Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሞዴል አሽከርካሪዎች

ሞዴል አሽከርካሪዎች

ቀን:

አቶ ሀብታሙ ተሻገር ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በአሽከርካሪነት ከተሰማሩ ከ28 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ 25 ዓመቱን በከባድ ጭነት ማመላለሻ፣ እንዲሁም ለሦስት ዓመታት ያህል ደግሞ በመደበኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ በዚህ የረዥም ዘመን አገልግሎታቸው አንድም አደጋ አለማድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ሀብታሙ በአሁኑ ጊዜ የየኛ ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ 2-ለ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር አባል ሆነው በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ድርጅት ከተቀጠሩ ሰባት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በ28 ዓመት የሹፌርነት ሙያቸው ከአደጋ ነፃ ሊሆኑ የቻሉት በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሠርክ ጠዋት ከመኝታቸው ሲነሱ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ለመንዳት የሚያስችላቸው አቋም ላይ መሆናቸውን ጤንነታቸውን ይፈትሻሉ፡፡

የድካምና የመሰላቸት፣ የመጨናነቅና የመነጫነጭ፣ የመፍዘዝም ስሜቶች ካሉባቸው ከማሽከርከር መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ተሽከርካሪያቸው አጠገብ እንኳን እንደማይደርሱ ይናገራሉ፡፡

ምክንያቱም እነዚህን የመሳሰሉና ሌሎችም በድብርት ስሜት ውስጥ ሆኖ ማሽከርከር እንቅልፍ ስለሚያስከትል ተሽከርካሪውን በሚገባ እየተቆጣጠሩ ለማሽከርከር፤ ከፊትም ሆነ ከበስተኋላ የሚመጣውን ሌላ ተሽከርካሪ ለማየት እንደሚያዳግት፣ ይህም ለከፋ አደጋና ብሎም ለሰው ሕይወት መጥፋት እንደሚዳርግ ነው አቶ ሀብታሙ የተናገሩት፡፡

በየወቅቱ የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና መውሰዳቸው፣ በረዳትነት ለብዙ ዓመታት መሥራታቸው፣ ከቀደሙት ሹፌሮች በቂ ልምድ መቅሰማቸውና በየወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ካለመድገምና ለመሻሻል መንቀሳቀሳቸው፣ አደጋ ከማድረስ፣ ከእንዝህላልነትና ከግዴለሽነት ስሜት እንዲያድርባቸው፣ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረጉመ ለጠንቃቃነታቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

የሥራ ባህሪያቸው ሆኖ ብዙ ጊዜ የሚያሽከረክሩት ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ደርሶ መልስ ነው፡፡ ቀደም ሲል ጂቡቲ ለመግባት ግፋ ቢል አንድ ቀን ተኩል ይፈጃል፡፡ አሁን ግን ሁለት ቀን ተኩል ይወስዳል፡፡ ይኼም ሊሆን የቻለው ከኢትዮጵያ ድንበር ጀምሮ ጂቡቲ እስከሚዘለቅ ድረስ ያለው መንገድ በመበላሸቱ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት መስመር ላይ ከባድ የጭነት መኪና እያሽከረክሩ ተልዕኮን ማሳካት ከፍተኛ የሆነ ትዕግሥትና መረጋጋትን ይጠይቃል፡፡ አለበለዘያ የተሽከርካሪው ዕድሜ በአጭሩ ሊቀጭ ንብረትም ሊወድም ይችላል፡፡

የተሽከርካሪው ሞተር ሲሞቅ ጥላ ወዳለበት ጥግ አቁሞ ማቀዝቀዝ፤ አሽከርካሪውና ረዳቱ እንዲናፈሱ ማድረግ፣ ከመሸም ጋቢና ውስጥ ባለው መኝታ አርፎ ለቀጣዩ ሥራ ቀልጣፋና ዝግጁ ሆኖ መገኘት፣ አጋጣሚን በመጠቀም መሸታ ቤት ሄዶ ከመዝናናት መቆጠብና ለመጥፎ ሱስ ተገዥ አለመሆን ለአሽከርካሪውም ሆነ ለተሽከርካሪው ደኅንነት በእጅጉ ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡

በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ሹፌር ሲባል ንብረት የሚያወድም፣ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ የሚያደርስና የኃላፊነት ስሜት የሌለው ተደርጎ ይታያል፡፡ ኅብረተሰቡ ከዚህ ዓይነቱ መጥፎ አስተሳሰብ እንዲወጣ ለማድረግ ቀጣይ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መካሄድ እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ፡፡ ሹፌሮችም በቅድሚያ ለሙያቸው አክብሮት እንዲሰጡ ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው የትራፊክ ሕግና ደንብን በማክበር፣ ከአልባሌ ቦታ ራስን በመጠበቅ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ጠንቃቃ ሆነው እስካሁን በመሥራታቸው የአሽከርካሪዎች ቁንጮ ሆነው ተሸልመዋል፡፡

‹‹ሽልማቱ በሥራዬ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኃላፊነት ስሜት እንዲያድርብኝ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አደጋን እስከ መጨረሻው እንድጸየፈው አድርጎኛል፡፡ ይኼን መሰል ውድድር ማካሄድና ፍሬያማ ውጤት ያመጡትን ሹፌሮች መሸለም በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት በመጠኑም ቢሆን እንዲቀል ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

የየኛ ድንበር ተሻጋሪ ደረጀ 2-ለ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ሎጬ እንደገለጹት፣ ማኅበሩ በየዓመቱ አሽከርካሪዎችን እያወዳደረ የተሻለ ውጤት ያገኙትን የሽልማት ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡ ውድድሩ በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው የራሳቸውን ተሽከርካሪ የሚያሽከረክሩ ባለንብረቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ተቀጥረው የሚሠሩ አሽከርካሪዎችን የተመለከተ ነው፡፡ ዘንድሮ በተካሄደው ውድድርም ከባለንብረቶች መካከል አሥር እንዲሁም ተቀጥረው ከሚያሽከረክሩ ሹፌሮች አሥር በድምሩ 20 አሽካርካሪዎች ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ በማለፋቸው የእውቅና ሠርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ለወጡ አሽከርካሪዎች ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለውድድሩም ስኬት ስድስት መስፈርቶች ተዘጋጅተው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ከመስፈርቶቹ መካከል አንደኛው አደጋ አለማድረስ ሲሆን፣ ቀጣዩ ደግሞ የተሽከርካሪዎች አያያዝና ሥነ ምግባርን ይመለከታል፡፡ የሥነ ምግባር መስፈርቱ ኮንትሮባንድ መጫን ክልከላ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

አንድ ተሽከርካሪ ችግር መንገድ ላይ ቆሞ ሲገኝ ችግሩ ምን እንደሆነ መጠየቅ መረዳዳትና በአሽከርካሪው ላይ ጂፒኤስ መግጠም፣ ጂፒኤሱ የሚያሳያቸውን ምልክቶች አለመካድና በየዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ አርኪ ውጤት ማስመዝገብ ከመስፈርቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡  

የየኛ ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ 2-ለ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር የመረጃና የትራፊክ ደኅንነት ሴፍቲ ኦፊሰር አቶ ጥላሁን ሀብተሚካኤል እንደገለጹት፣ አሽከርካሪዎች ባሉበት ጂቡቲ ድረስ በመሄድ በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠና እንደተሰጣቸው ሥልጠናውም ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን አሽከርካሪዎች በሥነ ልቦና የበቁ እንዲሆኑና በሚንቀሳቀሱባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስታውሱ የሚያደርግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በዓለም አንደኛ፣ በተሽከርካሪ ቁጥር ደግሞ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የትራፊክ አደጋ የሚከሰተውም 81 በመቶ በአሽከርካሪዎች ሲሆን፣ የቀረው 19 በመቶ ያህሉ ደግሞ በተሽከርካሪ፣ በእግረኛ፣ በመንገደኛና በሌሎች ችግሮች እንደሆነ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...