የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞችንና የታዛቢዎችን ክፍያ አላጠናቀቃችሁም ላላቸው በርካታ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ቀነ ገደቡ እስከ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የነበረ ቢሆንም፣ ክፍያውን ባለመፈጸማቸው ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ሌላ እሳቤ ለታኅሳስ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ማዘዋወሩንም ገልጿል፡፡ ይህን በማይፈጽም ክለብ ላይም ከከፍተኛ የብሔራዊ ሊግ ውድድር የሚያስባርር ዕርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማስጠንቀቂያ እንደ አንዳንድ የስፖርቱ ቤተሰቦች አስተያየት፣ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል›› በሚል ብሂል በተደጋጋሚ ለሚያጋጥሙት ችግሮች የራሱ አደረጃጀትና የአካሄድ አለመጣጣም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ ማሳሰቢያ፣ በዚህ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ እንዲወዳደሩ የመረጣቸው 32 ቡድኖች ናቸው፡፡ ይሁንና እነዚህ በከፍተኛ የብሔራዊ ሊግ ፉክክር ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑት አብዛኞቹ ቡድኖች በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተሟላ አቅም ያልፈጠሩ መሆናቸው እየታወቀ በማያዛልቃቸው የፋይናንስና የአደረጃጀት ተሞክሮ በቀጥታ ወደ ውድድሩ እንዲገቡ ማድረግ የችግሩ መሠረት ስለመሆኑ ጭምር የስፖርቱ ቤተሰቦች ይገልጻሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ወንድምኩን አላዩ ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በዚህ በከፍተኛ ሊግ ውስጥ ለመወዳደር የተመዘገበ እያንዳንዱ ክለብ ለዳኞችና ታዛቢዎች ክፍያ መክፈል የሚጠበቅበት ዝቅተኛው 300,000 ብር ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊው፣ ይህን አስተያየት እስከሰጡበት ድረስ ክፍያቸውን ያጠናቀቁ ክለቦች 22 ብቻ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ክፍያውም ባለመፈጸሙ ምክንያትም ታኅሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. መጀመር የነበረበት የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ዓመታዊ ውድድር፣ ወደ ታኅሳስ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲዘዋወር ስለመደረጉም ተናግረዋል፡፡
እንደ ስፖርቱ ቤተሰቦች ደግሞ አብዛኞቹ የክልል ቡድኖች ዓላማ በክልልና በዞን መካከል ያለውን ፉክክር ለማስቀጠልና ተወካይ ላለማጣት ብቻ በሚመስል መልኩ መዘጋጀታቸው ቀጣይነት የሌለው ተሳትፎ እንደማያመጣ እየታወቀ ፌዴሬሽኑ በቸልተኝነት ወይም ባልተገባ የተሳትፎ መብት ለከፍተኛ የብሔራዊ ሊግ እንዲበቁ ማድረጉ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ችግሩ የክለቦች ብቻ ሳይሆን የፌዴሬሽኑም ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡