Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትና አዲሱ ቼክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያራምዳል የተባለው አዲሱ የቼክ ክፍያ አገልግሎት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ሁለም ባንኮች በአንድ ተመሳሳይ ቼክ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም ከቀድሞ በተሻለ ዘመናዊ አሠራርን ይፈጥል የተባለው ይህ አገልግሎት፣ አሁን ይጀመር እንጂ አገልግሎቱ ይጀመራል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ወስዷል፡፡

አዲሱን አገልግሎት መጀመር አስመልክቶ ባለፈው ሐሙስ በተሰናዳ ፕሮግራም ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና አገልግሎቱ መዘግየቱን አምነዋል፡፡ ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ ከዓመታት በላይ ዘግይቶ መጀመሩም የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ አሠራሩ ለአገሪቱ የመጀመሪያ በመሆኑም በመካከል ያጋጠሙ ችግሮች ስለነበሩ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ቢሆንም ግን ሥራው አሁን መጀመሩ የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ጋር በመተባበር ጥናት በማስጠናት ለአገልግሎት ያበቃው ይህ ፕሮጀክት፣ ተግባራዊ መሆኑ ከዚህ ቀደም ቼክ ለመመንዘር ይወስድ የነበረውን ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ አሠራሩን በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቼክ ለመመንዘር ወደ አንድ ቀን እንዲያጥር እንደሚያደርግም አቶ ጌታሁን ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ነባሮቹ ቼኮች ክፍያ የሚፈጸምባቸው ደንበኛው ቼኮቹን ባንክ ለክፍያ ባቀረበና ወደ የቼክ ማጣሪያ ሥርዓቱ በባንኮቹ በገቡ ሁለተኛ ቀን ነው፡፡ አዲሶቹ ቼኮች ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ ሲውሉ ግን የማጣራትና ክፍያ የመፈጸም ጊዜው ወደ አንድ ቀን ዝቅ ይላል፡፡

አዲሱ ቼክ ተግባራዊ ቢሆንም አሁን በሥራ ላይ የቆየው ቼክ ግን እስከ ስድስት ወራት ድረስ ከአዲሱ ቼክ ጋር ጐን ለጐን እንደሚሠሩም ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የቼክ ማጣሪያ ሥርዓት ባንኮች ከደንበኞቻቸው የተቀበሏቸውን የራሳቸው ያልሆኑ ቼኮችን እርስ በርሳቸው የሚለዋወጡበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚተዳደር ሥርዓት ነው፡፡

አዲሶቹ ቼኮችና ነባሮቹ ቼኮች በቼክ ማጣሪያ ሥርዓት ውስጥ ጎን ለጎን ከታኅሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት ይሠራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ነባሮቹ ቼኮች ቀስ በቀስ በአዲሶቹ ሙሉ በሙሉ ይተካሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2016 ላይ ነባሮቹ ቼኮች በቼክ ማጣሪያ ሥርዓት ውስጥ ገብተው ክፍያ እንዳይፈጸምባቸው ይደረጋል፡፡

ጊዜው ለስድስት ወራት የተራዘመበት ዋናው ምክንያት፣ ተገልጋዩ አዲሶቹን ቼኮች እየተለማመደ እንዲሄድ ለማድረግና ባንኮቹ ያሳተሟቸውን ነባር ቼኮች ደንበኞቻቸው እንዲጠቀሙባቸው በቂ ጊዜ ለመስጠት ታስቦ ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም በዚህ ስድስት ወራት ውስጥ በሥራ ላይ ያልዋሉ የባንክ ቼኮች ከዚያ በኋላም ቢሆን ከቼክ ማጣሪያ ሥርዓቱ ውጭ ሥራ ላይ ሊውሉ እንደማይችሉም ተጠቁሟል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ እየተገበራቸው ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ አዲሶቹ ቼኮች አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈለገው የቼክ የማጣራትና ክፍያ ሥርዓትን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ አሻሽሎ ቀልጣፋና ደኅንነቱ ይበልጥ የተጠበቀ እንዲሆንና በዚህ ረገድ ያለውን ሥጋት ለመቀነስ ጭምር ነው ተብሏል፡፡ የቼክ ክፍያ ሥርዓቱ የተቀላጠፈ መሆን የሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ልውውጥ በማሳለጥ፤ በዚህም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ አዲሶቹ ቼኮች ሁሉም ባንኮች በጋራ ሆነው ያሳተሙዋቸው ናቸው፡፡ ሕትመቱም በህንድ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቼኩን በአገር ውስጥ ለማሳተም የተሞከረ ቢሆንም፣ ባለመቻሉ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ እንዲታተም ተደርጓል፡፡ ወደፊት ግን እዚሁ ለማሳተም መታቀዱንና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለዚህ ዝግጅት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡  

ነባሮቹ ቼኮችም ሁሉም ባንኮች እንዳመቻቸው ያዘጋጇቸው በመሆናቸው ወጥነት የሌላቸውና በመጠንም ሆነ በይዘት ሰፊ ልዩነት የሚስተዋልባቸው መሆኑን የሚያመለክተው መረጃ፣ በዚህ ምክንያት ቼኮቹ ለአሠራር አመቺ ያልነበሩ ከመሆናቸው ባሻገር በቀላሉ ለማጭበርበር የተጋለጡ ሆነው እንደቆዩም ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ አባ በበኩላቸው፣ አዲሱ አሠራር ለባንኮችም ሆነ ለደንበኞች ጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ ዘመናዊ አሠራርን ለማስረጽ ይረዳል ብለዋል፡፡

የአሁኖቹ ወጥ ቼኮች ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቀው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አስመስሎ በመሥራት ወይም የተጭበረበረ ቼክ በማዘጋጀት የሚካሄደው ሕገወጥ ድርጊትን ለመከላከል የሚረዱ ባህርያትንም ያካተቱ ስለመሆናቸው አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

አዲሶቹ ቼኮች ከየባንኮቹ አርማዎችና ባንኮቹ ከሚጠቀማቸው የኮርፖሬት መገለጫ ቀለማት በስተቀር በቅርጽም ሆነ በይዘት ተመሳሳይና ወጥ የሆኑ ናቸው፡፡ ቼኮች በይዘት ተመሳሳይ ከመሆናቸው በተጨማሪ ደኅንነታቸውን ለማጠናከር ሲባል ፊት ለፊታቸውን ወደ ብርሃን ተደርገው ሲታዩ ቢያንስ አንድ የዋሊያ ምሥልና “WALIA IBEX” የሚል ጽሑፍ ይታይባቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ቼኮቹ ወደ ባንኮቹ ለክፍያ ሲቀርቡ የሚነበቡት በልዩ ሁኔታ በቼኮቹ ላይ የተቀመጡ ኮዶችን (Magnetic Ink Character Recognition (MICR)) ሊያነብ በሚችል ማሽን ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች የሚስጥር ባህርያት ቼኮቹ በሕገወጦች ድርጊት ተመስለው እንዳይሠሩ ለመከላከል የሚረዱ መሆናቸውን የአቶ ጌታሁን ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ቼኮቹ የተዘጋጁት በረቀቀ ቴክኖሎጂ በመሆኑና ከዝግጅት ጀምሮ ስለቼኮቹ አጠቃቀምና ዝርዝር ጉዳዮች ለሁሉም ባንኮች ሥልጠና በመሰጠቱ በቀጣይ በባንኮች ዘንድ ያለው የቼክ ክፍያ ሥርዓት ፈጣንና ቀልጣፋ እንደሚሆን ይጠበቃልም ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ያቀላጥፋል የተባለውን ሁሉም ባንኮች በአንድ የክፍያ ካርድ መጠቀም የሚያስችላቸውን የክፍያ ሥርዓት ፕሮጀክትም በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአንድ ካርድ የሁሉም ባንክ ደንበኞች በየትኛውም ባንክ ኤቲኤሞች መጠቀም የሚያስችላቸው ይህ ፕሮጀክት ግን፣ ወደ ሥራ ይገባል ከተባለ ሁለት ዓመታት አልፈውታል፡፡ ይህም ፕሮጀክት ስለመዘግየቱ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አምነዋል፡፡ ሆኖም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች