የሉሲ ዓለም አቀፍ ጉዞ ለንግድና ለባህል ኤግዚቢሽን ፕሮግራም በአይጂ ኢንተርቴይመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በውብሸት ጉታ አስመጪና ላኪ ኩባንያ የጋራ ተባባሪነት በአራት የአውሮፓ አገሮች እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
ሐሙስ ታኅሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ በኤግዚቢሽኑ የአገር በቀል ኩባንያ ምርቶችን ለአውሮፓ የንግድ ማኅበረሰብ ማሳየትና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ማስተዋወቅ ዓላማው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአይጂ ኢንተርቴይመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይስሃቅ ጌቱ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በኦሮሚያ ቴሌቪዥን አማካይነት ኮካ ኮላ ሱፐር ስታር በሚል ፕሮግራም የአይዶል ውድድር የማካሄድ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሆኑ ትዕይንቶችንና ሌሎች መስህቦችን በማቅረብ ቱሪስቶች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ፣ የውጭ ምንዛሪም እንዲገኝ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ አብራርተዋል፡፡
ዝግጅቱ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሃንጋሪ፣ ቡዳፔስት ከተማ ኤግዚቢሽን ላይ በመሳተፍ ልምድ እንዳላቸው የገለጹት በአስመጪና ላኪ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ውብሸት ጉታ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ባለ አራትና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችና ሪዞርቶች የሚገኙበት ደረጃና የሚሰጡት አገልግሎት በተለያዩ ማስተዋወቂያ ዘዴዎች ማለትም በራሪ ወረቀቶችንና ልዩ ልዩ ማሳያ ዘዴዎችን በመጠቀም ስለ አገሪቱ ገጽታ በማቅረብ ለቱሪስቶች የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀሙ የጉዞው አንዱ ዓላማ ነው ተብሏል፡፡
የመጀመርያው የሉሲ ዓለም አቀፍ ጉዞ ለንግድና ለባህል ኤግዚቢሽን ፕሮግራም መዳረሻውን ቡዳፔስት የሚያደርግ ሲሆን፣ ከሃንጋሪ በመቀጠል ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እንዲሁም በጀርመን ተከታታይ ጉዞዎችን እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ በንግድና ባህል ኤግዚቢሽኑ የጉዞ ፕሮግራም ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ቢራ አምራች ፋብሪካዎች፣ የወይን ጠጅ ፋብሪካዎች፣ የጉዞና አስጎብኝ ወኪሎች፣ የቆዳ ፋብሪካዎችና እንዲሁም ቡና ላኪዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ ፍላጎት ያላቸው ማንኛቸውም የንግድ ዘርፎችና ባለሀብቶች መሳተፍ እንደሚችሉ አቶ ውብሸት አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ነዋሪነታቸውን በቡዳፔስት ያደረጉት ዶ/ር ባሎንግ ሻንዶር ከፍተኛ ባለሀብትና የሃንጋሪ ንግድና የባህል ማዕከል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በአጋርነት አብረው እንደሚሠሩ ገልጸው፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጉዞ ፕሮግራሙና ለኤግዚቢሽኑ አጋር አካላት እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጥ ሞዴሎችንና ፋሽን ትርዒቶችን ማቅረብ በፕሮግራሙ ከተካተቱት ውስጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ የሚታወቁት አቶ ሙሉ ገበየሁ የአርቱን ሥራ በማቅረብ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሃንጋሪ ቡዳፔስት ቢጀመር ኦስትሪያን፣ ስዊዘርላንድናን ጀርመንን ለማዳረስ እንደታቀደ ተገልጿል፡፡ በቀጣይም በ20 የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ ዝግጅት ለማቅረብ እየተሠራ እንደሆነም ታውቋል፡፡ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው አራተኛው የኤግዚቢሽን ፕሮግራም ላይ ከ20 በላይ የአፍሪካ አገሮች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡