Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሂፕ ሃፕን በአገርኛ

ሂፕ ሃፕን በአገርኛ

ቀን:

ሂፕ ሃፕ በአገርኛ እንዲ እያማረበት

እኛም ተሸልመን ተመርቀንበት

አይዟችሁ ጐብዙ ብለውን በርቱበት

የስንቱ ቤት ድግስ አማረበት እውነት

እዚ ቤት እዛ ቤት ሁሉም ጋር ሲጠሩን

ይኼ የኛ ዜማ አውቀው መጣፈጡን

ሁሉም ሰሚ ሆነ ከፍቶ ዘግቶ በሩን

አንድ ሰው ቀርቶኛል ልወቀው እቅጩን

ሂፕ ሃፕ በአገርኛ ሰምተው ያውቁ እንደሆነ

እስኪ ጠይቋቸው ክቡር ሚኒስትሩን…

የተቀነጨበው በቅርቡ ከተለቀቀው የልጅ ሚካኤል (ፋፍ) አልበም ‹‹ዛሬ ይሁን ነገ›› ሲሆን፣ የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ይህ ዘፈን ተደማጭነት ካገኙ ሥራዎቹ አንዱ ነው፡፡ የሂፕ ሃፕ አልበሙ በሙዚቃ ማሰራጫ ድረ ገጾች ተጭኖ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርቧል፡፡ ልጅ ሚካኤል እንደሚናገረውም፣ ከጠበቀው በላይ በጐ ምላሽ እየተሰጠው ነው፡፡ ስልቱ የሚወደደው በወጣቶች ቢሆንም በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ጆሮ እንዳገኘ ያምናል፡፡

የተወለደው ጃንሜዳ አካባቢ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች በሚዘጋጁ ካርኒቫሎች ላይ መድረክ በመምራትና ዲጄዎች የሚከፍቷቸውን ሙዚቃዎች ተከትሎ በመዝፈን ሙዚቃን ‹‹ሀ›› ብሎ የተቀላቀለው ልጅ ሚካኤል የሂፕ ሃፕ ፍቅር ያደረበት በለጋ ዕድሜው ነው፡፡

የሌሎች አገሮችን ታሪክ፣ ባህልና አኗኗር የሚያንፀባርቁ ዘፈኖችን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንደማይገባ ያምናል፡፡ አልበሙን በሚያዘጋጅበት ወቅትም አገር ውስጥ ካለው አድማጭ ጋር ሊያግባባው የሚችል ግጥም መጻፍ ላይ አተኩሯል፡፡ ሂፕ ሃፕ በኢትዮጵያ ከተለመደው የሙዚቃ ዘዬ ስለሚለይ የአድማጭን ቀልብ ለመግዛት የዘፈኑ ግጥም ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል ይላል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ አካባቢ በአሜሪካ ውስጥ በጥቁር አሜሪካውያን የተፈጠረውን ሂፕ ሃፕ በተለይም ከነፃነት ትግል ጋር አያይዘው የሚያነሱት አሉ፡፡ በአጭር ጊዜ በፍጥነት ዓለም ላይ የተሰራጨው ሂፕ ሃፕ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ በይበልጥ የወጣቶችን ቀልብ እንደሚስብ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የሂፕ ሃፕ ሙዚቃ ቃላት አጠቃቀምና የሙዚቀኞቹ አቀራረብ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም አይታጡም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሂፕ ሃፕ ጥቂት ዓመታት ያስቆጠረ የሙዚቃ ዘዬ ነው፡፡ የሂፕ ሃፕ ፍቅር ያላቸው ወጣት ዘፋኞች ብዙ ቢሆኑም ከውስን መድረኮች ሲያልፉ አይስተዋልም፡፡ አልበም የለቀቁ፣ በአገር ውስጥና በውጭም ሥራቸውን የሚያቀርቡ ቢኖሩም፣ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሂፕ ሃፕ ፈተና የበዛበት ዘዬ እንደሆነ ሙዚቀኞቹ ይስማሙበታል፡፡ አንዱ ተግዳሮት በአድማጮች የሚሰጠው አነስተኛ ግምት ሲሆን፣ በቂ መድረክ አለማግኘትና የስፖንሰሮች ውስንነትም ይጠቀሳሉ፡፡

ልጅ ሚካኤል ዘርፉን በዋነኛነት የሚፈታተነው አድማጮችና የሂፕ ሃፕ አርቲስቶችም ያላቸው ግንዛቤ ማነስ ነው ይላል፡፡ አድማጮች ሂፕ ሃፕ ከኢትዮጵያ ውጪ ስለመጣ ከሚሰጡት አናሳ ቦታ ባሻገር፣ ሙዚቀኞቹ የሚያስተላልፉት መልዕክት በጐ እንዳልሆነ ይገምታሉ፡፡ በእርግጥ ሁሉም አርቲስቶች ባይሆኑም የውጭውን የሂፕ ሃፕ ባህል ያላግባብ በቀጥታ የሚያመጡ አሉ፡፡ በእሱ እምነት፣ ለኢትዮጵያውያን አድማጮች ሂፕ ሃፕ በኢትትዮጵያ ቅኝት ቢሠራ መልካም ነው፡፡

‹‹የሂፕ ሃፕ ትርጉም ያልገባቸውና ለአድማጭ ግልጽ ያልሆነ ሙዚቃ የሚሠሩ ዘፋኞች ከአድማጮች የማንነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል፤›› የሚለው ሙዚቀኛው፣ የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች ብዙኃኑ የሚገነዘበውን ሙዚቃ ካልሠሩ፣ ሕዝቡ ለስልቱ ያለው ዝቅተኛ ግምት እንደማይለወጥ ያምናል፡፡ በእርግጥ በተሻለ መንገድ የሚሠሩትንም የማይሠሩትንም በአንድ ሚዛን የመፈረጅ ነገር እንዳለ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

‹‹ቅጥ ያጣ ዘፈን››ን በመሰሉ አሉታዊ ቃላት ሂፕ ሃፕን የሚገልጹ ገጥመውታል፡፡ አለባበሳቸውና አነጋገራቸው አጸያፊ እንደሆነ በመውሰድ ገና የስልቱን ስም ሲሰሙ የሚያንገሸግሻቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹‹ሂፕ ሃፕ የውስጤን ስሜት የምገልጽበት፣ ሂፕ ሃፕን ከማይወድና ጥሩ ስም ከማይሰጠው ሰው ጋር መታረቂያዬም ነው፤›› ሲል የሚገልጸው ልጅ ሚካኤል፣ ሙዚቀኞቹ ተጽእኖውን መቋቋምና ዘርፉን ማሳደግ የሚችሉት የሚጠቀሙት ቋንቋ፣ የሙዚቃው ይዘትና አቀራረብ ፈር ሲይዝ ነው ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው አንፃር ዛሬ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ድሮም ዛሬም የሂፕ ሃፕ ቦታ ቢሆኑም፣ ዛሬ ዛሬ ሥራዎቻቸውን በክልል ከተሞችና ከኢትዮጵያ ውጪም የማቅረብ ዕድል አላቸው፡፡

የልጅ ሚካኤልን ሐሳብ ከሞላ ጎደል የሚጋራው ሌላው የሂፕ ሃፕ አርቲስት ቴዲ ዮ፣ ሙዚቀኞቹ በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪም መድረክ ማግኘታው ባለፉት ዓመታት የታየ ለውጥ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከዓመታት በፊት ሥራዎቹን ባቀረበባቸው የክልል ከተሞች ያሉ አድማጮች ቁጥር ዛሬ ጨምሯል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ቋንቋዎች ራፕ የሚያደርጉ ወጣቶችም ተበራክተዋል፡፡ ሂፕ ሃፕ ከኢትዮጵያ ሽለላና ቀረርቶ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውና ከውጭ ስለተቀዳ ለብዙዎች ቦታ ባይሰጡትም፣ ትኩረት ከተቸረው አድማጮች በቀላሉ የሚወዱት ስልት እንደሆነ ይናገራል፡፡

እንደ ሌሎች የሙዚቃ ዘዬዎች ሁሉ የኮፒ ራይት መብት ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች ከሌሎች ሙዚቀኞች ያነሰ ቦታ የሚሰጣቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ ‹‹ሂፕ ሃፕ ሙዚቃ የማይመስላቸው አሉ፡፡ ሙዚቀኞቹ ለየት እንዳሉ ፍጡራን የሚታዩበት ጊዜም አለ፤›› የሚለው ቴዲ ዮ፣ ዘርፉ መስዋዕትነት እንዳስከፈለው ይገልጻል፡፡ ሂፕ ሃፕ አመርቂ ገቢ አለማስገኘቱ ፈታኝ እንደሆነም ያክላል፡፡  

ወደ ሙዚቃው የገባው በትምህርት ቤቶች በሚካሄዱ ካርኒቫሎች ራፕ በማድረግ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ የሂፕ ሃፕ ሙዚቃዎችን ከሬዲዮ ጣቢያዎች በካሴት በመቅዳት ይለማመድ ነበር፡፡ የቀን ፓርቲዎች ሲዘጋጁ ከማይጠፉ ወጣቶች አንዱ የሆነው ቴዲ ዮ ፍሪ ስታይል (መድረክ ላይ ግጥሞችን እየፈጠሩ በዜማ በማቅረብ) የሚወዳደርባቸውን ጊዜዎች ያስታውሳል፡፡

ከሕዝብ ያስተዋወቀውን ‹‹ጉራጌ ቶን›› ከለቀቀ በኋላ ዘፈኑን በትልልቅ መድረኮች ማቅረቡ የሙዚቃ ሕይወቱን እንደለወጠው ይናገራል፡፡ የሂፕ ሃፕ አልበሞች እምብዛም ባልነበሩበት ጊዜ በ2001 ዓ.ም. የለቀቀው የመጀመሪያ አልበሙ፣ በስፋት ባይሰራጭም ጥሩ እንደተደመጠ ይናገራል፡፡

አሁን ‹‹እስረኛ›› የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ሠርቶ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቅርቡ እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡ ሂፕ ሃፕን ከኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ጋር በማዋሃድ እንደሠራ ይናገራል፡፡ የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ ሲባል ከቋንቋ በተጨማሪ በተለያየ መንገድ አገሪቱን የሚወክል መሆን አለበት ይላል፡፡ ዘፋኞቹ በተለያዩ መድረኮች የሚያቀርቧቸውን በመሰነድና በድረ ገጾች በማሰራጨት ተደራሽነታቸውን ማስፋት እንደሚገባቸውም ያክላል፡፡

‹‹ሂፕ ሃፕ ሕይወቴ ነው፤ የተፈጠርኩት ለዚህ ስለሆነ ሌላ ነገር መሆን አልችልም፤›› የሚለው ሙዚቀኛው፣ በሂፕ ሃፕ መልካም መልዕክቶችን ማስተላለፍና ለውጥ ማምጣት ይሻል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ሂፕ ሃፕ እንዲያድግ ከሙዚቀኞቹ በተጨማሪ የዲጄዎችና ፕሮዲውሰሮች ድርሻም ሰፊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሂፕ ሃፕ ለአርቲስቱ ከሚያስፈልጉ አልባሳትና የመድረክ ግብአቶች አንፃር ከፍተኛ በጀት ስለሚጠይቅ ድጋፍ የሚሰጡ አካሎች ቢበራከቱ ለውጥ እንደሚመጣ ያምናል፡፡

አስተያየታቸውን እንደሰጡን ዘፋኞች ሁላ ካርኒቫሎች ላይ ራፕ በማድረግ ሙዚቃን የተቀላቀለው ኤምሲ ሲያምረኝ፣ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሂፕ ሃፕ ተደማጭነት እያገኘ መሆኑን ይስማማበታል፡፡ ዘርፉ የሚፈለገው ደረጃ እንዳይደርስ እንቅፋት የሚለው የመገናኛ ብዙኃንንና የተለያዩ ተቋሞችን ችላ ባይነት ነው፡፡

መገናኛ ብዙኃን ለኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ አርቲስቶች ተገቢውን ሽፋን እንዳልሰጡ ይገልጻል፡፡ ሙዚቃዎቻቸውን ለማጫወት ፈቃደኛ የሆኑ ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ፣ ለሌሎች አገሮች አርቲስቶች ቅድሚያ የሚሰጥበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ጥሩ ስም እንዲኖረንና እንድናድግ የሚያበረታቱን ጥቂቶች ናቸው፤ ስፖንሰር ስንጠይቅ ምክንያት ፈልገው የሚከለክሉን ይበዛሉ፤›› ይላል፡፡

ሂፕ ሃፕን ከሚያደንቁ ወጣቶች መካከል ገንዘብ አውጥተው አልበም የመግዛት አቅሙ ያላቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ዘርፉ ገቢ አለማስገኘቱ አንዳንዶቹን የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች ወደ ሌላ ስልት እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ኤምሲ ሲያምረኝ እንደሚለው፣ ከዚህ በተቃራኒው ከአንጋፋ አርቲስቶች ጋር (ፊቸሪንግ እየሠሩ) መጣመራቸው እንደ ጥሩ ጅማሮ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ከዓመታት በፊት ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት የተዘጋጀ ካርኒቫል ላይ ሄዶ ‹‹ማድ ቦይስ›› የተሰኙ ቡድን አባላት ይተዋወቃል፡፡ አብሯቸው ለጥቂት ጊዜ ከሠራ በኋላ እንደ ሳም ቮድና ሳሚ ካሳ ያሉ የሂፕ ሃፕ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ጋር ‹‹ሐበሻ ፌኖሚና›› የሚል ቡድን መሠረቱ፡፡ በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያ አልበማቸው አሜሪካ ቢለቀቅም፣ አገር ውስጥ አልተሰራጨም፡፡ ቡድኑ ከተበተነ በኋላ በከፊል የእንግሊዝኛና አማርኛ አልበም አዘጋጀ፡፡ አልበሙ ተደማጭነት እንደማያገኝ በመስጋት እንግሊዝኛዎቹን ወደ አማርኛ በመመለስ፣ አልበሙን በዚህ ዓመት ለመልቀቅ መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡

‹‹ልጆቻችንን አበላሻችሁ›› የሚሉ ወላጆች፣ መድረክ ላይ ዕቃ የሚወረውሩ ታዳሚዎች ገጥመውት እንዳሳዘነው ሁሉ፣ አድናቆታቸውን የሚቸሩት ተስፋ ይሰጡታል፡፡ በሂፕ ሃፕ ዓመታትን ካስቆጠሩ ሙዚቀኞች አንዱ የሆነው ኤምሲ ሲያምረኝ፣ እሱና የሙያ አጋሮቹ ሂፕ ሃፕን ለማቆም መታገላቸውን ይገልጻል፡፡ ቴዲ ዮና ልጅ ሚካኤል የሚታያቸውን የተስፋ ጭላንጭልም ይጋራል፡፡

የጀንግል ስቱዲዮ ባለቤትና ሙዚቃ አቀናባሪ ጆላክስ በብዛት የሚሠራው ሂፕ ሃፕና ዳንሶል ሙዚቃ ሲሆን፣ ጥሩ የሂፕ ሃፕ ሙዚቃ የሚሠሩ ወጣቶች ቢኖሩም ወደ ስቱዲዮው ሲመጡ ገንዘብ እንደሌላቸው ይናገራል፡፡ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ የሂፕ ሃፕ አድማጮች ቁጥር መበራከቱን ገልጾ፣ ሙዚቀኞቹ ስፖንሰር አግኝተው ሥራዎቻቸውን ለገበያ ቢያውሉ እንደሚወደዱ እምነቱ ነው፡፡

ዘፋኞቹ ተሰባስበው ሕዝቡ ሥራዎቻቸውን የሚያደምጥበት መድረክ ቢያዘጋጁ፣ ሂፕ ሃፕን የመስማት ልማድ እንደሚበለጽግ ያምናል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተለቀቁ የሂፕ ሃፕ አልበሞች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው፣ ዘርፉ የበለጠ ሥራ እንደሚያሻው ያመለክታል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ዲጄ አሮን በበኩሉ፣ እንደ ሌሎች የሙዚቃ ዘዬዎች የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ በየቤቱ ገብቷል ባይባልም ተደማጭነቱ ሰፍቷል ይላል፡፡ ስልቱ የኢትዮጵያን ባህል አይወክልም የሚለው አስተሳሰብ ብዙዎቹ አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን ደፍረው ወደ ገበያ እንዳያወጡ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ወጣቶች አጸያፊ ቃላት በመጠቀም መዝፈናቸው መልካም ነገር የሚሠሩትንም የሚሸፍንበት አጋጣሚ እንዳለ ይናገራል፡፡ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ስልት ይከተል ባይባልም በሂፕ ሃፕና በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ መካከል አማካይ ቦታ መኖር አለበት ይላል፡፡

ያሉት የሂፕ ሃፕ ሙዚቃዎች ጥቂት ከመሆናቸው አንፃር የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ በብዛት በክለቦች ባይከፈትም፣ ተወዳጅ የሆኑት ይለቀቃሉ፡፡ ዲጄዎች በክለብ፣ በላውንጅ ወይም ሌላ የመዝናኛ ቦታ እንዳለው ሕዝብ ስሜት ሙዚቃዎቹን እንደሚያስደምጡም ዲጄ አሮን ያክላል፡፡

የሂፕ ሃፕ አድማጭ አልአዛር ፀጋዬ በተለይም የአሜሪካውያኑ ሂፕ ሃፕ አድናቂ ሲሆን፣ ሂፕ ሃፕ ከጥቁር አሜሪካውያን ታሪክ ጋር ያለውን ተያያዥነት ጠቅሶ፣ ለኢትዮጵያዊ ጆሮ አዲስ ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች መነሻቸው ያደረጉት የውጭ ራፐሮችን እንደመሆኑ ከሚያድርባቸው ተጽእኖ የሚላቀቁት ጥቂቱ ናቸው ይላል፡፡

በአንድ ሙዚቃ ማስተላለፍ ከተፈለገው መልዕክት በሚቃረኑ ግብአቶች ቪዲዮ ክሊፖች የሚሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእሱ እምነት፣ የኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ በፍጥነት የማያድገውም የውጭውን ለማስመሰል ሲሞከር ነው፡፡ በሌላ በኩል የሂፕ ሃፕን የሙዚቃ ስልት ተጠቅመው ለኢትዮጵያዊ አድማጭ የሚሆን ሙዚቃ የሚሠሩት መበረታታት እንዳለባቸውም ይናገራል፡፡                      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...