Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊዕውቅናን ለናፈቀው ጋዜጠኝነት

ዕውቅናን ለናፈቀው ጋዜጠኝነት

ቀን:

በየሽርፍራፊ ደቂቃ በተለያዩ የዓለም ጥጎች የሚከሰቱ ሁነቶችን ጋዜጠኛው ምንም ሳይቀር ከጆሮዎ በማድረስ፣ በዓይኖ በማሳየት ባሉበት ሆነው ማንኛውም መረጃ እንዲያገኙ የማድረግ ሚና ይጫወታል፡፡ በየፈርጁ የሚከናወኑ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ክስተቶች፣ በእርስ በርስ ጦርነት የሚተላለቁ ዜጎችን አሳዛኝ ገፅታ በካሜራው አስቀርቶ በቴሌቪዥን መስኮት ያስቃኝዎታል፣ በዓይነ ህሊናዎ ምስል መፍጠር የሚችል ገላጭ ጽሑፍ ቀምሮ በጋዜጣ ያስነብቦታል፣ በሬዲዮ ያስደምጦታል፡፡ ልብ ያላሉትን የታሪክ አጋጣሚ መዝግቦ በማስቀመጥ ያስደምሞታል፡፡ ያላስተዋሉትን ቁም ነገር በተለየ መነጽር አንጥሮ በማውጣት እንዲህም አለ ሊያስብልዎ የጋዜጠኛው ሙያዊ ግዴታው የልቡም ትርታ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነ የሚበታተን ትኩረቶን ይዞ ታሪኩን እንዲጨርሱ በተዋበ አገላለጽ ሊማርኮ ሰርክ ከብዕሩ ይታገላል፡፡

ዓለምን ወደ አንድ መንደር በማሸጋገሩ ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወተው ጋዜጠኝነት ሙያዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን መረጃዎችን ከሰላ አስተያየትና ትችት ጋር የማቅረብ ግብር ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ከሙያዊ ግዴታ በላይ የሆነ ተግባሩን ለማከናወን በሥራ ሰዓት ራሱን ገድቦ ሳይሆን አኗኗሩን በሥራው ቃኝቶ፣ አዋዋሉን፣ መዝናኛውን ሳይቀር መረጃ ማግኘት በሚያስችሉት ቀዳዳዎች ጋር ተጠግቶ ወሬ እያነፈነፈ ነው፡፡ እነዚህን መስዋዕትነት ሁሉ ለሚከፍልለት ለዚህ ሙያ ካሳው የሚያገኛት ከወር እስከወር የምታደርሰው ደመወዝ ሳትሆን የሕዝብ ክብር ነው፡፡ ይህም ለሥራው ዕውቅና በመስጠት ይገለጻል፡፡

በምዕራባውያን ጋዜጠኞች ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በዘመናዊ ጋዜጠኝነት ቅርፅ ላይ በተወሰነ መልኩ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ የፑሊትዘር ሽልማት ጋዜጠኛው የሚከብርበት፣ በሥራው ዕውቅና የሚያገኝበት አንዱ አጋጣሚ ነው፡፡ የዚህ መድረክ መሠረት የሆነው ሃንጋሪያዊው ስደተኛ ጆሴፍ ፑሊትዘር ወደ አሜሪካ የተሰደደው እ.ኤ.አ. በ1864 የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያበቃ አካባቢ ነበር፡፡

- Advertisement -

ፑሊትዘር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርቶ ራሱን ከፈተሸ በኋላ ነው ወደ ጋዜጣ ሥራ የገባው፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራ ካለው ጥሩ ችሎታ ጎን ለጎንም በቢዝነስ ረገድም እንዲሁ የላቀ ተሰጥኦ እንደነበረው የታሪክ ማህደሩ ያሳያል፡፡ ያለውን ድርብ ችሎታም ኒውዮርክ ወርልድና ኢቭኒንግ ወርልድ የመሳሰሉ በወቅቱ የነበሩ ትልልቅ የሚዲያ ተቋማትን በመግዛት እንደ ጋዜጠኛም እንደ ነጋዴም ሆኖ በመሥራት በአንዴ የስኬት ማማ ላይ ወጥቷል፡፡

ሙያውን ለማሳደግ በኮሎምቢያ ጋዜጠኞች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ሲያቋቁም፣ የላቀ የጋዜጠኝነት ክህሎት ያላቸውን ደግሞ በጽሑፋቸው እየተመረጡ ዕውቅናና የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙበትን የፑሊትዘር ሽልማትን አስጀመረ፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የሽልማት ፕሮግራም ኮከብ ሆኖ መመረጥ የአሜሪካ ጋዜጠኞች ሁሉ ህልም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህ የሽልማት ዘርፍ ውጪ በየአገሩ የጋዜጠኛውን የመሥራት ፍላጎት የሚያነሳሱ፣ ተሸላሚው ይበልጥ በርትቶ እንዲሠራ የሚያግዙ የተለያዩ ጋዜጠኛውን ማዕከል ያደረጉ ሽልማቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

በጋዜጣ ሥራ በኢትዮጵያ ፋና ወጊ የሆነው አዕምሮ ጋዜጣ በ1900 ዓ.ም.፣ ቴሌቪዥን በ1950ዎቹ፣ ሬዲዮ ደግሞ በ1920ዎቹ ቢጀመርም የአጀማመሩን ያህል ሙያውም ሆነ ጋዜጠኞችን በችሎታቸው ዕውቅና የመስጠት ባህሉ ይነገራል፡፡ ለጋዜጠኛው ዕውቅና የሚሰጥባቸው እንደ ፑሊትዘር ያሉ በየዓመቱ የሚካሄዱ ሽልማቶች ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የህልም ያህል የራቁ ናቸው፡፡

እንደ ኢንቫይሮመንታል ጆርናሊስት አሶሴሽን ያሉ አንዳንድ  የሙያ ማኅበራት መሰል የሽልማት ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ያደረጉት ጥረት ብዙም ሳይቆዩ ነበር በተለያዩ አጋጣሚዎች ተሰናክለው የቀሩት፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች በየግላቸው የሚያዘጋጁዋቸው ፕሮግራሞች ቢኖሩም በተበጣጠሰ ሁኔታና ድርጅታዊ አጀንዳቸውን የሚደግፉ ሥራዎችን መርጠው የሚሸልሙበት በመሆኑ የጋዜጠኛውን ችሎታ ነጥሮ የማይለካበት ለችሎታው ዕውቅና አገኘ ብሎ ደፍሮ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፡፡

በዚህ መካከል ግን ሙሉ ትኩረቱን በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያደረገ የሽልማት ሥነ ሥርዓት በየዓመቱ ለማዘጋጀት ዋይጂኤስ መልቲ ሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የጀመረው እንቅስቃሴ በበጎ ጎኑ እየታየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ጤናማ የፉክክር መንፈስን በማዳበር ለሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ እንዲተጉ ማድረግ፣ ሙያው የሚፈልገውን መንገድ በመከተል ልቆ መገኘት፣ ተሽሎ ለመዝለቅ የሚደረገውን ፉክክርና ጥረትም እንደሚያጠናክረው የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው አሻግሬ ገልፀዋል፡፡ የመወዳደሪያ ዘርፎቹም እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ (ከሁሉም ዘርፎች)

በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመገናኛ ብዙኃን ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያገለገለ/ች፣ አገር አቀፍ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለን ፕሮግራም ወይም ዘገባን ለተመልካች ወይም ለአንባቢ ማድረስ የቻለ/ች፣ የፖሊስ የአፈጻጸም መመሪያ ክፍተቶችን በመጠቆም በአገር አቀፍ ደረጀ ለውጥ እንዲያመጣ ያደረገ/ች፣ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማስፈን በዘገባዎቹ የሠራ/ች፣ ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ወራት ውስጥ ሥራዎቹን ያቀረበ/ች፣ ተቀማነቱን በኢትዮጵያ ያደረገ/ች፣ በግሉም ሆነ በሚሠራበት ተቋም ውክልና ሊወዳደር የሚችል የምትችል፡፡

የዓመቱ ምርጥ የምርመራ ጋዜጠኛ

ከግለሰብ የዘለለ ማኅበረሰብ ተኮር ችግሮች ላይ የሚያጠነጥን ዘገባ (ፕሮግራም) ያቀረበ/ች፣ የተለያዩ የቁጥር መረጃዎችንና ሰነዶችን በማቅረብ መሞገት የቻለ/ች፣ ወጥነት ያለውን (ከዚህ በፊት ያልተዳሰሰ) ጉዳይ ያቀረበ/ች፣ በማኅበረሰብ ውስጥ ያለን ማነቆ ለመፍታት የሞከረ/ች፣ ለአገር ዕድገት ማነቆ የሆኑ ምስጢራዊ መረጃዎችን አነፍንፎ ማቅረብ የቻለ/ች፡፡

የዓመቱ ምርጥ የኦንላይን ሚዲያ ጋዜጠኛ

ሰበር ዜናዎችን ማቅረብ የቻለ/ች፣ ለመረጃው እውነትነት የሚጨነቅ/ የምትጨነቅ፣ ሚዛናዊ ዘገባን ለተከታዮች ያደረሰ/ች፣ ከተከታዮቹ ጋር ወዳጃዊ ግንኙነት በድረ ገጽ የመሠረተ/ች፣ የድምፅና ምስል መረጃዎችን የሚያቀርብ/የምታቀርብ፣ ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ጊዜያት በሥራ ላይ የነበረ/ች፣ ለአገር አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ድርጅት ድረ ገጽ ሥራውን ማቅረብ የሚችል፣ መቀመጫውን ኢትዮጵያ ያደረገ/ች፡፡

የዓመቱ ምርጥ የስፖርት ተንታኝ (ጋዜጠኛ)

ቢያንስ ሁለት ናሙናዎችን ለአድማጭ (ተመልካች) ያደረሰ አልያም ለተደራሲ ያበቃ ሥራውን ለውድድር ማቅረብ የሚችል፡፡ በአገር ውስጥ ትንታኔ ላይ የጠለቀ ዕውቀት ያለው አዳዲስ መረጃዎችን በመንተራስ ተከታታይ ትንታኔዎችን ያቀረበ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎቹ በግል አልያም በፕሮግራም ስም ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡

የዓመቱ ምርጥ የፎቶ ጋዜጠኛ

      ሕይወትን፣ ተፈጥሮን፣ በድርጊት የተሞሉ ጉዳዮችን፣ በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ አስገራሚ ነገሮችን በካሜራው በመያዝ ለተመልካች ያደረሰ/ች፣ የተመጣጠነ የፎቶ ኮምፖዝሽን ያለው ሥራን ያቀረበ/ች፣ የተመልካችን ስሜት መኮርኮር የሚችል ፎቶን ያቀረበ/ች፣ ለፎቶ ጋዜጠኛ መርሆች የተገዛ/ች

የዓመቱ ምርጥ ሰውኛ ጉዳይ አቅራቢ

እውነታዊ የሆነ ተፅዕኖን ሊያመጣ የሚችል ሥራ ያቀረበ/ች፣ በሥራው የተመልካች/ተደራሲን ስሜት ማሸነፍ የቻለ/ች፣ እውነተኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችል፣ ሥነ ጽሑፍ የገለጻ አቅሙ የጎላ የሆነ (ለህትመት)፣ የዝግጅት ቴክኒኩ የላቀ የሆነ (ለኤሌክትሮኒክስ)፣ ከ30 ደቂቃ ያልዘለለ (ከዛ በላይ ከሆነ አጥሮ ለውድድሩ እንዲቀርብ ማድረግ ይቻላል)

የዓመቱ ምርጥ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ

በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ውስጥ ዝግጅቱ/ቷ ተፅዕኖ መፈጠር የታለ/ች፣ በተለይም በዘርፉ ውስጥ ያሉ አሠራሮች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሽጋገሩ ለማድረግ የጣረ/ች፣ የዝግጅቱ አቅራቢ ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ የሆነ ከማስመልከትና ከመናገር ባለፈ ራሱንም የመዝናኛው አካል ያደረገ/ች፣ ተዓማኒነት ያለውን መረጃ በቀዳሚነት ማድረግ የቻለ፣ በተከታታዮች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ፣

ምርጥ የፊውቸር ዘገባ/ፕሮግራም አዘጋጅ

ይህ የውድድር መስክ ለሁሉም ዓይነት ዘርፎች ክፍት የሆነ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በዜና፣ በስፖርት፣ በመዝናኛ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የፊውቸር ዘገባዎችን/ፕሮግራሞችን ያቀረበ/ች፣ ፊውቸሩ አንድ ዝግጅት አልያም ንግግር መነሻ ያድርግ እንጂ መዳረሻው የዝግጅቱ አልያም የንግግሩ አንድምታ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፡፡ ፊውቸሩ አዲስ መረጃን የሰጠ መሆን አለበት፡፡ የአድማጭ ተመልካቹን አልያም የአንባቢውን ስሜት ማሸነፍ የቻለ፣ ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ ያልበለጡ ቃላትን የያዘ፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ

ከ20 ዓመት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገለ፣ የአገር ዕድገትን ለማምጣት በሥራዎቹ የታገለ፣ በአገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የጎላ አሻራን ያበረከተ፣ በሥራዎቹ ለበርካቶች አርአያ የሆነ፡፡

የዓመቱ ምርጥ ዘጋቢ ፊልም

በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘጋቢ ፊልምን ያቀረበ/ች፣ አገራዊ ጉዳይን በሥራዎቹ የዳስሰ/ች፣ በሥራው ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ያስተናገደ/ች፣ የዘጋቢ ፊልም መሠረታዊ መርሆችን ማሟላት የቻለ/ች፣ የቴክኒክ ደረጃው ከፍ ያለ ዘጋቢ ፊልምን ያቀረበ/ች፣

የዓመቱ ተስፈኛ ጋዜጠኛ

ከሁለት ዓመት ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ በአድማጭ ተመልካች አልያም አንባቢያን ዘንድ መነጋገሪያ የሆነ ሥራን ያቀረበ/ች፣ ሁለት ናሙናዎችን በዓመቱ ውስጥ ከሠራቸው ሥራዎች ማቅረብ የሚችል፣ ዕድሜው ከ35 ዓመት በላይ ያልሆነ፣

የዓመቱ ምርጥ ዐምደኛ

ቢያንስ ለስድስት ወራት ዐምደኛ በመሆን ያገለገለ/ች (በተከታታይ መሆን አይጠበቅበትም)፣ ለሚያነሳቸው ሐሳቦች ሳይንሳዊና አመክኖያዊ ማስረጃዎችን ያቀረበ/ች፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በመንተራስ ጥልቅ ትንታኔ ያቀረበ/ች፣ ለአዎንታዊ አስተሳሰቦች መዳበር አስተዋፅዎ ያበረከተ/ች፣ ሚዛናዊ ሥራን ያቀረበ/ች፤

የዓመቱ ምርጥ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ፣ የዓመቱ ምርጥ የሬዲዮ ዜና አንባቢ፣ የዓመቱ ምርጥ የስፖርት የቀጥታ ስርጭት ጋዜጠኛ፣ የዓመቱ ምርጥ የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅ የመወዳደሪያ መስፈርቶቹ በዳኞች ተለይተው በቅርቡ ይፋ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በዚህ የሽልማት መድረክ ላይ ተወዳድረው ተሸላሚ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ገለልተኛ በሆኑ አካላት በዕጩነት ቀርበው ተመዝነው የሚሸለሙ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት፣ በመረጣው ተግባር ላይ፣ ከብሮድካስት ባለሥልጣን፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከሚዲያ ካውንስል፣ ከጋዜጠኞች ማኅበር፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወክሉ ግለሰቦች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የተወዳዳሪዎቹ የመመዘኛ ነጥቦችም በእነዚህ አካላት የጋራ ውይይት የሚወሰን ይሆናሉ፡፡

ይህ የሽልማት ፕሮግራም በቋሚነት በየዓመቱ እንደሚካሄድ፣ የመጀመሪያው ፕሮግራምም ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡ ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎችም ከመስከረም 1 ቀን እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የተሠሩ እንደሚሆኑ አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...