Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የዳኝነት ክፍተቱን እያየን አካሄዱን መጠበቅ አላስፈለገንም››

‹‹የዳኝነት ክፍተቱን እያየን አካሄዱን መጠበቅ አላስፈለገንም››

ቀን:

አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ

ከጥንካሬያቸው ይልቅ ክፍተት ጎልተው ከሚታዩባቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በእግር ኳስ ዳኞች ላይ በወሰደው የዕገዳ ውሳኔ ምክንያት የሳምንቱ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል፡፡ ታኅሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ደደቢትንና ኢትዮጵያ ቡናን በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ቡና ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዕድል ሽረዋል›› በሚል የፌዴሬሽኑ ዳኞች ኮሚቴ የዳኞችንም ሆነ የጨዋታ ታዛቢ ዳኛን ሪፖርት ሳይጠብቅ በዋና ዳኛው ላይ የአንድ ዓመት የዕገዳ ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው አድርጓል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም በፌዴሬሽኑ ላይ ጫናና ትችት በርትቷል፡፡ ብዙዎች የዳኝነት ጥፋቱ የተፈጸመው ኢትዮጵያ ቡና ላይ በመሆኑ እንጂ፣ ደጋፊ በሌላቸው ክለቦች ላይ ቢሆን ኖሮ አንድ ዓመት አይደለም ማስጠንቀቂያ እንኳ አያሰጥም ነበር በሚል ውሳኔውን በመቃወም ላይ ይገኛሉ፡፡ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው በበኩላቸው በውሳኔው ተገቢነት አንዳችም ጥርጣሬ እንደሌላቸው ሆኖ ቅጣትና ዕገዳ ግን መፍትሔ እንደማይሆን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶም የእግር ኳስ ዳኝነት ቅጽበታዊ ውሳኔዎችን የሚሻ እንደመሆኑ ጥፋቶችን መቀነስ ካልሆነ ፍፁም የሚባል የዳኝነት ሥርዓት ግን አሁን አይደለም ወደፊት እንደማይኖር ግን ይከራከራሉ፡፡ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከእግር ኳስ ዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚታዩ አለመግባባቶች ከወትሮው የተለየ መልኩ እየተስተናገደ ነው፡፡ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆንዎ ለዚህ ምክንያት የሚሉት ይኖራል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- የተጨዋቾች ንክኪ በሚበዛበት እግር ፍፁም የሆነ ነገር መጠበቅ እስከዛሬም የለም ወደፊትም ይኖራል ብለን አንጠብቅም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የእግር ኳስ ዳኝነት በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ የታጀበ በመሆኑ የተነሳ ምንም ዓይነት ኮሽታ ሳይፈጠር ማስተናገድ ስለሚከብድ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በኢትዮጵያ የሊግ ውድድር ላይ ብቻ የሚከሰት እንዳልሆነ፣ ይልቁንም በእግር ኳስ ደረጃቸው በላቁ አገሮች ሁሌም እንደምንመለከተው ጉልህ የሆነ የዳኝነት ስህተቶች ይታያሉ፡፡ እኛም ጋ የሚስተዋሉት ችግሮች የዚሁ ነፀብራቆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ስህተቶችን መቀነስ ካልሆነ ፍፁም የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል እግረ መንገዴን ለመግለጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ደደቢትንና ኢትዮጵያ ቡናን በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ላይ የተጣለባቸው ዕገዳ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ሁለት ዓይነት አመለካከቶችን ማስተናገድ ጀምሯል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ውሳኔው ተገቢና ትክክልም ነው፡፡ ምክንያቱም ዕገዳው የተላለፈበት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ራሱ ውሳኔውን በፀጋ እንደሚቀበለው ነው የነገረን፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዴት እንደተሳነው ራሱን በመውቀስ ጭምር ነው የተናገረው፡፡ ምክንያቱም ዳኝነት ምንም እንኳ ቅጽበታዊ ውሳኔን የሚሻ እንደመሆኑ ዳኛው በተላለፈበት ውሳኔ መፀፀት እንደሌለበት፣ ይልቁንም በቀጣይ በተሻለ በራስ መተማመንና ብቃቱን አዳብሮ መምጣት እንደሚጠበቅበት ጭምር ፌዴሬሽኑ ነግሮታል፡፡ እሱም ተቀብሎታል፡፡

ሪፖርተር፡- በእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ ውስጥ ያለፉ በመሆኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ላይ ለተላለፈው የዳኝነት ስህተት መነሻው ምንድነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- በእግር ኳስ ዳኝነት የጎንዮሽ ዕይታ (ዲያጎናል ሲስተም) የሚባል እንቅስቃሴ አለ፡፡ በዚህን ጊዜ አንድ የመሀል ዳኛ ማድረግ የሚገባው በተለይ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ፍጥነቱን ቀንሶ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በሚገባ ተመልክቶ ሊቆጣጠር የሚችለበት ቦታ ላይ መገኘት ይጠበቅበታል፡፡ ዳኛው ከመሀል ሜዳ በመጣበት ፍጥነት ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሚገባ ከሆነ፣ እያንዳንዱን ድርጊት ቅርበት ላይ ስላለ ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ለእንቅስቃሴው ቅርብ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ቦታው ላይ ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን ወስዶ ሕጉ የሚፈቅድለትን ውሳኔ መስጠት የግድ ይላል፡፡ እንደሚታወቀው ታላላቅ ዳኞች በተለይ የመሀል ዳኞች ፍፁም ቅጣት ምት ክልል (በሙያው አነጋገር 16.50) ውስጥ በመጡበት ፍጥነት ዘለው ሲገቡ አይስተዋልም፡፡ ከገቡም መውሰድ ያለቸባቸውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ 16.50 ቀርቶ እስከ 5.50 ድረስ ነው ሮጦ የሚገባው፡፡ ይህ እንቅስቃሴው ደግሞ ለዳኝነት ስህተት እንደሚዳርገው በግልም ተነጋግረናል፡፡ ምክንያቱም እዚያ ቦታ ላይ በእንደዚያ ዓይነት ቅርበት ሕጉ የሚያዘውን ተግባራዊ አለማድረግ ከተጠያቂነት ስለማያድን ማለት ነው፡፡ የውሳኔያችንም መነሻ ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕጉ እንደተጠበቀ ሆኖ በዕለቱ ዳኛ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ግን ከመቼም ጊዜ በበለጠ የፈጠነ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያከናወኑት እሑድ ታኅሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ውሳኔው የተላለፈው ደግሞ በማግሥቱ ሰኞ  ጠዋት ነው፡፡ በዚያ መሀል ለውሳኔ የሚያግዙ የዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኛ ሪፖርቶች አልታዩም፡፡ ለውሳኔው አነጋጋሪነት አንዱና ዋናውም ይኼው ነው፡፡ ለዚህ የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ በተገኘበት የተከናወነ ጨዋታ  ስለሆነ በታዩ የዳኝነት ስህተቶች የዳኛና ታዛቢ ዳኛ ሪፖርቶችን መጠበቅ የማያስፈልግበት ሁኔታ አለ፡፡ እርግጥ ነው ጨዋታው የክልል ከተሞች ላይ የተደረገ ቢሆን ኖሮ የዳኝነቶችንና የታዛቢ ዳኛ ሪፖርቶቹን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ውሳኔ ለማስተላለፍ ሪፖርቶች መነሻ ስለሚሆኑ ማለት ነው፡፡ ሌላው ለምን እዚህኛው ውሳኔ ላይ ትኩረት እንደተደረገ ባይገባኝም የዚህ ተመሳሳይ ውሳኔዎች ቀደም ባሉት ቀናት  ተላልፈዋል፡፡ በማሳያነት ብንመለከት የካፍ ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት ካይሮና ሱዳን ካርቱም የሚደረጉ ጨዋታዎች ተመሳሳይ ጥፋቶች ተከስተው በተመሳሳይ ቀን ውሳኔ ሲሰጣቸው አንመለከትም፡፡ የካይሮው ይፈጥናል፡፡ ምክንያቱም ጨዋታው በሚከናወንበት ሰዓትና ቦታ የካፍ የዳኞች ኮሚቴ አባላት ስለሚኖሩ ጥፋት ከተፈጸመም በአካል ተገኝተው የተመለከቱት ስለሆነ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ማስረጃ ሳይጠይቁ ነው ውሳኔ የሚያስተላልፉት፡፡ የእኛም ውሳኔ የዚሁ አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ቡና የበርካታ ደጋፊ ባለቤት በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ተፅዕኖውን ፈርቶ ነው ዳኛው ላይ አጣዳፊ ውሳኔ ያሳለፈው የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ልዑልሰገድ፡- እንደዛ ማለት ይከብዳል፡፡ እርግጥ ደጋፊ ያለው ክለብ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ሚዲያውም ቢሆን በዚህ ተፅዕኖ ሥር መግባቱን የሚያመላክቱ በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች ጉዳይን ሳምንቱን ሙሉ መነጋገሪያ የሚያደርጉ አሉ፡፡ የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ ውሳኔን ከዚህ አኳያ እንመልከተው ከተባለ በተፅዕኖ የተላለፈ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከደደቢትና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በፊት በተከናወኑ ጨዋታዎች በዳሸን ቢራ ላይ የታየውን የዳኝነት ስህተት ዓይቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከነማንና ወልዲያ ከነማ የዳኙት የመሀል ዳኛ፣ የጨዋታው ታዛቢ ዳኛና ረዳት ዳኞች ላይ የስድስት ወራት የዕገዳ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ እነዚህም በተፅዕኖ ነው ለምን አልተባለም? ደጋፊ ላላቸውም ሆነ ለሌላቸው ክለቦች ዞሮ ዞሮ ሊያግባባ የሚችል ሕግ ስላለ ተፅዕኖው እንዳለ ሆኖ ሕግና ሥርዓት ሲጓደል ዝም ማለትን አልመረጥንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ ዳኛ ጥንካሬም ይሁን ድክመት የመጨረሻው ተደርጎ የሚወሰደው የታዛቢ ዳኛው ሪፖርት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ያንን የሚወስነው ጨዋታው የሚከናወንበት ቦታና ሰዓት ነው፡፡ ሆኖም የጨዋታው ታዛቢ ዳኛ ሪፖርት እንደተባለው የዳኛውን ጥንካሬም ይሁን ክፍተቱ የምንለይበት ነው፡፡ ሆኖም የዳኝነት ክፍተቱን እያየን አካሄዱን (ፕሮሲጀሩን) መጠበቅ አላስፈለገንም፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ አገሪቱን በመወከል በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ከሚዳኙ ጥቂት ዳኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ የአሁኑ ዕገዳ ይህን የአገሪቱን የኢንተርናሽናል ተሳትፎ ወደ ኋላ አይጎትተውም?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ትክክል ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኞችን ለማፍራት ብዙ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም አንድ ኢንተርናሽናል ደረጃ ላይ የደረሰ ዳኛን በሌላ ሰው ልንተካው አንችልም፡፡ ምትክ የለውም ብለን ደግሞ ሕጎች ሲጨፈለቁ ከደፈጠጡ ዝም የምንልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ውሳኔያችንም ከነበረው ሁኔታ በመነሳት የተላለፈ ነው፡፡ እንደተባለው ኢንተርናሸናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በኢንተርናሽናል ደረጃም ቢሆን የጨዋታ ዕድል አይመጣለትም፡፡ የሚገርመው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር  (ፊፋ) ቀደም ሲል ከሚታወቁት ኢንተርናሽናል ዳኞች ውጪ ለአዳዲሶች ትኩረት ያን ያህል ነው፡፡ ለማሳደግ ሰፊ ጊዜ ወስዶ ከተመለከተ በኋላ ነው ዕድሉን የሚሰጠው፡፡ ከዚህ አኳያ ጉዳት እንዳለው ይሰማናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳኛው ቀደም ሲል ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው ታግደው የቆዩ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት ደግሞ ከአገሪቱ ትክልልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ምደባው ላይ ትኩረት መደረግ እንደነበረበት ይደመጣል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- በአሁኑ ወቅት በኢንተርናሽናል ደረጃ ትልቅ ስም ካላቸው ዳኞቻችን ውስጥ የመጀመርያው ባምላክ ተሰማ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኃይለ ኢየሱስ ባዘዘው ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምናገኘው ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴን ነው፡፡ ካፍም ምደባ ሲስጥ ይህንኑ ደረጃና ብቃት እየተመለከተ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢንተርናሸናል ዳኛ ለሚ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ጥፋት ታግደው ነበር የሚባለው ትክክል አይደለም፡፡ ለዳኛው የተሰጣቸው የቃል ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ እስካሁንም የተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮችን ዳኝቶ ምስጉን ተብሎ የተመሰገነ ነው፡፡ ሌላው ለዕለቱ ጨዋታ ባምላክን እንዳንመድብ ኢትዮጵያ ቡና ቀደም ብሎ ለፌዴሬሽኑ ባስገባው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጋቸው ማናቸውም ጨዋታዎች ባምላክን በዳኝነት እንዳይመደብባቸው ስለጠየቁ ነው፡፡ ኃይለ ኢየሱስ ደግሞ ከዕለቱ ጨዋታ ቀደም ባሉት ቀናት ጨዋታ መርቷል፡፡ የነበረን አማራጭ ለሚ ብቻ ነው፡፡ ለዚያም ነው የመደብነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክለብ ስለጠየቀ ብቻ ጥያቄውን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ከሙያዊ ሥነ ምግባር አኳያ ይቻላል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- በሙያ ደረጃ አይቻልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ለዳኛውም ሲባል የተሻለውን አማራጭ እንወስዳለን፡፡ ያደረግነውም ያንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀደም ባሉት ዓመታት እንስት ዳኞች ጨዋታውን በብቃት ሲመሩ እናስታውሳለን፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ሴቶች የወንዶችን ጨዋታ መዳኘት አይችሉም በሚል ተከልክለዋል ለምድነው?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ትክክል ነው፣ አሁንም አሉ፡፡ ግን ምድነው ፊፋ አዲስ ያወጣው መስፈርት አለ፡፡ ያንን መሥፈርት አሁንም ካሟሉ መዳኘት ይችላሉ፡፡ መሥፈርቱ ለወንድ ወይም ለሴቶች ተብሎ አልተቀመጠም፡፡ አንድን ከፍተኛ ሊግ ሊመራ የሚችል ዳኛ ይህን መሥፈርት ማሟላት ይኖርበታል ስለሚል ብቻ ነው፡፡ ይህ መሥፈርት ባለበት ያላሟሉ ሴቶችን መድበን ጥፋት ቢፈጠር ጣጣው የባሰ ነው፡፡ ያን ጊዜ ተጠያቂው ዳኛው ሳይሆን መዳቢው አካል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...