Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመመርመር ፈተና

የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመመርመር ፈተና

ቀን:

በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተንሰራፍቶ መኖሩ የተገለጠ ሃቅ ነው፡፡ ከብሩንዲ እስከ ደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያ እስከ ሊቢያ፣ ከኮንጐ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ እስከ ናይጄሪያ በየአቅጣጫው በየዕለቱ የምንሰማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ብዙ ናቸው፡፡ ምርጫን ተከትሎ፣ የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ በሥልጣን ሽግግር መካከል፣ በእርስ በርስ ጦርነት የሚታዩት ረገጣዎችና ጥሰቶች የአፍሪካ መገለጫ መሆናቸው ሊቀር አልቻለም፡፡ በአገራችንም በተለያዩ ጊዜያት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሪፖርት ካደረጉ ሰዎች ሲነገሩ፣ በውጭ የመገናኛ ብዙኃን ሲዘገቡ እንሰማለን፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ የነበረው ሁከትና ግርግር፣ በጋምቤላ ክልል ተፈጥሮ የነበረ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ፣ በጅማ አካባቢ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከቅርቡ ሊጠቀሱ የሚችሉት ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን የሰዎች ሞት፣ ድብደባ፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የንብረት መውደም የቀረልን አይመስልም፡፡ በአማራ ክልል በጭልጋ ወረዳ በአማራና በቅማንት ብሔረሰብ መካከል የነበረው ግጭት፣ በጎንደር ማረሚያ ቤት የተነሳ የእሳት ቃጠሎን ተከትሎ የታራሚዎች ሞት፣ ከአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ብጥብጥ የሰሞኑ ትኩሳት ነበር፡፡ አኃዙ ግራ ቀኙን ባያስማማም ሰዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፤ ንብረቶች ወድመዋል፣ ትምህርትና ሥራ ቆሟል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሊገለጽ የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚኖር ማንም የማይክደው ነው፡፡ በታራሚዎች ላይ የተኮሰ፣ ንጹኃንን የገደለ፣ የሕዝብና የመንግሥትን ንብረት ያወደመው ማን ነው? የሚለው ተጣርቶ ዕርምጃ ካልተወሰደ ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ መኖር፣ ስለ ነፃነት፣ ስለ አካል ደኅንነት ወዘተ. መናገር ትርጉም አይኖረውም፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ጽሑፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምንነትን፣ ጥሰት የመመርመር ግዴታ ያለበትን አካል፣ የምርመራውን ጥቅም፣ ዘዴውን፣ መርሆቹን በአጭሩ በመዳሰስ፣ የምርመራን ፈተናዎች ለማስቃኘት ያሰብነው፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምንድን ነው?

የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ሰነዶች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ‹‹Human right violations›› ወይም ‹‹Human rights abuses›› በማለት ይገልጹታል፡፡ ሁለቱም ሰዎች ሰው በመሆናቸው በተፈጥሮ ያገኙዋቸውን መብቶች የመንጠቅ፣ ያለአግባብ የመገደብና የማሳጣትን ሁኔታ ያመለክታሉ፡፡ ጥሰት (Violation) የሚለው ከ‹‹Abuse›› የጠበበ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በመንግሥት አካላት የሚፈጸሙትን የሚያካትት ከመንግሥት ውጭ በሆኑ አካላት (non-state actors) የሚፈጸሙትን እንደማይጨምር መግባባት አለ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ለሥልጠና ባዘጋጀው ሰነድ ‹‹Human rights violations›› include government transgressions of the rights guaranteed by national, regional and international human rights law and includes acts and omissions directly attributable to the state involving the failure to implement legal obligations derived from human rights standards” በሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥትና ተቋማቱ በብሔራዊ፣ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ዋስትና ያገኙትን ሰብዓዊ መብቶች ባለማክበር፣ ወደጎን በማድረግ፣ በመገርሰስ ወይም ማድረግ ያለበትን ሳያደርግ ከቀረ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት እንችላለን፡፡ በሕግ፣ በፖሊሲ ወይም በዳበረ ልማድ የተቀመጡ መብቶችን አለማክበር፣ ዋስትና የተሰጣቸውን ጥበቃዎች ዋጋ ማሳጣት፣ መንግሥት የማክበር፣ የመጠበቅና የማሟላት ግዴታውን ካልተወጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት ያስችላል፡፡ ለአብነት ፖሊስ ያለአግባብ ከደበደበ፣ ካሰቃየ፣ ከገደለ፣ ንብረት ካወደመ፣ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሷል ለማለት ይቻላል፡፡ በጎንደር፣ በጭልጋ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተፈጸሙት ድርጊቶችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሆን አለመሆናቸው ሊጣራ ይገባዋል፡፡ አጥፊው፣ የተጣሰው መብት፣ የወደመው የንብረት ግምት፣ ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች፣ ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሔዎች ወዘተ. ሊጣሩ ይገባል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥሰት የመመርመር ግዴታ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም አለመፈጸሙን፣ ከተፈጸመ የጉዳቱን መጠን፣ የፈጸመውን አካል ኃላፊነትና ለተጎጂው ሊሰጠው የሚገባውን መፍትሔ (Remedy) የማጣራት ግዴታ በዋናነት የመንግሥት ነው፡፡ ሦስት ዓይነት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተለይ ከባድና በስፋት የሚፈጸሙትን ጥሰቶች የማጣራትና ያጠፉትን ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን ይደነግጋሉ፡፡ የመጀመሪያው ከወንጀል ሕግ ጋር የተያያዙ ስምምነቶች በግልጽ መንግሥት የዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ከሰብዓዊነት የሚቃረኑ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎችን የመክሰስና የመቅጣት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋሉ፡፡ ለአብነት የ1949 የጄኔቫ ኮንቬንሽንን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በአንቀጽ 146 ‹‹The High contracting parties shall be under the obligation to search for persons alleged to have committed or to have ordered to commit such grave breaches (war crimes) and shall bring such persons, regardless of their nationality, before its own courts…›› ሲል መደንገጉ ለዚህ ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ማረጋገጥና ማክበር (ensure and respect) የሚሉ በብዙ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የሚገኙ ድንጋጌዎች መንግሥት ቢያንስ በራሱ ፍርድ ቤት ሰብዓዊ መብት ጥሰትን መርምሮ አጥፊውን ሊቀጣ እንደሚገባው ይደነግጋሉ፡፡ ሦስተኛው በሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች መንግሥት መፍትሔ ‹‹Remedy›› ሊሰጥ እንደሚገባው በመግለጽ የተቀረጹ ድንጋጌዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መርምሮ አጥፊውን እስከማስቀጣት የሚደርስ ነው፡፡ ለአብነት ሁሉ ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ (UDHR) ብንመለከት በአንቀጽ 8 ‹‹Every one has the right to an effective remedy  by the competent national tribunals for acts violating the fundamental rights granted him by the constitution or by law›› ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመመርመርና መፍትሔ የማፈላለግ ግዴታ በዋናነት የመንግሥት እንደመሆኑ መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤት ወዘተ. እንዲያጣራው የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥት ከዘገየ ወይም ፈቃደኛ ካልሆነ ወይም ጎን ለጎን ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ግን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ምርመራውን ያከናውናሉ፡፡ በአገራችን ሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ) አከናውነዋለሁ እንዳለው ማለት ነው፡፡

ጥሰትን የመመርመር ጥቅሞች

ሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመከታተል፣ የመመርመርና የመመዝገብ አምስት ጥቅሞችን ይዘረዝራል፡፡ የመጀመሪያው የተሠሩ፣ የጠፉ፣ የተደበደቡ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ዕርዳታ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ የት እንደሚገኙ ለማወቅ፣ ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊም ከሆነ የግል ነፃነትን ወይም አካልን ነፃ ለማውጣት አቤቱታ (Habeas corpus) ለማቅረብ ይረዳል፡፡ ሁለተኛው መፍትሔ ለመፈለግ ያስችላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመረምርና የሚዘገብ ከሆነ ጥፋተኛው ለሕግ እንዲቀርብና የተበደሉ ወገኖች በፍርድ ቤት መፍትሔ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ጥሰቱ ሳይታወቅና መፍትሔ ሳያገኝ ተዳፍኖ አይቀርም፡፡ የተጎዳ ሰውም ካለ ሕክምና እንዲያገኝ ምርመራው ይረዳል፡፡ ሦስተኛው የምርመራ ጥቅም መንግሥት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር አጣጥሞ የሚለውጣቸው ወይም የሚያሻሽላቸው ሕግጋትና ልማዶች ካሉ እንዲስተካከሉ አስተያየት ለመስጠት ያስችላል፡፡  ትክክለኛ መረጃ፣ ያልተዛቡ ግኝቶችና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ግንዛቤ ያስገቡ ምርመራዎች ለሕግና ለፖሊሲ ለውጥ መነሻ ይሆናሉ፡፡ አራተኛው ጥቅም ምርመራውን ተከትሎ በሕግ አስፈጻሚ አካላት ውስጥ የሚገኙ ተገቢ ያልሆኑ ጠባዮችን ለመለወጥ ያስችላል፡፡ ሕግ አውጪዎች፣ ፖሊሶች፣ ዳኞች ወዘተ. ስለሰብዓዊ መብት ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር ያስችላል፡፡ የመጨረሻው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መመርመር ጥቅሙ ኅብረተሰቡ እንዲነቃ፣ ጥሰትን እንዲቃወም ብሎም ለመከላከል እንዲችል ያደርገዋል፡፡

የምርመራ ዘዴዎች

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ተቋማት የተለመዱ ሦስት ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ዘዴዎች አሉ፣ እነርሱም ክትትል (Monitoring)፣ ሐቅ ፍለጋ (Fact Finding) እንዲሁም ምልከታ (Observation) ናቸው፡፡ እነዚህ ዘዴዎች ዓላማቸው ሁሉንም የሚያስማማ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርመራ አከናውኖ እውነቱን ማፈላለግ ነው፡፡ ‹‹Monitoring›› የሚለውን ትርጉም ‹‹A broad term describing the active collection, verification and immediate use of information to address human rights problems›› በሚል ይተረጉሙታል፡፡ የሰብዓዊ መብት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል መረጃን በፍጥነት የመሰብሰብ፣ እውነትነቱን የማረጋገጥና ወዲያውኑ ለጥቅም የማዋል ዘዴ ነው፡፡ ይህ ዘዴ ስለ ግጭቶች መረጃ መሰብሰብ፣ ክስተቶችን (ምርጫ፣ የፍርድ ቤት ሙግት፣ ሰላማዊ ሠልፍ) መታዘብ፣ የእስር ቤቶችንና የስደተኛ ጣቢያዎችን መጎብኘት፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና ሌሎች አካላት ጋር መወያየት፣ መረጃ ማግኘትና መፍትሔ መፈለግን ያጠቃልላል፡፡ ሁለተኛው ‹‹Fact finding›› ሲሆን ‹‹describes a process of drawing conclusions of fact from monitoring activities›› በሚል የሚገልጹት ክትትሉን መነሻ በመድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን በተመለከተ ተአማኝ የሆነ መደምደሚያ መስጠት ነው፡፡ ከክትትል ጠበብ ያለ ወሰን ያለው ሲሆን፣ አንድ ተፈጸመ የተባለን ኩነት (የሰብዓዊ መብት ጥሰት) በተመለከተ መረጃ መሰብሰብ የመረጃውን ታማኝነት ማረጋገጥና ስለ ጥሰቱ መደምደሚያ ላይ መድረስ ነው፡፡ ‹‹Observation›› የምንለው ‹‹more passive process of watching events such as assemblies, trials, elections and demonstrations›› በቅርብ ሆኖ የሰብዓዊ መብት ክትትልን ስብሰባን፣ የፍርድ ቤት ሒደትን፣ ምርጫንና ሰላማዊ ሠልፍን በመታዘብ መረጃ የሚሰበስብበት ዘዴ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተጓማጋቹ ድርጅት (Human Rights Watch) እነዚህን ሦስት ዘዴዎች በስፋት በመተንተን ስለ መረጃ አሰባሰብ፣ ምንጮቹን፣ ቃለ መጠይቅ አደራረግ ወዘተ. ሰፊ ማኑዋል አዘጋጅቷል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመረምር አካል በዝርዝር በዳሰሰው ጠቃሚ አካሄዶችን ያገኝበታል፡፡

የምርመራ መሠረታዊ መርሆች

የሰብዓዊ መብት ምርመራን የሚያከናውን አካል ሊከተላቸው የሚገቡ አራት መሠረታዊ መርሆች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ትክክለኛ መረጃን መፈለግ አለበት፡፡ እውነታን እንጂ ሀሜትን፣ ስማ በለው ወይም የአንድ ወገን መረጃ ብቻ መሠረት ማድረግ የለበትም፡፡ ሁለተኛው ሚስጥር መጠበቅ ነው፡፡ ማንኛውም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በማጋለጥና መረጃ በመስጠት የተሳተፈ ሰውን ያለፈቃዱ ማንነቱን ይፋ አለማውጣት ተገቢ ነው፡፡ ሦስተኛው ገለልተኛነት ነው፡፡ ማንኛውም ምርመራ አንድ የተወሰነን አጀንዳ ለማራመድ፣ በብሔር፣ በጾታ ወይም በፖለቲካ አመለካከት መድልኦ የሚያደርግ ሊሆን አይገባም፡፡ በመጨረሻም፣ ምርመራ የሴቶች መብቶችን በተለየ ግንዛቤ በማስገባት ሴቶች እንዳይረሱና የተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተለይቶ እንዲመዘገብ የሚያስችል ምርመራ መሆን ይገባዋል፡፡

የሚገጥሙ ፈተናዎች

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ሥራ በመንግሥትም ይሠራ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ሥራ ነው፡፡ በመንግሥት በሚሰየም ገለልተኛ ቡድን የሚመራ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ሥራ ከመንግሥት ከራሱ፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተለያዩ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ የሁሉም ፈተናዎች ቁንጮ ከላይ የዘረዘራቸውን መሠረታዊ መርሆች ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነው፡፡ እውነተኛና በመረጃ የተደገፈ ሪፖርት አለማቅረብ፣ ሚስጥር ካለመጠበቅ የተነሳ መረጃውን የሰጡት ሰዎች ላይ ጫና እንዲደርስ ምክንያት መሆን፣ ገለልተኛነትን ከአጣሪው ቡድን አመራረጥ ጀምሮ በአሠራሩ፣ መረጃ አሰባሰቡና ሪፖርት አደራረጉ ለማረጋገጥ አለመቻል በዋናነት የሚስተዋሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡

የምርመራ ሥራውን የሚያከናውነው አካል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ከሆነ ግን ችግሮቹ ከዚህም ይሰፋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ከተሟጋች ቡድኑ እኩል ገለልተኛ አጣሪ ቡድንም ላይ ሊስተዋሉ ይችላሉ፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች እነዚህን ፈተናዎች በደምሳሳው በሰባት በመክፈል መነሻቸውንና መፍትሔያቸውን ይጠቁማል፡፡ የመጀመሪያው ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመመርመር የሚሳተፉ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦቻቸው በምርመራው በመሳተፋቸው ገቢያቸው ሊቀንስ ወይም ገቢያቸውንም ሊያጡ ይችላሉ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ ፈቃድ ሊከለከሉ ይችላሉ፣ ሥራቸውን ሊያጡ ይችላል፣ ከፍተኛ ግብር ሊጣልባቸው ይችላል፤ የሥራ ዕድሎች ሊዘጉ ይችላሉ ወዘተ. ሁለተኛው ፈተና ከሕግ ሥርዓት መጠንከር ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም የሚችል አጣብቂኝ ነው፡፡ የመሰብሰብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚጋፉ ሕግጋት መኖር፣ የሕዝብ ደኅንነትን መነሻ ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን የሚከለክሉ ወይም የሚገድቡ ሕጎችና አሠራሮች መኖርና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጉን እንደተመቻቸው የሚለውጡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሦስተኛው፣ ያልተገባ ስያሜ ወይም ስም የማጥፋት ሥራ ሊኖር መቻሉ ነው፡፡ በምርመራው የያዘው አቋም ያልተንፀባረቀለት የመንግሥት አካል፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ወይም የሲቪል ማኅበረሰብ በምርመራው ለተሳተፉ ሰዎች ያልተገባ ስም በመስጠት የሚያሸማቀቁበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አራተኛው፣ መርማሪው በምርመራው ሒደት በሚሰማቸው አሰቃቂ እውነታዎች ሥነ ልቦናው ሊጎዳ የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ አምስተኛው፣ መርማሪውን ከሎጂስቲክ ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ መረጃ ለማግኘትና ሕዝቡን ለማናገር እንዲሁም መረጃውን በአግባቡ ለመመዘገብ የትራንስፖርት ችግር፣ ካሜራና ኮምፒዩተርን የመሰሉ ጥሬ ዕቃዎች አለማግኘት እንዲሁም ሕዝቡን ለማግኘት አመቺ መሠረተ ልማት አለመኖር የተወሰኑት ናቸው፡፡ ስድስተኛው፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት መረጃ የሚሰበሰብ አካል የፈለገውን መረጃ፣ ሰው ወይም ቦታ ላያገኝ ይችላል፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች መረጃ ባለመስጠት፣ ተጠቂ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ምስክሮች በፍርኃት እንዲሁም ጥሰቱ የተፈጸመበትን ቦታ ለማየት አለመመቻቸት መረጃ ለማግኘት ፈተና ይሆናሉ፡፡ የመጨረሻው ግን በተግባር ተንሰራፍቶ የሚገኘው ዋናው በሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ሥራ የሚሳተፍ ሰው የሚያጋጥመው ፈተና ከራሱ፣ ከቤተሰቡ ወይም ባልንጀራው ላይ ያነጣጠረ የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት ወይም የነፃነት ሥጋት ነው፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በተንሰራፋበት አፍሪካ ጥሰቱን እንደማጣራት ፈታኝ ሥራ አይኖርም፡፡ ከላይ ካየናቸው አንዱ ወይም የተወሰኑት ወይም ሁሉም ለማጣራት በተሰየሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወይም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡ አገራችንም ከዚህ የተለየ ምስክርነት የሚያሰጥ ታሪክ ያላት አይመስልም፡፡ ከዚህ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ የተካፈሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አንዳንዱ ከአገር ሲሰደድ፣ አንዳንዱ ጫና እንዳደረበት ሲናገር፣ አንዳንዱ ሪፖርቱ ሕዝባዊ ተቀባይነትን ሳያገኝ ሲብጠለጠል አስተውለናል፡፡ ቀጣዩስ ምን ይሆን? የተገደሉት፣ የቆሰሉት፣ የተሰደዱት፣ ንብረታቸው የተዘረፈባቸው ሰዎች ጉዳይ ተጣርቶ ጥሰቱ ይታረም ይሆን? ያጠፉት (ካሉ) ይቀጡ ይሆን? አገራችን ነገ የምትመልሰው የቤት ሥራ ነው፡፡   

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

   

             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን አገርን የሚጠቅምና ሕገወጥነትን የሚነቅል ሆኖ እንደ አዲስ ሊቀረጽ ይገባል!

ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንድትገባ ካደረጓት የተለያዩ...

የኢትዮጵያ ከአጎአ የገበያ ዕድል መታገድ በኢንዱስትሪዎች ላይ ያስከተለው ጉዳት

የአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2000 መገባደጃ ላይ ያፀደቀው የአፍሪካ ዕድገትና...

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ - ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ...