Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጥቂቶች የምግብ ምርጫ

የጥቂቶች የምግብ ምርጫ

ቀን:

በምዕራቡ ዓለም ሥጋና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በመተው አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ መሆን በእጅጉ እየተስፋፋ ያለ የአኗኗር ዘዬ ነው፡፡ ለብዙዎች ሥጋ ተመራጭ ምግብ በሆነበት በእኛ ማኅበረሰብም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አትክልት ተመጋቢ (Vegetarian) መሆን እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለእነዚህ ዓይነት ተመጋቢዎች የሚሆኑ ሌሎች ምግቦችን ብቻ የሚያዘጋጁ ቤቶችም በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየተከፈቱ ነው፡፡

ሰዎች በተለያየ ምክንያት የዚህ ዓይነት የአኗኗር ዘዬ ተከታይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች በጤና ምክንያት፣ ከአኗኗር ዘዬ ምርጫ ጋር በተያያዘ፣ በመንፈሳዊነት ፍልስፍና በሌሎችም ወደዚህ ምርጫ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ብዙዎች አትክልት ተመጋቢ ወደመሆን ያመሩት በተለያዩ የምሥራቁ ዓለም ፍልስፍናዎች ምክንያት ነው፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር የሆነችው ፀደይ ወንድሙ ከ17 ዓመታት በፊት አትክልት ተመጋቢ ለመሆን እንድትወስን ያደረጋት አንድ ጋዜጣ ላይ ያነበበችው የህንዳዊው ፈላስፋ ኦሾ የአመጋገብ ፍልስፍና ነበር፡፡

 ‹‹ሥጋ መመገብ እያደከመኝ ነበር፡፡ ከዚያም ያነብኩትን ነገር በራሴ ላይ ለመመልከት ራሴን መከታተል ጀመርኩኝ፤›› የምትለው ፀደይ ኦሾ ሥጋና አትክልት ተመጋቢ ስለመሆን ባለው ነገር ላይ ሳትወሰን ሌሎች ፍልስፍናዎችን፣ ሳይንሳዊ ጥናቶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ጭምር በማንበብ አትክልት ተመጋቢ ለመሆን መወሰኗን ትናገራለች፡፡ ከንባቧ የደረሰችበት ነገር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሁኔታ ሥጋ ተመጋቢ እንዲሆን ሳይሆን አትክልትና ፍራፍሬ እንዲመገብ ዲዛይን የተደረገ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያም በአንድ ጊዜ ሳይሆን፣ ደረጃ በደረጃ ሥጋ ልታቆም ቻለች፡፡

እንደ ሒንዱይዝምና ቡዲዝም ያሉ የምሥራቁ ዓለም እምነቶች አትክልት ተመጋቢ መሆንን ያበረታታሉ፡፡ በሒንዱይዝም አትክልት ተመጋቢ መሆንን አመፀኛ ካለመሆንና ከመንፈሳዊነት ጋር ይያያዛል፡፡ መንፈሳዊ መሠረቱ እንደሚያይል ግን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ፀደይ ካነበበቻቸው ደግሞ መካከል የሒይንዱይዝም መርህ አንደኛው ነው፡፡

እሷ እንደምትለው በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት እንደ እሷ ዘወትር አትክልት ተመጋቢ ለሆኑ ሰዎች የምርጫቸውን ምግብ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህም ያደረገችው አትክልት ተመጋቢ መሆንን የሚያበረታቱ እምነቶችና ፍልስፍናዎች የሚመክሯቸው የአመጋገብ ሥርዓቶችን በመከተል የራሷን ምግብ ማዘጋጀትን ነው፡፡ ሥጋ ባለመብላቷ የምታጣውን ፕሮቲን ለመተካት አዘውትራ ከምትመገባቸው መካከል የባቄላ በቆልት ይገኝበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአትክልት ተመጋቢዎች ምግብ ብቻ የሚያዘጋጁ ቤቶች እንዲሁም መደበኛ አትክልት ቤቶች ብቅ ብቅ ማለት እንደ ፀደይ ላሉ የምርጫቸውን ማግኘት ቢያስችሉም ዋጋውም የዚያኑ ያህል በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት እየጨመረ መሆኑን እንደታዘበች ትናገራለች፡፡ እንደ ጉድለት የምትጠቅሰው ዋጋን ብቻ ሳይሆን የምግብ አቀራረቡንም ነው፡፡ ‹‹የተለያየ ቀለም ያላቸው አትክልቶች መደባለቅ መልካም ቢሆንም መደባለቃቸው የማይመከር በጣም ጣፋጭና ጎምዛዛ አትልክቶችና ፍራፍሬዎች አሉ፤›› የምትለው ፀደይ ለአትክልት ተመጋቢዎች ብቻ ምግብ ከማቅረብ በዘለለ የምግቦቹ አቀራረብ የተጠና ሊሆን እንደሚገባ ታሳስባለች፡፡

ለምን ሥጋ መብላት እንዳቆመች የሚጠይቋት ብዙ ናቸው፡፡ በውሳኔዋ ለመቀለድ የሚሞክሩም አጋጥመዋታል፡፡ ሥጋ ማቆም እየፈለጉ አለመቻላቸውን የሚገልጹላትም አሉ፡፡ በተቃራኒው ሥጋ ብቻ ሳይሆን እንደ እንቁላል፣ ዓይብና ቅቤ ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ጭምር የማይመገቡ (Vegan) ሰዎችም አሉ፡፡

የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆነው ኤባ ተስፋዬ ቬጋን የመሆን ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ይህን ማድረግ ማኅበራዊ ሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በማመን አትክልት ተመጋቢ (Vegetarian) ብቻ ለመሆን ወስኗል፡፡ ሥጋ አቁሞ ይህንን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲመርጥ ያደረገው ዋነኛው ነገር ጤናማ የአኗኗር ዘዬ መፈለግ ቢሆንም የሚከተለው እምነት (የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት) ተፅዕኖም እንዳለበት ይገልጻል፡፡

‹‹ሥጋ ተመራጭ በሆነበት በእኛ ማኅበረሰብ ሠርግና ልደትን በመሰሉ ዝግጅቶች ተገኝቶ ሥጋ አልበላም ሲባል ሰው ግራ ይገባዋል ምን ልስጥ ብሎም ይጨነቃል፤›› የሚለው ኤባ እንደ እሱ ላሉ ተጋባዥ መሆንም ችግር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹ልጋብዝህ ብሎ የምበላው አትክልት ነው ሲባል ግብዣው ዝቅ የተደረገበት የሚመስለው ሰው ብዙ  ነው፤›› ይላል፡፡

እንደ ፀደይ ኤባም ሥጋ አቁሞ አትክልት ተመጋቢ መሆንን ከሃይማኖ፣ ከሳይንስና ከሥነ ልቦና አንፃር ይመለከተዋል፡፡ አትክልት ተመጋቢ መሆኑን እንቅስቃሴ ማድረግን ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ ነገሮች ይደግፈዋል፡፡ አመጋገብ ከሰው ልጆች ስሜት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የሚተነትኑ አሉ፡፡ አንዳንድ የአመጋገብ ዘዬዎች ሰዎች በስሜት ያልተረጋጉ እንዲሆኑ ሲያደርጉ መረጋጋትን የሚፈጥሩ የመስከን ስሜቶችን የሚያሳድሩም መኖራቸው ይገለጻል፡፡ ሥጋ ተመጋቢ መሆን ከመጀመርያው፤ ሁለተኛው ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ ከመሆን ጋር እንደሚያያዝ ይገለጻል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ የሆኑ እንደ ሒትለር ያሉ ሰዎች መኖር ደግሞ ጥያቄ እንዲያነሱ የግድ ይላል፡፡

ኤባ እንደሚገልጸው ከሥጋ ውጭ የሆኑ ምግቦችን ማግኘት ለሱና አትክልት ተመጋቢ ለሆኑ ብቻ ሳይሆን ለማንም አስቸጋሪ ነው፡፡ ትኩረት ተሰጥቶት በሚገባ የሚሠራው ሥጋ በመሆኑ ነው ይህ የሆነው፡፡ ይህ የሚፈልጉትን ዓይነት ምግብ በሚፈልጉት መልኩ ማግኝት አስቸጋሪ መሆኑ ላይ የፀደይን ሐሳብ ኤባም ይጋራል፡፡ ፀደይም እቤት ውስጥ እያዘጋጁ መመገብን እንደ አማራጭ ስታስቀምጥ ኤባም ይህንኑ ለማድረግ የምግብ ዝግጅት በመሠልጠን ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡

የእነሱ ዓይነት የምግብ ምርጫ ያላቸውን ሰዎች በተለይም ቬጋን የሆኑትን የመቀበል ነገር በማኅበረሰቡ አሁንም ገና እንደሆነ ያምናል፡፡ ‹‹ሥጋ አልበላም ስንል ምንድነው ታዲያ የምትበሉት? ብሎ የሚጠይቀው ሰው ብዙ ነው፡፡ ከሥጋ ውጭ ምግብ አለ ብሎ የማያምን ብዙ ነው፤›› ይላል፡፡ ሥጋ በተለያየ መንገድ ሊሠራ ቢችልም በትክክል ብዙ አማራጭ ያለው በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ሥነ ልቦና ላጠናው ኤባ አትክልት ተመጋቢ መሆን ከሥነ ልቦናና ከስሜት ጋር አለው የሚባለውን ግንኙነት በራሱ ተሞክሮ አጢኖት ከሆነ ጥያቄ አቅርበንለት ነበር፡፡ ‹‹ሥጋ ያቆምኩት በአሥራዎቹ መጨረሻ እያለሁኝ ስለነበር በዚያ ጊዜ አመጋገቤ ከስሜቴ ጋር የነበረውን መስተጋብር አላስተዋልኩትም፤›› በማለት ነገሩን በራሱ እንዳላየው ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ብዙዎች አካላዊ ብርታትንና ብቃትን ሥጋ ተመጋቢ ከመሆን ጋር ቢያያይዙትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ራሱን ሥጋ ተመጋቢ ከሆኑ ጓደኞቹ ጋር በማነፃፀር ብርቱዎች እንደ እሱ ያሉ አትክልትና ፍራፍሬ ጥራ ጥሬም ተመጋቢዎች እንደሆኑ ይደመድማል፡፡

የቬጋን ምግቦች ብቻ የሚዘጋጁበት ቦሌ አካባቢ የሚገኝ ላቪንግ ሀት (Loving hut) የተሰኘ ሬስቶራንት ነው፡፡ የሬስቶራንቱ ግቢ በር ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ የመሆን ጥቅሞች ተዘርዝረው በትልቁ ተለጥፈዋል፡፡ የሬስቶራንቱ ሜኑም ከምግብ ዝርዝሮች በተጨማሪ የቬጋን ምግብ ጠቀሜታዎችን የሚዘረዝር ገጽ ያለው ነው፡፡  

ምንም እንኳ ምሳ ሰዓት የነበረ ቢሆንም ቤቱ ጭር ያለ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ግርግርም የሚታይበት አይደለም፡፡ በርካታ የቬጋን ምግቦች በቤቱ እንደሚዘጋጁ የሜኑ ዝርዝር ያሳያል፡፡ ቤቱ ከተከፈተ አንድ ዓመት ሊሞላው ቢሆንም እንደ ንግድ ሲታይ ትርፋማ አለመሆኑን የሬስቶራንቱ ማናጀር አቶ እዝራ ፍስሀ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ የብዙ ሰው ምርጫ ሥጋ በመሆኑ ነው የሚለው እዝራ መጀመርያም ቤቱን ሲከፍቱ የገበያ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አውቀው እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ከሆነ ትርፋማ ላይሆን እንደሚችል እየታወቀ እንዴት ወደ ሥራ ተገባ? የሚል ጥያቄ ለአቶ እዝራ አቅርበን ነበር፡፡ ‹‹የጀመርነው እንደ ንግድ ከትርፍ አንፃር ብቻ ሳይሆን ቬጋን መሆንን ከማስፋፋት አንፃር ነው፤›› የሚል ነበር መልሱ፡፡ ከመጀመርያዎቹ ጊዜያት ዛሬ ላይ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ቤቱ ሰው አለው የሚያስብል ነገር አለመኖሩን ይገልጻል፡፡

አቶ እዝራም እንደ ኤባ ሁሉ በተለይም ቬጋን መሆን ሥጋ ተወዳጅ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ፈታኝ ነው ይላል፡፡ እሱም ቬጋን ነው፡፡ ይህን የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ከጀመረ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የጤና ጠቀሜታው እንዲገፋበት ቢያጠናክረውም የእሱም ቬጋን የመሆን መሠረት የእምነት ፍልስፍና ነው፡፡ ‹‹አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ መሆን ተፈጥሯዊና ትክክለኛው የኑሮ ዘዬ ነው ብዬ አምናለሁኝ፤›› ይላል፡፡

እሱ ቬጋን በመሆኑ ሥጋ ብቻም ሳይሆን እንደ እንቁላል፣ ዓይብና ቅቤ ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችንም አይመገብም፡፡ ይህ ደግሞ በማኅበራዊ ግንኙነቶቹ በተለያየ መንገድ ነፃ እንዳይሆን እንዳደረገው ይገልጻል፡፡

ያነጋገርነው ሌላ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ ወጣት ሥጋ መመገብ ካቆመ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የእሱም ውሳኔ በምሥራቁ ዓለም ክፍል የእምነት ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እንደ እሱ ላሉ ውጭ ምግብ ማግኘት ችግር መሆኑ ላይ ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያለው፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ መጀመርያ ላይ ቤተሰብ ሐሳቡን ለማስተው ይሞክሩ ነበር፡፡ ይህ እንደማይሆን ሲረዱ ግን ከሥጋ የሚያገኘውን ነገር መተካት የሚያስችሉትን ምግቦች በማዘጋጀት ይተባበሩት ጀመር፡፡ እንደ እሱ ዓይነት የምግብ ምርጫ ያደረጉ ሰዎች ሥጋ ለማቆም ከመወሰን ባሻገር በጥንቃቄ ምግባቸውን በመከታተል ሥጋ ባለመብላት የሚያጡትን ነገር መተካት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ብዙ ሰዎች ሥጋ አለመመገብ በረዥም ጊዜም ቢሆን ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚል አስተያየታቸውን በተደጋጋሚ ሲያንፀባርቁ አድምጧል፡፡ እሱ ግን በዚህ አይስማማም፡፡ በቅርቡ አሞት ሐኪም ጋር ሄዶ በነበረበት አጋጣሚ የአመጋገብ ሥርዓቱ ምናልባት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጤናው ላይ ተፅዕኖ ካሳደረ ብሎ ሐኪሙን መጠየቁን ይናገራል፡፡ ሐኪሙ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለው ገልጸውለታል፡፡

የሥርዓተ መግብ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃን ፍቅሩ ማንም ሰው የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዳለበት አጽንኦት በመስጠት አትክልትና ፍራፍሬ ብቻውን እንደ ዋና ምግብ መታየት እንደማይቻልም ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ከሥጋ ሊገኝ የሚችለውን ፕሮቲንና ሌላም ንጥረ ነገር የእህል ዘሮችን ከጥራጥሬም በመመገብ መተካት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም ሥጋንና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን የማይመገቡ ምግባቸው የተመጣጠነ መሆኑን እስከተከታተሉ ድረስ ሥጋ አለመመገባቸው በራሱ ችግር እንደማይሆን ያስረዳሉ፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...