬዚዳንት ኦባማ በዕለቱ ያደረጉትን ንግግር በሁሉም መገናኛ ብዙኃን ስለተዘገበ ፈልጎ ማግኘትና መረዳት ይቻላል፡፡ ለአሜሪካን ቬተራንስ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የገለጹባቸው ቃላት እጅግ የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ “መንግሥታትና መሪዎች ለሠራዊታቸው ክብር ዘብ ይቆማሉ፤” ነው ያሉት። በእርግጥ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር እንዳለን ይታወቃል፡፡ ይህ ግን በማይጨው ጦርነት ወቅት ፋሺስት ኢጣሊያንን ለመውጋት በአርበኞች የተመሠረተ ነው፡፡ ከነፃነት በኋላ በጦር ሚኒስቴርና በንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታ አርበኞችን ለመርዳት መቀጠሉ ይታወቃል። ከዚያ በኋላ ግን በበርካታ ግዳጆች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በኦጋዴን (በተደጋጋሚ ጊዜ ከሞቃዲሾ መንግሥት ለደረሰው ወረራ) በቅርቡም በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በቡሩንዲ፣ በዳርፉር (ሱዳን)፣ በአቢየ ግዛት (ደቡብ ሱዳን) ለዘመተው ሠራዊት ባለቤት ሊሆነው የሚችለው ይኸው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ነው። ዘላቂ፣ ዘላለማዊና ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ።
የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ዕውቅና ከተሰጠው በኋላ የተወሰኑ አባላት በሞት ሲለዩ፣ የተወሰኑት በጤናና በራሳቸው ምክንያት ኮሚቴውን ሊመሩ ባለመቻላቸው፣ እንዲሁም ዋና ጸሐፊው ወደ ውጭ አገር በሄዱበት ወቅት ከመከላከያና ከማኅበራት ኤጀንሲ ጋር ግንኙነት በመቋረጡ እንቅስቃሴው ለተወሰነ ጊዜ ተጎትቷል። በእነዚህ ከፍተኛ ልፋትና ድካም በጠየቁት ዓመታትም ከሥራ አስፈጻሚው ጎን በመሠለፍ ጉዳያችን ብለው በመተካት አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ ናቸው።
ከሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ካፕቴን ፀጋየ ገብረ ዮሐንስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ቢመረጡም፣ ለአንድ ወር ያህል ከመሩ በኋላ እሳቸውም ለሕክምና ከአገር ውጭ በመሄዳቸው ምክትል ሰብሳቢም ባለመኖሩ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ዋና ጸሐፊው ደርበው በመሥራት ኮሚቴውን እንዲመሩ ውክልና በመስጠታቸው፣ ከነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እኔ (ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር) በሰብሳቢነት ጭምር በማገልገል ላይ እገኛለሁ።
የቬተራንስ አሶሴሽን የመከላከያን ድጋፍ ቢያገኝም ውሳኔ የሚያሻቸው የቢሮና የመሰብሰቢያ ቦታ ችግር ሊፈታ ይገባዋል፡፡ ቀጣይ ሥራዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ማከናወንና የተፈለገው ግብ መድረስ የሚቻለውም የገንዘብ አቅም ሲኖር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ድጋፍ ካደረጉ ግለስቦች በተጨማሪ የሮኪ ቫሊ ባለቤት የነበሩት ኮሎኔል ንጉሤ እሸቴ ከረዳታቸው ኮሎኔል ለማ ለገሰ (ሁለቱም በሕይወት የሉም) ቢሯቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንድንገለገልበት ፈቅደዋል፡፡ በተለይ የዲላይት የጉዞና አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት የሆኑት አቶ ቢንያም ገብረ እግዚአብሔር ቢሯቸውን በቋሚነት እንድንጠቀምበት በመፍቀዳቸው፣ የቢሮና የስብስባ ቦታ ችግር በመወገዱ በተረጋጋ ሁኔታ መሥራትና የቅርብ ክትትልም ማድረግ በመቻሉ ዕውቅና በአጭር ጊዜ አግኝተናል።
የቀድሞ ባህር ኃይል አባላት ክበባቸውን ለሳምንታዊ ስብሰባ አሁን ድረስ እንድንገለገልበት ፈቅደዋልና ምሥጋና ይገባቸዋል። አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ ትክክለኛ አመራር በመስጠት ያገለገሉትን ሜ/ጄ አበበ ወልደ ማርያምና ኮሎኔል አበራ ኃይለ ማርያም ምንጊዜም ይታወሳሉ፡፡ አፈሩን ያቅልልላቸው፡፡ ዓላማቸውን ከግቡ ለማድረስ ጥረታችን ይቀጥላል። (የቬተራንስ ጋዜጣ እስኪፈጠር ድረስ ተዛማጅ ጹሑፎች ለማቅረብ እንድንችል ሪፖርተርን በአክብሮት እንጠይቃለን)።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡