Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና ውስብስብ ችግሮቹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እየታዩ ክርክሮችን ሲያስነሱ ቆይተዋል፡፡ በርካቶች ሕጉን ጨምሮ የፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ፣ ለፈቃድ የሚጠየቁት መስፈርቶችና አፈጻጸማቸውን ሲተቹ ቆይተዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ተቋራጮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎችም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ሲጠቅሱ ይደመጣሉ፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ‹‹የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ ዓበይት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ ለውይይት አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱ ያቀረበው ጽሑፍ፣ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከተሰናዳና ከፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች ላይ ከተደረገ ጥናት ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ጥናቱ በምክር ቤቱ የግሉ ዘርፍ ማበልጸጊያ ማዕከል አማካይነት የተካሄደ ከመሆኑም ባሻገር፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ወቅት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታዩ የሕግና የአሠራር ችግሮች ላይ ያጠነጠነ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ጥናት መሠረት ከሕግ አኳያ የሚመነጩ ችግሮች ከተባሉት ውስጥ የግንባታ ፈቃድ ሕግ በአገሪቱ ከተሞች በሙሉ በአንድ ዓይነት መንገድ እንዲተገበር ማሰቡ አንዱና ከችግሮቹ መካከል መነሻ የተደረገው ነው፡፡ ከዚህ ጎን ሕጉን ተከትሎ ፈቃድ ሰጪዎችንና ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችን ለማቋቋም የወጡ ሕጎች እርስ በርስ የሚጣረሱ፣ አንዱ ከሌላው የማይናበቡ ሆነው መገኘታቸው በግንባታ ሒደት ላይ ከሚጠቀሱ ችግሮች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ እንዲህ ያሉትን ጨምሮ ምክር ቤቱ በስፋት የጠቃቀሳቸው ችግሮች ለውይይት ቀርበዋል፡፡

የሕንፃ ፈቃድ ሥርዓት ለማስፈጸም የሚያልማቸው ግቦች የተገልጋዮችን ደኅንነትና ፍላጎት ማሟላት፣ የከተማ ውበትና ማስተር ፕላን መጠበቅ፣ የከተማ መሬትን በተገቢው መንገድ መጠቀም፣ ለአካባቢ ደኅንነት ተስማሚነትን ማረጋገጥና የመሳሰሉት መሆናቸውን ጥናቱ ይገልጻል፡፡

የግንባታ ፈቃድ ሥርዓት በሌለባቸው አሊያም በትክክል በማይሠራባቸው አገሮች የሚገነቡ ግንባታዎች የተገልጋዩን ኅብረተሰብ ደኅንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ በሃይቲ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የፈረሱትን ሕንፃዎችና ያለቁትን ሰዎች ያስታውሳል፡፡

‹‹በአንድ አገር የግንባታ ፈቃድ ሥርዓት መኖሩ ብቻውን በቂ ነው ማለት አይደለም፤›› የሚለው ይህ ጥናት፣ የግንባታ ፈቃድ ሥርዓቱ ጥሩና የሚተገበር መሆን አለበት፡፡ ጥሩ የግንባታ ፈቃድ ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ ሕንፃ ለመገንባት፣ ለማስፋፋት፣ ለማደስ አሊያም አፍርሶ ለመገንባት የሚጠየቁ መስፈርቶችን በማቀላጠፍ ለግሉ ዘርፍ በቀላሉ የንግድ ማሠሪያ ቦታ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ በመሆኑም ጥሩ የግንባታ ፈቃድ የንግድ ሥራን በማቅለል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህ አንፃር በዓለም ላይ ያሉ አገሮች ለኢንቨስትመንት ምቹነት ከሚለካባቸው መሥርፈቶች ውስጥ አንዱ የግንባታ ፈቃድ ሥርዓት ቅለት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ መመዘኛ ከ189 አገሮች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2015፣ 70ኛ ደረጃን ስለመያዝዋ ጠቅሷል፡፡ በ2016 ደግሞ ሦስት ደረጃዎችን ዝቅ ብላ በ73ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠችም ጥናቱ አስታውሷል፡፡

ጥሩ የግንባታ ፈቃድ ቀላልና ቀልጣፋ አሠራርን የተከተለ መሆን አለበት ሲባል፣ የሕንፃ ጥራትና አገልግሎት ደረጃ ይቀንስ ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባልም ይላል፡፡ ይልቁንም የፈቃድ አሰጣጡን ማቅለልና ማቀላጠፍ የሕንፃዎችን ጥራትና ለአገልግሎት ምቹነት ከማሻሻል ጋር አብሮ ሊሠራ ይችላል ይላል ጥናቱ፡፡

እነዚህን ጥቅሞች ታሳቢ በማድረግ በርካታ አገሮች የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥን በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ በመስጠት ከፍተኛ የአሠራር ማሻሻያዎችን አስመዝግበዋል፡፡ የግንባታ ፈቃድን አውቶሜት ማድረግ የተቀላጠፈ አሠራርን ከማስፈኑ በተጨማሪ ግልጽነትን በማስፈን ሙስናን እንዲቀንስ አስችሏቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአካል የመቅረብና ሰነዶችን የማቅረብ አስፈላጊነትን በመቀነስ አስተዳደራዊ ወጪንም በእጅጉ እንደሚቀንስ ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያም ከግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ግን በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ የሚገዛበት የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳለ ጥናቱ ጠቅሶ ይህም የግንባታ ፈቃድ የሚገዛበት አንዱ ሕግ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ዓ.ም. ነው፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡት ደንብ ቁጥር 243/2003 ዓ.ም. እና መመርያ ቁጥር 5/2003 ዓ.ም. ገዢ ሕጎች ናቸው፡፡ ሕጎቹ በፌዴራል የሕግ አውጪ የወጡና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ታስበው የወጡ ናቸው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥት አገር አቀፍ የምርትና የአገልግሎት ደረጃዎችን ይዋስናል ከሚለው ጋር የተጣጣመ ቢሆንም፣ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ የአፈጻጸም መመርያዎችን ጭምር በፌዴራል ደረጃ ማውጣትና በሁሉም ክልሎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ የአፈጻጸም መመርያዎች እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ እንዳይቃኙ በማድረግ ውጤታማነትን ሊቀንስ እንደሚችል ግን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማ አስተዳደሮች የማስፈጸሚያ ዝርዝር ሕጎችን ሲያወጡ የትኛው ሕግ ምንን እንደሚገዛ መለየቱ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውንም አሳይቷል፡፡ ለዚህም በምሳሌ የጠቀሰው የአዲስ አበባ አስተዳደርን ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የግንባታ ደንብና መመርያዎችን ያወጣ ሲሆን፣ በፌዴራል ከወጣው ደንብና መመርያ ጋር ያለው ግንኙነት፣ አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው? የሚለውን መለየቱ አስቸጋሪ መሆኑን ግን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የሊዝ ሕጉም አልፎ አልፎ የግንባታ ፈቃድ ጉዳዮችን የሚነካ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር የግንባታ ፈቃድ የሚገዛበት የሕግ ሥርዓት ብዙ ስለመሆኑም ጠቅሷል፡፡

ከግንባታ ፈቃድ ጋር ያሉ ችግሮችን ለማሳየት ጥናቱ ከጠቀሳቸው ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት የግንባታ ፈቃድ ሰጪ መሥሪያ ቤት ተደጋጋሚ የስምና መዋቅራዊ ለውጦች ሲደረግበት የቆየ መሆኑን ነው፡፡ ለውጦቹ ሊያሳኩ ያለሙት መልካም ዓላማ ቢኖራቸውም፣ ተደጋጋሚነታቸው ግን በተገልጋዩ ዘንድ ውዥምብር የሚፈጥር ነበር፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 17/1997 መሠረት የግንባታ ፈቃድ ሰጪ መሥሪያ ቤት የሥራና ከላይ የተገለጹት የግንባታ ሕጉ በጎ ጎኖች እንደተጠበቁ ሆነው በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ከሕጉ የሚመነጩ እንዲሁም ከሕጉ ውጭ በተለይ በአሠራር የሚከሰቱ አያሌ ችግሮች አሉት ብሏል፡፡

ከዋና ዋናዎቹ የሕጉ ጉድለቶች መካከል ሕጉ በአገሪቱ ባሉ ከተሞች ሁሉ በአንድ ዓይነት መንገድ ለመፈጸም ማለሙ አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(2)(ረ) መሠረት የፌዴራል መንግሥት የግንባታ ፈቃድ አዋጁን ማውጣቱ ተገቢ ቢሆንም፣ በፌዴራሉ የሚወጣው ሕግ አነስተኛውን መመዘኛና አጠቃላይ መዋቅር እንዲያስቀምጥ እንጂ በየደረጃውና በየአካባቢው ሕጉ የሚፈጸምበትን ዝርዝር መመርያ እንዲያወጣ እንዳልነበር ያትታል፡፡

አነስተኛ መመዘኛና መዋቅር ማስቀመጥ ማለት ክልሎችና በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ የአስተዳደር እርከኖች ከአነስተኛው መመዘኛ የተሻለ ለመደንገግ፣ አፈጻጸምን በተመለከተ የተሳለጠ አሠራር ለመከተል፣ እንደ አካባቢዎቻቸው አፈጻጸሙን ለመቃኘት፣ ወዘተ አማራጭ እንዲኖራቸው ማስቻል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለው ክፍተት መስተካከል እንደሚኖርበት ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግንባታ ፈቃድ ሕጉና የግንባታ ፈቃድ ሰጪና ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችን ለማቋቋም የወጡ ሕጎች ብዙና እርስ በርስ የማይናበቡ መሆናቸው በጥናቱ እንደ ችግር የተጠቆመ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከአዋጅ እስከ መመርያ ድረስ ያሉ ዝርዝር ሕጎች በፌዴራል መንግሥት ቢወጡም፣ የከተማ አስተዳደሮች ከሊዝ አፈጻጸም እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የግንባታ ፈቃድን የሚመለከቱ ደንብና መመርያ አያወጡም ማለት እንደማይቻል ከአዲስ አበባ አስተዳድር የሊዝ አፈጻጸም ደንብና መመርያ ተሞክሮ መረዳት ይቻላል ብሏል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ የተለያዩ ሕጎች ተበታትነው በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ እንዲቀመጡ መደረጉ የሕግ ግልጽነት ችግሮችን አስከትሏል ብሏል፡፡ እነዚህም ችግሮች የግንባታ ፈቃድ ሰጪና ተቆጣጣሪ ተቋማትን ያየን እንደሆነ በየአስተዳደሩ ራሳቸውን ችለው የሚቋቋሙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ያለውን አደረጃጀት ለምሳሌ የመንግሥት የመሠረተ ልማት ባለሥልጣን የነበረ ሲሆን፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ ደግሞ የቤቶችና መሠረተ ልማት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡ ለወረዳዎችና ቀበሌዎች ግን በግልጽ ተለይቶ የተሰጠ ሥልጣን አልነበረም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በ2002 የአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ደግሞ የመሬት፣ የግንባታ ፈቃድና የይዞታ አስተዳደር ቢሮ ተመሠረተ፡፡ ይህ ማሻሻያ በክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሥልጣን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ቢያመጣም፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ኃላፊነት ግን ያለማስቀመጡን በምሳሌነት ገልጿል፡፡

ጥናቱ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ይታያሉ የተባሉትን ችግሮች በዝርዝር ያስቀመጠም ነበር፡፡ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደት እያጋጠሙ ያሉ ዋና ዋና የሕግና የአሠራር ናቸው ብሎ በዋናነት ያስቀመጣቸው የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁ መስፈርቶች ቀዳሚ ነው፡፡ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ የሚያወጣው ወጪ፣ የሕግ ግልጽነት ችግሮች፣ ቢሮክራሲያዊና ዘገምተኛ አሠራሮች፣ የሕግና ተግባር መራራቅ፣ የፈቃድ ሰጪ ተቋማት የአቅም ችግሮችም ተጠቅሰዋል፡፡

የሕግ ተደራሽነትና ግልጽነት ችግሮች የዘርፉ ሌላው ራስ ምታት ስለመሆኑም ጥናቱ አትቷል፡፡ የግንባታ ፈቃድን የሚመለከቱ ሕጎች ብዛታቸው ቀላል ያለመሆኑ ያስታወሰው ይኸው ጥናት ዋናው አዋጅ፣ ደንብና መመርያ በፌዴራል ደረጃ የወጡ ቢሆንም በከተማ አስተዳደር ደረጃ የወጡ የሊዝ ደንቦች፣ መመርያዎችና ሌሎች የመስተዳድር አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች የግንባታ ፈቃድ ጉዳይን ይመለከታሉ፡፡ እነዚህ ሕጎች ሁሉ በአንድ ላይ ተሰባስበው የተቀመጡ ቢሆኑ ኖሮ ቢያንስ ችግሮችን ማቅለል እንደነበር ያመለክታል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግን አንድ ላይ ያለመገኘታቸውን ጠቅሷል፡፡ በተለይ ብዙዎቹ መመርያዎች የማይታወቁ ሲሆን፣ መቼ እንደሚወጡ፣ ማን እንደሚያወጣቸው፣ መቼ አንዱ ተሽሮ ሌላው እንደሚወጣ፣ የት እንደሚገኝ ስለማይታወቅ ፈቃድ ጠያቂዎች አንዱ ለአንዱ በመደዋወል ነውም ብሏል፡፡

ተገልጋዩ በሥራ ላይ ያለውን መመርያ በቀላሉ ስለማያገኝ በተሻረ መመርያ መሠረት ማመልከቻውን ያቀርብና አዲስ መመርያ እንደወጣ የሚሰማው ከፈቃድ ሰጪ መሥሪያ ቤቱ እየሆነ መምጣቱም ችግሩን ያሳያል ተብሏል፡፡ 

መመርያዎች በተለዋወጡ ቁጥር በአንድ ቀን መሬት የወሰዱ ሰዎች አንዱ ግንባታውን ለመጀመር በመዘግየቱ ብቻ በተለያየ መመርያ የሚስተናገዱት አሠራሮች ታይተዋል ብሏል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አሠራር አንዱ ይጠቀማል፤ አንዱ የሚጐዳ መሆኑን ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ሕጎቹ አልፎ አልፎ ከፍተኛ መደናገር የሚፈጥሩና እርስ በእርስ የሚጣረሱ ድንጋጌዎችንም ስለመያዛቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ የግንባታ ፈቃድ የሚከለከልባቸው ምክንያቶችና የግንባታ ሥራ የሚጀመርበትንና የሚጠናቀቅበትን ጊዜ የሚመለከት ድንጋጌዎችን በምሳሌነት አስቀምጧል፡፡

የግንባታ ፈቃድ ማመልከቻ በሕግ የተቀመጡ መስፈርቶች ከተሟሉ በኋላ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ግድፈቶች ካሉበት ውድቅ እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ግድፈቶች ቢኖሩበትም መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ካልሆኑ ተስተካክለው ፈቃድ እንዲሰጥ ሕጉ ጨምሮ ያሳያል፡፡ እዚህ ላይ ያለው ችግር መሠረታዊ የሕግ ግድፈቶች የሚባሉትንና መሠረታዊ ያልሆኑ የሚለውን መለየቱ ላይ ነው የሚለው ጥናቱ፣ እነዚህ ልዩነቶች ተብራርተው በግልጽ ካልተቀመጡ ተገልጋዩን ኅብረተሰብ ከማደናገር በተጨማሪ በፈቃድ አሰጣጡ ላይ ቢሮክራሲያዊ አሠራርንና ሙስናን የሚያስፋፉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን ሥጋት ገልጿል፡፡

ግንባታ የሚጀመርበትንና የሚጠናቀቅበትን ቀንም በተመለከተ የሚያደናግሩ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በግንባታ ሕጉ ውስጥ ለደረጃ ‹ሀ› ግንባታዎች የግንባታ ፈቃድ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የግንባታ ሥራ በስድስት ወራት ውስጥ መጀመር እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ የማጠናቀቂያው ጊዜ ደግሞ በ24 ወራት ውስጥ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ ለደረጃ ‹ለ› ግንባታዎች የግንባታ ሥራ የመጀመሪያ ጊዜው የግንባታ ፈቃድ ከተወሰደ ጊዜ ጀምሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሲሆን፣ የማጠናቀቂያ ጊዜ ደግሞ በ36 ወራት ውስጥ ነው፡፡ ለደረጃ ‹ሐ› ግንባታዎች በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ግንባታው መጀመር ያለበት ሲሆን፣ በ48 ወራት ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ለእነዚህ ለእያንዳንዳቸው የጊዜ ገደቦች የተፈቀዱ የማራዘሚያ ወራቶች ለደረጃ ‹ሀ› የስድስት ወራት ጭማሪ ያለ ሲሆን፣ ለደረጃ ‹ለ› እና ‹ሐ› ግንባታዎች የአንድ ዓመት ማራዘሚያ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ ያለው የጊዜ ገደቦቹ መቁጠር የሚጀምሩት ከመቼ ጀምሮ ነው? የሚለው ላይ ነው፡፡

ይህንን ብዥታ ለመመልከት እንደማሳያ ያስቀመጠው በሕንፃ አዋጁና በከተማ ሊዝ ደንቡ መካከል ያለውን ልዩነት ነው፡፡ የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ውስጥ ማራዘሚያ የሚሰጠው የግንባታ ፈቃድ ጥያቄው ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ሲል፤ የከተማ ሊዝ ደንብ ቁጥር 49/2004 ደግሞ የግንባታ ፈቃድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ይላል፡፡ የግንባታ ፈቃድ የፀደቀበትና የተሰጠበት ቀን አንድ ሊሆን የሚችለውን ያህል ሊለያይም ይችላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ችግሮች አሉ ብሏል፡፡

ይህ ጉዳይ ቀላል ቢመስልም የሚያስከትለው ቅጣት ሲታይ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን ያስገነዘበው ጥናቱ፣ ግንባታውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለመጀመር የሊዝ ዋጋውን ሰባት በመቶ ድረስ የሚያስቀጣ መሆኑ ያትታል፡፡ መሬቱን እስከመመለስ የሚደርስ ቅጣትም አለው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ግንባታን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለማጠናቀቅ መሬት እስከ መመለስና ሌሎች ቅጣቶችንም ሊያስከትል የሚችል ስለሆነ፣ የግንባታ መጀመሪያና ማጠናቀቂያ ቀነ ገደቦች በማያሻማ መንገድ መቀመጥ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ በተጨማሪም የከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ላይ የተቀመጡት ቅጣቶች የሊዝ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው ደንብ ውስጥ ያለውን የጊዜ ገደብ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው እንጂ በሕንፃ አዋጁ ውስጥ ያለውን ታሳቢ ያደረጉ ያለመሆናቸውም የፍቃድ አሰጣጡ ችግር የቢሮክራሲና ዘገምተኛ አሠራሮች የሚታዩበት ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡

የግንባታ ሕጉ ቢሮክራሲን ለማጥፋትና አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ በማሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ቀነ ገደቦችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በተግባር ግን እየተሠራበት አለመሆኑን የተለያዩ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የፈቃድ ሰጪ መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ትክክል ነው ብለው የሚያምኑት መንገድ ከመወሰን ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጡ ስለሚያጓትቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ወሰንተኛ ባለይዞታ ፎርሙን አልሞላም ካለ ምን ይደረጋል ለሚለው የግንባታ ፈቃድ ሰጪ የሥራ ኃላፊዎች አመልካቹንና ወሰንተኛውን ‹‹ተስማሙ›› ከማለት ውጪ ወሰንተኛው አልስማማም ቢል ምንም ውሳኔ ሲሰጡ አለመታየታቸው ትልቅ ችግር መሆኑን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡ ብዙ የግንባታ ፈቃድ ማመልከቻዎች የሚዘገዩበት ዋናው ምክንያት ወሰንተኞች በማን አለብኝነት ስምምነታቸውን ስለማይሰጡ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች አያሌ ለቢሮክራሲ የተጋለጡ አሠራሮች የግንባታ ማነቆዎች ስለመሆናቸው ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል በሕጉ የተቀመጡ ቀነ ገደቦች ያለመከበራቸውንም ጥናቱ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የግንባታ ፕላን ስምምነት (Planning consent) በሦስት ቀናት ውስጥ መሰጠት እንዳለበት በደንብ ቁጥር 243/2004 በአንቀጽ 4(6) ላይ ቢደነገግም፣ በተግባር ግን ከዚህ እጅግ የረዘመ ጊዜ እንደሚወስድ ይታወቃል፡፡ ሌሎች የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸው አገልግሎቶች በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት ከግንባታ ፈቃድ ዓላማ ውጪ አጥር ለማጠር፣ የጣሪያ ክዳን ለመቀየር፣ ወዘተ. ግንባታ ፈቃድ እንዲኖር ማስገደድ የተለመደ ሲሆን፣ ይህም አገልግሎት ሰጪውንም ሆነ ተቀባዩን የሚጠቅምበት መንገድ ግልጽ አይደለም፡፡ በአገልግሎት ሰጪው በኩል ከሕጉ ዓላማ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጊዜውን እንዲያጠፉ የሚያደርገው ሲሆን፣ ለአገልግሎት ተቀባዮችም ቢሆን ለወጪና ለጊዜ ብክነት የሚዳርጋቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህና መሰል አሠራሮች ለቢሮክራሲና ዘገምተኛ አሠራር በር የሚከፍቱና የግሉን ዘርፍ ለከፍተኛ ወጪ እንዲሁም ለጊዜ ብክነት የሚዳርጉ እንደሆኑ ያብራራል፡፡

የኢትዮጵያ የግንባታ ፈቃድ ሕግ አጠቃላይ የአቀራረፅ ችግር እንዳለበት የተደረጉትን የዳሰሳ ምልከታዎች በአብነት ያስቀመጠው ይኸው ጥናት፣ መተግበር ያለባቸው ሕጐችም ተፈጻሚ ያለመሆናቸውን አሳይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ከ900 በላይ የከተማ መስተዳድሮች የፌዴራል የግንባታ ሕጉን መፈጸም ያለመጀመራቸውን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልግ የሰውና የቁሳቁስ አቅም የላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁሉ ከተሞች የግንባታ ፈቃድ ሳይሰጥ ሕንፃዎች እንዴት እየተገነቡ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ተብሏል፡፡ ስለሆነም የአገሪቱ የግንባታ ፈቃድ ሕግ በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ውጭ እየተተገበረ አይደለም ለማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የግንባታ ሕጉን ዋና ዋና መርሆዎች ማስፈጸም በሚችል መልኩ በየአካባቢው ያሉ መስተዳድሮች ዝርዝር መመርያዎችን ቀርፀው ማስፈጸም እንዲችሉ ዝርዝር የማስፈጸሚያ ሕጎችን እንዲያወጡ ሥልጣን ሊተውላቸው እንደሚገባም ጥናቱ ይመሰክራል፡፡ ለምሳሌ በፌዴራል የግንባታ ሕግ ውስጥ የተቀመጡት ቀነ ገደቦች በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ከዘጠኝ መቶ በላይ ከተሞች በአንድ ዓይነት መንገድ ሊፈጸም ስለማይችል፣ እያንዳንዱ አካባቢ የየራሱን ሊያወጣ ይገባል ብሏል፡፡

ከፈቃድ አሰጣጡ ውጭ ሌሎች ግድፈቶች የሚታዩበት ይህ ዘርፍ በዋናነት ሦስት ዓይነተኛ ችግሮች እንዳሉበት ጥናቱ አመላክቷል፡፡ እነዚህም የተቋማት በተደጋጋሚ መቀየር፣ የግንባታ ፈቃድ ሥራ ከመሬት አስተዳደር ጋር አንድ ላይ መሠራቱ የሚፈጥረውን ችግርና ደረጃ በደረጃ ለሚደረግ ግንባታ የፈቃድ አሰጣጥ ግልጽ ያለመሆኑን ማንሳት ይቻላል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ እንኳን በአዲስ አበባ ያለውን የግንባታ ፈቃድ ሥርዓት ብንቃኝ አያሌ የተቋም ለውጦችን እንመለከታለን፡፡ በተደረጋሚ ሲደረጉ የነበሩ ለውጦች የግንባታ ፈቃድ ሰጪ ተቋም ረግቶ በሰው ኃይልና የአሠራር ልምድ (ተቋማዊ ባህል) እንዳያዳብር አድርጓል፡፡ ይልቁንም ተቋማዊ ለውጥ በተደረገ ቁጥር አመራሩና ሠራተኛው እየተቀያየረ ተቋማዊ አቅምን እንደ አዲስ የመገንባት ሥራ በተደጋጋሚ እየተሠራ ቆይቷል፡፡ ተቋማት ሲፈርሱና ሲቀያየሩ የዳታዎችና መረጃዎች አያያዝና አጠባበቅ ላይም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ይህን ዓይነቱን በየወቅቱ የሚደረግ የተቋም ለውጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስቀር የማያዳግም ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡

ሌላው ተቋማዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የግንባታ ፈቃድ ተቋም ከመሬት አስተዳደር ወይም ከመሠረተ ልማት ጉዳዮች ጋር መያያዙ ነው፡፡ ይህም የተቋሙን ውጤታማነት በእጅጉ ከሚጎዱ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜያት የግንባታ ፈቃድ ሰጪ ቢሮው ከመሬት አስተዳደርና ከመሠረተ ልማት ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ጋር የተጣመረ ስለነበር የግንባታ ፈቃድን ዋና ሥራው አድርጎ የሚሠራ አካል አልነበረም፡፡ ነገር ግን የመጨረሻው ለውጥ ቢያንስ ቢያንስ የግንባታ ፈቃድ ሥራን የሚሠራውን ተቋም ከእነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች ለይቶታል፡፡ ነገር ግን አሁንም ተጠሪነቱ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ከመሬት አስተዳደር ጉዳዮች ነፃ ሆኗል ለማለት አይቻልም ብሏል፡፡

ጥናቱ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጡ ችግሮች ላይ ብቻ ያጠነጠነ ሳይሆን የመፍትሔ ሐሳቦች ያላቸውንም አስቀምጧል፡፡ እንደ መፍትሔ ከተቀመጡት ውስጥ ግንባታ የሚጀመርበትንና የሚጠናቀቅበትን ቀን ለማስላት በሕንፃ አዋጁና በሊዝ ሕጉ መካከል ያለውን ልዩነት ማስተካከል አንዱ ነው፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ማጠቃለያ ላይ ከቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱን አውቶሜትድ በሆነ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ፣ ይህም ማመልከቻዎች ሲቀርቡ፣ ከቀረቡም በኋላ የሚገኙበት የአፈጻጸም ሒደት፣ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁ መስፈርቶችና ሌሎችም ይዘቶች በዚህ አሠራር እንዲቃኙ የሚጠይቀው ይገኝበታል፡፡

ከዚህ ባሻገር ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁ መስፈርቶች በሙሉ ተሟልተው ከቀረቡ በኋላ ማመልከቻዎች የቀረቡለት አካል በመጨረሻው ሒደት ወቅት ውድቅ የሚያደርግበት አሠራርም እንዲታረም ተጠይቋል፡፡ ግንባታ ሲጀመር ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ያለውን የጊዜ ብዛት በማስላት በሕንፃ አዋጁና በሊዝ ሕጉ መካከል የሚታዩ የጊዜ አሰፋፈር ልዩነቶች እንዲታረቁ ማደረግም በመፍትሔነት ከተጠቆሙት መካከል ይመደባል፡፡ እንዲህ ያሉትን ጨምሮ በርከት ያሉ የመፍትሔ ሐሳቦች በሕጎቹና በአተገባበራቸው ላይ፣ በአስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም በመሥሪያ ቤቶች አቅምና ብቃት ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል በተባሉ ሐሳቦች ላይ ምክር ቤቱ መፍትሔ ያላቸውን ነጥቦች አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች