Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኳድራንት የተባለው የሎጂስቲክስ ኩባንያ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እንደሚቀላቀል ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በቢሾፍቱ በ120 ሚሊዮን ብር የማዕድን ውኃ ፋብሪካ ይከፍታል ተብሏል

አገር በቀሉ ኳድራንት ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥራ የጀመረበትን አምስተኛ ዓመት በማስመልከት ባካሄደው ሥነ ሥርዓት፣ ከዚህ ቀደም በነዳጅ፣ በጋዝ እንዲሁም በማዕድን ፍለጋና ቁፋሮ መስክ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ሲሰጥ ከቆየው የሎጂስቲክስ አገልግሎት ባሻገር በማዕድንና በአምራች ዘርፎች ውስጥ የመሠማራት ዓላማ እንዳለው ገለጸ፡፡

የኩንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲስ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ ኳድራንት ኢንቨስትመንት ከአምስት ዓመት በፊት በሎጂስቲክስ መስክ ሥራ ሲጀምር በነዳጅ ፍለጋ፣ ጥናትና ቁፋሮ ሥራዎች ላይ ለተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች፣ ከካምፕ መረጣና ተከላ፣ ሲቪል ሥራዎች፣ ግዙፍ ጭነቶች የማጓጓዝ ሥራዎችን ጨምሮ የነዳጅና የሰው ኃይል አቅርቦትን ጨምሮ የምግብ ዝግጅት ሥራዎችን ሙሉ ለሙሉ በኮንትራት በመውሰድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ፔትሮትራንስ፣ አፍሪካ ኦይል፣ ታሎው ኦይል፣ ቢኤችፒ ቢሊቶን፣ ዩፒኤስኤል፣ ፖሊ-ጂሲኤል እንዲሁም ለሩስያው ጋዝፕሮም ኩባንያ የኢትዮጵያ ተጠሪ የነበረው ጂቢፒ ግሎባል ሪሶርስ ከተባሉትና ከሌሎችም ጋር አብሮ ሲሠራ መቆየቱን አቶ አዲስ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የነዳጅና የጋዝ ፍለጋ ሥራዎች ላይ ከተሠማሩ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ጋርም በሙሉ አጋርነት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት ግን ኳድራንት ኢንቨስትመንት በመኪና ኪራይ ሥራ ለእነዚህ ኩባንያዎች አገልግሎት በመስጠት ወደ ዘርፉ መግባቱን አቶ አዲስ አስታውሰዋል፡፡ እስካሁን በመሥራት ከሚታወቅበት የሎጂስቲክስ ሥራ ባሻገር ወደ ኢንዱስትሪ ማዕድን እንዲሁም የታሸገ የማዕድን ውኃ አምራችነት ሥራ ላይ ለመሠማራት እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ሽብሩ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ፣ ኳድራንት በቢሾፍቱ ከተማ ለማዕድን ውኃ ማምረቻ የሚውል መሬት ተረክቦ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ 120 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢንዱስትሪ ማዕድን ውጤቶች አምራችነት ላይ በመሰማራት ጥሬ ዕቃዎችን በማምረት ለፋብሪካዎች ለማቅረብ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አቶ አዲስ እንደሚገልጹት ኩባንያው የሚያመርተው ውኃ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ እንደ አቶ አዲስ ማብራሪያ ኩባንያው ወደ ማዕድን ውኃ አምራችነት ከገባባቸው ምክንያቶች ውስጥ በየጊዜው ለፍጆታ የሚያውለው 120 ሺሕ የታሸገ ውኃ መጠን ነው፡፡

የአምስተኛ ዓመት ምሥረታውንና የሥራ እንቅስቃሴውን በማስመልከት በሒልተን ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት ከተገኙት መካከል የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ዋጋሪ ፉሪ የኩባንያውን ወደ ማዕድን ዘርፍ ለመግባት መዘጋጀት እንደሚበረታታ አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳ ከፍተኛ ሥጋት የተሞላበት ዘርፍም ቢሆንም፣ ሌሎች የውጭ ኩባንያዎችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡

ኩባንያው እስካሁን ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለአገሪቱ ማስገኘቱን፣ ለ500 ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡ በሒልተን በተካሄደው ሥነ ሥርዓትም፣ ኳድራንት ላለፉት አምስት ዓመታት አግዘውናል፣ አብረውን ሠርተዋል ላላቸው ባንኮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ግለሰቦች የመታሰቢያ ሽልማት አበርክቷል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች