በአሰፋ አደፍርስ
ይህች አነስተኛ ማስታወሻ ልጽፍ ያነሳሳኝ አገራችን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ሀብት የታደለችና ምንም ቀረሽ የማትባል አገር ብትሆንም፣ ሕዝቧ ከዓመት ወደ ዓመት ችግረኛና ሁሌም ተመፅዋች፣ የአገሮች ሁሉ የበታች ሆናለች፡፡ በዚህ ምክንያት ከልቤ ሳዝን ከኖርኩኝ በኋላ አገሬን ዞሬ ከቀድሞውም በበለጠ ለመገንዘብና የተሰማኝን ለወገን ለአገር በመላ ለማስታወቅ፣ እኔን የሚቆጨኝ ሁሉንም እንዲቆጨውና ከወሬ ይልቅ ለሥራ፣ ከመመቀኛኘት ይልቅ ወደ ቀናነት፣ በበላውና በጠጣው ብቻ በቃኝ ብሎ መቀመጥ ሳይሆን፣ አገሬ ባላት የተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ሀብት የሚገባትን ያህል ተጠቅማና ልጆቿን ጠቅማለች ወይ? ካልሆነስ ለምን? ብሎ ራሱን ጠይቆ እንዲነሳሳና በቀና መንፈስ ለራሱ፣ ለወገኑና፣ ለአገሩ ጭምር ሠርቶ በኢንዱስትሪ የተራመዱት ዓለማት ወደ ደረሱበት እንዲደርሱ ለማበረታታት ነው፡፡
ይህንን ሐሳብ ሳወጣና ሳወርድ ለብዙ ዘመናት ከቆየሁ በኋላ በማሰብ የህልም ሩጫ መሮጥ ብቻ ሳይሆን፣ ታጥቆ መነሳት እንዳለብን በመገንዘብ ለጥናት ተዘጋጅቼ ተነሳሳሁ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ሲጉላላብኝ የነበረውንም ሐሳቤን በጹሑፍ ለማስቀመጥና ወገኖቼን ለመቀስቀስ ወሰንኩ፡፡ ይህንን ስልም ያሰበና በጉዳዩ የተቆጨ የለም ማለቴ ሳይሆን፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይሳካና ሳይሞላላቸው ቀርቶ ይሆናል በማለት ነው፡፡ አገሬ ምንድን ጎድሏት? ሕዝቧ ለምንድነው የተራበው? ምንድን ጎድሏት ነው ሁሌ ዓመት ቆጥረን ወደ ዓለም አቀፍ የልመና ኮሮጆ ይዘን በማስተዛዘን የምንራወጠው? ወጣት ትውልድ፣ አዛውንት አባትና እናቶች ለዕለት ጉርስና ለዓመት ልብስ በልመና ተሰማርተው በውርጭና በሐሩር ተቃጥለው ሳያልፍላቸው ኖረው የሚያልፉት? የሚል ሐሳብ ሲጉላላብኝ ከሦስት አሥርት ዓመታት አልፏል፡፡ ታዲያ ይህንን ጉዳይ እንዴት ልመልስ እችላለሁ ብዬ ራሴን ከጠየቅሁኝ በኋላ፣ ቀደም ሲል ከማውቀው የበለጠ ለማወቅ የአገሬን ወራጅ ወንዞችን፣ ደለሎቿን፣ ምንጩንና፣ ለም አፈሯን፣ አባጣውንና ጎርባጣውን በየፈርጁ ለማየትና ለማገናዘብ ወስኜ ተነሳሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ ስወስን ኢትዮጵያን ዳር እስከ ዳር ከልጅነቴ ጀምሬ ባውቅም በማስተባበር ለመገመት እንዲያመቸኝ በዘመናዊ አዕምሮዬ ለማገናዘብ በመወሰን የአገሬን ዳር ድንበሯን ካካለልኩኝ በኋላ ለምን ተቸገርን? ለምንስ ተራብን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ወስኜ ተነሳሁ፡፡ የእኔና የእርስዎ በልቶ ማደር ብቻ በቂ አይደለምና፡፡ አገራችን በሁሉም የበለፀገች ሀብታም አገር መሆኗን ለመግለጽ አሁን ተዘጋጅቼያለሁ፡፡
የታሪክ መሠረታችን ከሆነችው ከጥንታዊቷ የኢትዮጵያ እምብርት ከሆነችዋ አክሱም ብናነሳስ? ምናልባት አክሱም ለእኛ ምናችን ነች የሚሉ ወጣቱንም ምናችሁ ናት የሚሉ ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የታሪክ አተረጓጎም ሊሆን ወይም ያለማገናዘብ ሊሆን ይችላል ብዬ ከማለፍ ሌላ፣ አክሱም የእኔም የእናንተም የኢትዮጵያዊ ሁሉ ብለን በኢትዮጵያዊነታችንና በአንድነታችን ተባብረንና አብረን ሁሉንም ለመቋቋም መነሳሳት አለብን፡፡ የዚያ ነች የዚህ ነች የሚለው የትም ሊያደርሰን ስለማይችል፣ የአንድነታችንን ዓርማ ሳንዘነጋ የአብሮነትን ዜማ ብናዜም ነው ውጤት ልናመጣ የምንችለውና ለአንድነታችን ቅድሚያ እንስጥ፡፡ ምንም የሌላቸው ፒራሚድን (ሰው ሠራሽ ተራራ) ብቻ ይዘው በችሎታቸው በመጠቀም፣ ሌሎቹ ደግሞ የአራዊት መንጋ በሀብትነት በመጠቀም የቱሪስትን ፍላጎት በመሳብ ብቻ ከለሙት አገሮች ጌታ ተሠልፈው የሚኖሩ አሉ፡፡ ከልመና ርቀው ምንም ሳይሸማቀቁና ከሁሉ እኩል ሆነው አገራቸውን አስከብረውና ኮርተው ይኖራሉ፡፡ እስራኤላዊያን ለብዙ ዘመናት እየተንከራተቱ እንደ ባርያ ሲቆጠሩ ኖረው ነፃነታቸውን በዛሬዋ ታላቋ አሜሪካ ዕርዳታ ቢያገኙም፣ አገራቸውን ከበረሃነት ወደ ገነትነት በቆራጥነትና ተግቶ በመሥራት ከራሳቸውም አልፈው ለሌላም ለመትረፍ መብቃታቸው እጅግ የሚያስደስትና ታላቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ታላቅነት ነው፡፡
እነሱ ቆርጠው በመሥራታቸው አገራቸውን በማይታመን ሁኔታ ለውጠው አልፈው ተርፈው የተቸገረን መርዳር ሲችሉ በሕዝብ ብዛት፣ በመሬት ቆዳ ስፋትና በተፈጥሮ ሀብት እንደ አፍሪካ ያልታደሉ ሆነው ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ሁሉ ለተረፈን እጃቸውን ለዕርዳታ ሲዘረጉ፣ ዓለምንም በጥበባቸውና ከኃያላን በሚያገኙት ዕርዳታ ተጠናክረው በታላቅነት ታውቀውና ተከብረው መኖር ሲችሉ፣ የስካንድኔቪያን አገሮች በረዶውንና ቁሩን ተቋቁመው ራሳቸውን መቻል ብቻ ሳይሆን ለሌላውም መትረፍ ሲቃጣቸው፣ የእኛ ይህንን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ተጠቅመን ከችግር ተርታ የማንወጣበት ምክንያት ጨርሶ ሊታየኝ አልቻለም፡፡ ትናንትና በኢኮኖሚ ከእኛ በታች የነበሩት እንደ እነ ኮሪያ ያሉት አገሮች በቴክኖሎጂ ተራቀው አገራቸውን ከችግር ነፃ ለማድረግ በተጧጧፉበት ዘመን፣ ትናንት በቅኝ ገዥዎች ተይዘው ይሰቃዩ የነበሩት አፍሪካዊያን ወገኖቻችን ዛሬ ሊቀድመን ሲውተረተሩና ለልማት ሲሽቀዳደሙ፣ እኛ ነባሮቹ ባለንበት እየረገጥን ኖረናል፣ አሁንም አለን፡፡ አለን ማለት አይቀርምና እኛ ግን ከተፈጥሮ ሀብትም ሌላ የቱሪስት ሀብት ያለን ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ለምሳሌ ግብፅ በፒራሚዷ ብቻ የዓለምን ዓይን ስባ ከእኛ አሽቆልቁሎ በሚወርደው ዓባይ ወንዛችን እንደ አንጡራ ንብረት የዓባይ ንጉሥ ተብላ የዓለምን ጎብኝዎች ዓይን ስትስብ፣ በዓባይ ላይ የመርከብ መዝናኛ አዘጋጅታ ጎብኝዎችን እያንሸራሸረች ለመስኖ ብቻ ሳይሆን የጎብኝዎችን ቀልብ መሳቢያና የገቢ ምንጭ ስታደርግ፣ እኛ ግን ነባሩን ተረት ‘የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው’ እያልን ተቀምጠናል፡፡ በውኃችን ተጠቅማ የጥጥ ምርት ላኪ ሆና ተጋርተን አብረን እንጠቀም ከማለት ይልቅ፣ በየጊዜው ልታስፈራራን ስትሞክር ቆይታለች፡፡ በአጭሩ ወንዞቻችንን ተጠቅመን ከችግር እንውጣ ለማለት እንጂ፣ እኔ የፖለቲካ ሰው ሆኜ ፖለቲካውን ለመቃኘት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ኬንያ በዱር አራዊት ሀብትና ከእኛ በማይመጣጠን የሰብልና የቡና ምርት ብቻ የዓለምን ዓይን ስትስብ፣ በዓለም የሌሉትን የአዕዋፍባ፣ የዱር እንስሳትን ዘር ጠንቅቃ የያዘች፣ በክርስትና እምነቷ ቀደምት ከመሆኗም በላይ በየትኛውም ዓለም የማይገኙትን ገዳማት ከሺሕ ዓመታት በላይ ተንከባክባ ያኖረችና የኖረች አገራችን፣ የነብዩ መሐመድን ቤተሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ መጠለያ ሰጥታ ከአደጋም የተከላከለችና ለእምነታቸው የተደላደለ መሸጋገሪያ የሆነች ኢትዮጵያችን መቸገሯ ለምን ይሆን ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ፣ መልሳችን እንደሚባለው ድርቅ ይሆን? ወይስ የመሥራት ባህላችን ተፅዕኖ ተጋርዶብን ይሆን? ሠርተው የሚያሠሩ መልካም መሪዎች አጥተን ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንችል ብቻ ነው፡፡ ልመናን ዓመት ከዓመት በጀት አድርገን መሠለፋችንን በማቆምና እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ በተገቢው መንገድ መጠቀም ስንችል ብቻ ነው ማንነታችንን ማሳወቅ የምንችለው፡፡ ግማሽ ጎናችን በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ፣ ግማሽ ጎናችን እየተራቆተ አለን ብለን ለመናገር አንችልም፡፡ አሜሪካን የመሰለች ሰፊ አገር አንዱ ግዛት በበረዶ ቢጥለቀለቅ ከሌላው ግዛት በማሸጋሸግ እንኳንስ ለአሜሪካውያን ለሌላውም ተርፋ የኖረችው በአመራር ብቃትና በሕዝብ አንድነት የተመሠረተ ሲስተም ስላላት ብቻ ነው፡፡ የነበረውን የታሪክ ባለቤትነታችንንም የምናረጋግጠው፣ በእርግጥ ተባብረንና ተስማምተን ማንነታችንን መለየትና ባለን ተጠቅመንና ተደራጅተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡
ባለፈው ታሪክ ብቻ መመፃደቁ በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን ለመለወጥ ቆርጦ መነሳት የምንችለው ለእኔ የሚል ሳይሆን ለአገሬ ለወገኔ የሚል መልካም ሥራ ሠርቼ ልለፍ የሚል ጠንካራና ቆራጥ የቴዎድሮስ ዓይነት ለክብሩ እንጂ ሕንፃ ለመሥራት ያልተዘጋጀ መሪ ሲመጣልን፣ ወይም ያንን መሪ የመፍጠር ኅብረት በልቦናችን ውስጥ ሲሰርፅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ከባድ ምኞቴ ምሁራን ወገኖቼ መላ ሊመቱበት ይገባል፡፡ አንዱ ሰርቆም ሆነ ነጥቆ ሕንፃ በሠራ ቁጥር ከየት አምጥቶ ነው? እያልን ከመንሾካሾክ በይፋ ተጋልጦ ያ ልምድ ሆኖ እንዳይቀጥል መሠረት በማስያዝ መልካም አረዓያ አስተምረን ወደ መልካም መለወጥ ስንችል እንጂ፣ በሐሜትና በአሉባልታ ጊዜን ማጥፋት መቆም አለበት፡፡ ሠርቶና ለፍቶ ያደገን ግለሰብ ግን እሰዬው እንኳን ተሳካልህ ማለት እንጂ፣ ማጣጣልና ለምን አደገ ብለን የጎሪጥ ከመተያየት ይልቅ ማበረታታትና መርዳት ካልተቻለም ማድነቅ ይገባናል፡፡ ይህንን ልምድ አድርገን እንንቀሳቀስ፡፡ ሁሉም መሠረቱን ይዞ አገሩን እንዲረዳ ልምድም እንዲያካብት ከስርቆትና ከማጭበርበር እንዲርቅ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ለኢትዮጵያ እንዲያስብ ከታች ጀምረን ለማስተማር ማበረታታትና መንገድ ማስያዝ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ አስተዋጽኦ መሆን አለበት፡፡
የሕዝብ ባህል አንዴ ከተበላሸና ልማድ ሆኖ ከሰረፀ መመለሻ የለውምና አሁኑኑ እንነሳሳ፣ እንበረታታ፡፡ የኢትዮጵያን ነባር ባህሏን፣ መከባበሩን፣ መነፋፈቁን ለማጥፋት ከተሞከረ እነሆ 40 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጋጥ ወጥነት ተንሰራፋ፡፡ ደርግ የተባለ ከታሪክ፣ ከባህላችንና ከሁለንተናችን ያልተዋሀደ ባዕድ መሳይ ዱብ ዕዳ በአገራችን ሥር ነቀል የባህል ማጥፋት ዘመቻ ብሎ ተያይዞት ሳይሳካለትና ጨርሶ ሳያጠፋው ራሱ ጠፋ፡፡ ያ የጠፋውን ባህል ደግ ደጉ እንዲያንሰራራ፣ ክፉ ክፉውን ለታሪክ ጥለን በጋራ ለአገራችን ደኅንነትና ብልፅግና በርትተን መሥራት አለብን፡፡ ይህንን ሁሉ ካልኩ በኋላ ልማት፣ ልማት የምትለው ምንድነው? ብላችሁ ለምትጠይቁኝ ትንሽ ላመላክትና ጀግና የሆነ ኢትዮጵያዊ በአሉባልታ ሳይሆን፣ እንደኔ በጽሑፍ በይፋ ሕዝብ እያነበብን እንድንወያይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1920 የዛሬዋ ሳዑዲ ዓረቢያ ምን ነበረች? ዛሬ የት ነች? ዘይትና ወርቅ ብቻ አይደለም ዋጋ ያለው የተፈጥሮ ሀብት፡፡ ይታሰብበት፣ እንወያይበት፡፡ ለምን ይህንን እንዳነሳሁ ይገባችኋል፡፡ አሊያም አስረዳለሁ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ብቻ በቀን 600‚000 ሊትር ወተት ያስፈልጋታል ሊቀርብ የሚችለው 60‚000 ሊትር ወተት ብቻ ነው፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሲሆን መላውን ኢትዮጵያን ስናስብ የትየለሌ መሆኑ ነው፡፡ ምን አጥተን ነው በቂ ወተት የማናመርተው? በእንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ ሆነን በምርት ብዛትና ጥራት ወደ መጨረሻው ነን፡፡ ለምን ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ለመንግሥትም ምክር እንድንሰጥ ዕድሉ ይከፈት፡፡
ከራሳችን ተርፈን የወተት ተዋፅዖ ወደ ጎረቤት አገር ለመላክ ስንችል፣ እኛ ግን የወተት ዴቄት እያስመጣን ነው፡፡ ለምን? መሬት ነው? ውኃ ነው? የሚሠራ የሰው ኃይል አጥተን ነው? ወይስ ዕውቀት ነው ያነሰን? ይህንን መልሱልኝ፡፡ በአንድና በሁለት ሰዓታት በረራ ወይም በመርከብ ለዓረብ አገሮች ከእኛ የሚቀርብ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ የሥጋ ከብት ወይም ሥጋ ለዓረብ አገሮች ሌሎች ከእኛ የተሻለ ሲያቀርቡ የእኛ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝበት ምክንያቱ ምንድነው? ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡናችን፣ ሰሊጣችን፣ ኑጋችን፣ ሱፋችን፣ ቦለቄያችንና የመሳሰሉትን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ለምን ተሳነን? ከሁሉ በላይ ስንዴ ስንለምን አናፍርም ይሆን? አሁንም መሬት፣ ውኃ፣ ወይስ ጎልማሳ ሠራተኛ ጠፍቶ? ወይስ በመስኩ የሠለጠነ አጥተን ይሆን? የሚገርመው ነገር አትክልትና ሥጋ ሳይቀር ታላላቅ ሆቴሎች በአዲስ አበባ ከተማችን ከውጭ እንደሚያስመየጡ ታውቃላችሁ? አይገርምም? ይህንን ለማስቀረትና በአምስትና በስድስት እጥፍ ምርታችንና የገበያ ሁኔታ አያያዛችንን ለውጠን ለሥራ ተባብረን መንግሥት ፈቃደኛ ሆኖ የመመካከርና የነወያየት ዕድል ከተፈጠረ፣ ሕፃን ተሸክማ በየመንገዱ የምትለምነዋን ወገናችንን፣ ሥራ አጥቶ የሚንገላታውን ወጣት ኢትዮጵያዊ፣ ጧሪ አጥተው የሰው ያለህ የሚሉትን አዛውንት አባቶችና እናቶች ለመጦርና ለአገር ኩራት ለመሆን እንችላለን፡፡
ግን ግለኝነትን ለጊዜው ቸል ብለን አገርና ወገንን ለማስቀደም ልቦና ካለን ነው ይህንን ማድረግ የምንችለው፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ሳይሆን ዛሬውኑ ከጀመርን በአሥር ዓመታት ውስጥ ችግርን ከኢትዮጵያ ምድረ ገጽ እምደምናጠፋ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህንን ለመፈጸም የቆረጠ ከእኔ በላይ አገሬ ወገኔ የሚል ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ መንግሥት ብቻ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ እኛ ሕዝቡ ማለቴ ነው ሞክረን መንግሥት ካልተባበረ ያኔ ነው መንግሥትን ልንወቅስ የምንችለውና እኛው እንሞክር፡፡ እንገናኝ፣ የምንገናኘውም ለዚህ ለልማት ብቻ እንጂ ለፖለቲካ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ መንግሥት ከፈለገ ለወገን የሚበጀውን አብሮ መቀየስ፣ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን ማለት ይገባዋል፡፡ መጀመሪያ ምሁራን እንገናኝ፣ እንነጋገርበት፡፡ ያጠናሁትንም ጥናት ተመልከቱና የሚጨመረው ተጨምሮ፣ የሚለወጠው ተለውጦ በየአስፈላጊው ክፍል በር እናኳኳ፡፡ እርግጠኛ ነኝ በሩ ይከፈታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡