Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

ከሰለሞን ወርቁ

አገራችን በከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረችበት አጋጣሚ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በመመረጥዎ፣ ከሕዝቡ ጋርም በጋራ በመሥራት አገራችንን ከገባችበት ችግር ለማውጣት በማመንዎና ቆርጠው በመነሳትዎ በቅድሚያ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንልዎ እመኛለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በእርስዎ የሥራ ዘመን ሊያሳኳቸው ካስቀመጧቸው በርካታ ተግባራት ውስጥ ቀዳሚዎቹን በማስቀደም ተከታዮቹን በጊዜያቸው እያስከተሉ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት የጋራ መግባባት መኖር ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ ባለፉት አጭር ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ እነዚህም ውይይቶች ተስፋ ሰጪ ጭላንጭል የፈነጠቁ ናቸው፡፡ ወደ ቀና አስተሳሰብና የቀደመ ጥብቅ መስተጋብር ይወስዱናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ እኔ መረዳት በጋራ መግባባታችን ውስጥ አንኳር የሆነ ጉዳይ እንዳለ ይሰማኛል፤ ይህም ሥነ ምኅዳር ነው፡፡

በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በምንኖርበት ዩኒቨርስ ውስጥ ጤናማ የተፈጥሮና ሰው ግንኙነት በሌለበት ምኅዳር ውስጥ መልካም የሰዎች ለሰዎች ግንኙነት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የሥልጣኔ መስመራችን ከባህላችን፣ ከጥንታዊ ዕውቀታችን፣ ከልማድና እሴቶቻችን ተፋትቷል፡፡ ለዚህም ከተፈጥሮ ጋር የነበረን ጤናማ መስተጋብር ከፍተኛ አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት ዛሬ ላይ ያለን ማኅበራዊ የትስስር መስመር እንዲሰል አስገድዶታል፡፡ በዚህ መልኩ የምንቀጥል ከሆነም ወደ ቀደመው ሳይሆን ወደ ኋላ የምንመለስበት ጊዜ አጭር አይሆንም፡፡ ‹‹ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ . . . ›› እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡ የአገራችን የባህል፣ የቋንቋ፣ የእምነት፣ ጥንታዊ ዕውቀት፣ የአኗኗር ዘይቤና ማኅበራዊ እሴታችን መዳበር መሠረቱ የሥነ ምኅዳር አረዳዳችና መልካም ግንኙነታችን ውጤት ነው፡፡ በአንፃሩ ዛሬ ላይ እየመዘዝን የምናመጣው ከጥንታዊ ዕውቀታችን ጋር ማስተጋበር ያቃተን ያላለመድነው ባዕድ ባህል የቁርሾው መነሾ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ወደ የትኛውም አቅጣጫ ዕድገት ብንሻ ለሥልጣኔ ማቡኪያ ውኃ ከወንዛችን እስካልቀዳን ድረስ አንድ ጋት ወደ ፊት፣ ሺሕ ወደ ኋላ ስንመለስ እንቀጥላለን!!!          

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት በአገራችን ፖለቲካዊ ትኩረት የተነፈገው ነገር ግን በእጅጉ አገራዊ መግባባትን ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዋነኛው ነው፡፡ ሥነ ምኅዳር እንዲያስገኝልን ከምንጠብቀው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በላቀ መልኩ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ “ፖለቲካዊ ትኩረት” ለሚለው ሐሳብ መጠቁም ይሆን ዘንድ ክልላዊ አስተዳደር አከላለልን መነሻ አድርገን ስንመለከት ሰባት ብሔራዊ ፓርኮች ከሁለት በላይ በሆኑ ክልሎች ተዋስነው የሚገኙ ሲሆኑ፣ አራቱ ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ ፓርኮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ አሥራ አንዱ ብሔራዊ ፓርኮች ድንበር ተሻጋሪ የሆኑት ከሌሎች አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ሲኖራቸው፣ በክልሎች መካከል የሚገኙትም የቀደመ ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ትስስራችንን በማደርጀት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ቀሪው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን፣ የዓለም ቅርስ በመሆን የተፈጥሮን ከአንድ ማኅበረሰብ ሀብትነት የላቀ የሰው ልጆች ሁሉ ህልውና መሠረት መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ቀጣዩ የውይይት ነጥብ የተፈጥሮ ጉዳይ መሆን እንደሚኖርበት እጠቁማለሁ፡፡          

በአገራችን የተፈጥሮ ልማትና ጥበቃ ሥራ ባሳለፍናቸው ዘመናት የተሞከሩ ጅምሮች አሁን ላይ አድርሰውናል፡፡ በየትኛውም መልኩ ወደኋላ እንመለሳለን የሚል እምነት የለኝም ወደ ተሻለ ደረጃ እንጂ፤ ምናልባትም እኔ እዚህ መግለጽ በፈለግኩት ደረጃ ሳይሆን ክቡርነትዎ አገራችን ያላትን ፀጋም ሆነ በተፈጥሮ ላይ የተጋረጠውን ሰው ሠራሽ ጫና በተሻለ ደረጃ ያውቁታል ብዬ እገምታለሁ፡፡   

ከዳሎል 110 ሜትር ከባህር ጠለል በታች እስከ ራስ ደጀን 4,543 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ የያዘች አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይህ የአየር ንብረት ተለያይነት የበርካታ እጅግ ማራኪ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ክቡርነትዎ ይህንን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ አልጠራጠርም፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሀብቷ ተጠብቆና ለምቶ ለአገራችን ዘላቂ ልማት ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ ከማመን ባሻገር የተፈጥሮ ሀብት መውደም የአንድ አገር ሥልጣኔ ቁልቁለት መውረድ ቀጥተኛ አመላካች ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካሏት 25 ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የሚተዳደሩት በወረቀት ላይ ካለው ስማቸውና በምስል ተቀርፆ ከቀረው ትዝታቸው ውጪ አገሪቱ ላይ ተፈልገው አይገኙም፡፡ በአሜሪካ የሎው ስቶን ብሔራዊ ፓርክ፣ በአፍሪካ ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ ቀዳሚዎቹ ብሔራዊ ፓርኮች ናቸው ብለን እዚህ ስንመጣ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ቀዳሚው ብሔራዊ ፓርክ ነበር እንላለን (ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አቻው መሆኑን አልዘነጋሁም)፡፡

በወረቀት ላይ ከቀሩት ብሔራዊ ፓርኮቻችን ውስጥ አዋሽ አንዱ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የመጀመርያው ብሔራዊ ፓርክ ነው (ነበር)፡፡ አቢጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአፍሪካ ካሉ የካልዴራ ሐይቆች ቀዳሚውና ሁለተኛው የሻሎ (ጰሊቃን) ወፎች መራቢያ አሁን በሕይወት አለ ለማለት ከማንደፍርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ፣ በአፍሪካ ብቸኛው ዝሆኖችን ለመጠበቅ የተቋቋመ መጠለያ፣ በዓለም ላይ ካሉ የዝሆን ዝርያዎች የዚያ ብቻ ዝርያ የሚገኝበት፣ በአገራችን በስፋቱ ቀዳሚው የዱር እንስሳት ጥብቅ ሥፍራ፣ እጅግ የሚባል አደጋ ላይ ከወደቀ ሰነባብቷል፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ በተቀናጀ መልኩ ባልተጠና የልማት ፕሮጀክት ምክንያት አደጋ ተጋርጦበታል፣ ጎረቤቱ ማጎ ብሔራዊ ፓርክም የአሳሩ ተጋሪ ነው፡፡ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ ገራሌ ብሔራዊ ፓርክና ሀላይደጌ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ ችግሮቻቸው ሥር እየሰደደ ያሉና ለነገ ህልውናቸው ዋስትና የሌላቸው ጥብቅ ሥፍራ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከ1958 ዓ.ም. ጥብቅ ሥፍራዎችን ማቋቋም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ አሁን ላይ 65 በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ጥብቅ ሥፍራዎች አሏት፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ2000 ዓ.ም. በአዲስ መልክ እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ ለዘጠኝ ጊዜ የአደረጃጀት ለውጥ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁን ባለው ቁመና የአገሪቱን አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ከስምንት በመቶ በላይ የሚያስተዳድር ተቋም ነው፡፡ ይህንን የሚያክል ትልቅ ተቋም እስካሁን ድረስ በመንግሥት ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ግን እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ የዚህን አቋም ትክክለኛነት ለማስረገጥ ከላይ ከጠቀስኩት የጽሑፍና ጥብቅ ሥፍራዎቹ በአካል ያሉበት ሁኔታን ከማሳየት የዘለለ አንዳችም ማስረጃ መደርደር እንደማያስፈልግ አምናለሁ፡፡ የችግሮቹ ስፋትና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰደው እንቅስቃሴ የማይመጣጠን በመሆኑና ከዚያም ባሻገር ዘርፉን ወደ ጎን ገፍቶ ሌሎች የዕለት ተዕለት ሥራዎች ላይ በመጠመዳችን ፍፁም መተኪያ የማይገኝለትን ለህልውናችንም ወሳኝ የሆነውን ሀብት እያጣን እንገኛለን፡፡

እርግጥ ነው የአገራችን ሁኔታ እጅግ የከፋ ሆነ እንጂ በሌሎች ጥቂት አገሮችም ለሥነ ምኅዳር የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለዚህም አሜሪካዊ የሥነ ምኅዳር ተመራማሪ አደም የተፈጥሮ ለህልውናችን መሠረት መሆን ስለማንከፍልበት ልንገለገልበት ብቻ በችሮታ የተሰጠን አድርገን ቆጥረነዋል ሲል ይገልጻል፡፡

በአገራችን የዱር እንስሳት በዘመናዊ መልክ መጠበቅ የተጀመረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) ነበር፡፡ ሥርዓቱ እስካከተመበት ድረስም አብዛኛዎቹ ብሔራዊ ፓርኮች ተመሥርተዋል፡፡ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ ግን በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1881-1906) እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የዱር አራዊትና ዕፀዋት የተፈጥሮ መልካቸውንና ቦታቸውን ይዘው በደንብ እንዲጠበቁና በከንቱም እንዳይጠፉ ማድረግ በራሱ የውበት አፍቃሪነትና የርኅራኄም ተግባር ከመሆኑም በላይ የአገሪቱም የተፈጥሮ ቅርስ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጋል”፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቃላቸው መሠረት ካወረሱን ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ እኛ ለመጪው ትውልድ ማውረስ ያልቻልናቸው በአደራ የተቀበልናቸው ሀብቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ ለዚህ የላቀ አደራ ከቃልዎ በላይ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲኖርዎና በተቋሙ የሚታየውን ጭላንጭል በተስፋ እንዲያበሩት እጠይቃለሁ፡፡

የታንዛኒያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጁሌስ ኔሬሬ ታንዛኒያ አሁን ላለችበት የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነት ደረጃ መድረስ ከንግግር ያለፈ ተግባራዊ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካ የሥነ ምኅዳር አጠባበቅ ሥርዓት ዛሬ ላይ ስማቸው እንደ ዓምድ የቆመ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ናቸው፡፡ ወደ ሥልጣን በመጡበት ዘመን ከፍተኛ ትኩረት ለተፈጥሮ በመስጠት አገራቸውን አሁን ላለችበት ደረጃ ማብቃት ችለዋል፡፡ ተፈጥሮን ከማድነቅ በላቀ ደረጃ ተቋርቋሪ ነበሩ፡፡

‹‹ዛፎች በራሳቸው ተፈጥሯዊ የመታሰቢያ ሐውልቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ እጆች ሊያንጿቸው ከሚችሉት የትኛውም ኪነ ሕንፃ እጅግ የላቁ፣ ይህንን ሀብት ማቆየት አለመቻል የሥልጣኔያችን ትልቅ ነውር ይሆናል፡፡›› ይህ ቴዎዶር ሩዝቬልት ከተናገሩት የሚጠቀስ ሲሆን፣ ከንግግራቸው የላቀው ተግባራዊ ሥራዎቻቸው ደግሞ በአሜሪካ የተፈጥሮ ጥበቃ ታሪክ ውስጥ እንደ መነሻ ነጥብ ተደርጎ ይወሰዳል፤ 1894 ዓ.ም. ገደማ፡፡  

በአገራችን የዘመናዊው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ይህንን ሀብት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በተለያየ ደረጃ ውሳኔዎች ሲተላለፉ መቆየታቸው ዕሙን ነው፡፡ አብዛኞቹ ማለት በሚያስችል መልኩ ይተላለፉ የነበሩ ውሳኔዎች ፖለቲካዊ ጠቀሜታን በማስቀደም ላይ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡ በተፈጥሮ ላይ ፖለቲካዊ ጠቀሜታን በማስቀደም የሚወሰድ ውሳኔ ደግሞ የአንድን አገር ፖለቲካዊ ሥርዓት አለመረጋጋት ጠቋሚ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም የሚወሰዱት አማራጮች ዘላቂ ያልነበሩ በመሆናቸው ለፖለቲካዊ መፍትሔነት የሚረዱት ለአጭር ጊዜ ዕፎይታ ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነበር፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! በዚህ ወቅት አገራችን በአረንጓዴ ልማት እየታተረች ባለችበት ጊዜ የዱር እንስሳት ጥብቅ ሥፍራዎችን በተሻለ ደረጃ ማልማት በየዓመቱ ችግኝ ለመትከል ከሚደረገው ርብርብ እጅግ የላቀውን ድርሻ እንደሚወስድ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አዲስ የምናለማውም የነበረውን ለማጥፋት እንዳይደል አይካድም፡፡ ያም ቢሆን እንኳ ከንቱ ልፋት ስለሚሆን በቅድሚያ ያሉንን ሀብት በመጠበቅና በተሻለ መልኩ በማልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባን አሳስባለሁ፡፡ ለዕለታዊ ዕፎይታ ሲባል ዛሬ የምንወስዳቸው ዕርምጃዎች ፍፁም ሊተኩ የማይችሉ የተፈጥሮ ሀብት ውድመትን ያስከትላሉ፡፡ በአንፃሩ ግን በአጭር ጊዜ ጠንካራ አሠራር ዘላቂ ልማት ማምጣት ስለሚያስችል የቀሩንን ጥብቅ ሥፍራዎች ማልማት ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ክቡርነትዎ በእርስዎ የሥራ ዘመን ይህ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ወደ መልካም ደረጃ እንዲሸጋገር እጠይቃለሁ፡፡ ለዚህ ዘርፍ ፈር መያዝ የበኩልዎን ለመወጣት የላቀ ሥራ ይጠበቅብዎታል፡፡ የተሳካ የሥራ ዘመን ይሁንልዎ!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles