Wednesday, February 28, 2024

‹‹የህዳሴው ግድብ የሕዝብ ስለሆነ ኃላፊነት የጎደለው ስምምነት ፈርሞ መምጣት አይቻልም››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተመከሩ ሁለት ምክረ ሐሳቦችን በውጭ አማካሪዎች ለማስጠናት፣ ሁለት ኩባንያዎችን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ቢመርጡም ወደ ትግበራ መሸጋገር አልተቻለም፡፡

ሦስቱ አገሮች በደረሱት ሙሉ ስምምነት መሠረት የፈረንሣዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ ኩባንያ ዋና የፕሮጀክቱ አጥኚና ተዋዋይ ሲሆን፣ 30 በመቶ የሚሆነውን የጥናቱ ሥራን ደግሞ ዴልታሬዝ ለተባለው የኔዘርላንድ ኩባንያ እንዲሰጥ በሚል ተወስኗል፡፡

ይሁን እንጂ በስምምነቱ መሠረት ሥራውን ማስጀመር አልተቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዴልታሬዝ የተባለው ኩባንያ የሙያ ነፃነቱን የሚጋፋ የሥራ መዘርዝር ከዋና ኮንትራክተሩ ቀርቧል በሚል ራሱን ማግለሉ ነው፡፡

ሦስቱ አገሮች በደረሱት ስምምነት መሠረት ቢአርኤል የተባለው ኩባንያ ለጥናቱ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይኼም ማለት ዴልታሬዝ 30 በመቶውን ጥናት ቢያከናውንም፣ የጥናቱ ውጤት ይዘት የሚወሰነው 70 በመቶ ከሚሆነው የጥናቱ አካል ጋር ተገናዘበና ውሳኔውም በዋና ኮንትራክተሩ መሆኑ ለዴልታሬዝ የሚስማማ አልሆነም፡፡

በዚሁ የተነሳ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ላይ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ምክንያት ጥናቱን ማካሄድ ከነበረበት ጊዜ ተጓቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ሦስት ሐሳቦችን ቢያቀርብም በወቅቱ ተቀባይነት ማግኘት አልተቻለም፡፡

ከቀረቡት ሐሳቦች አንደኛው ሁለቱን ኩባንያዎች ማግባባት፣ ሁለተኛው ሁሉንም ጥናት የፈረንሣዩ ኩባንያ ብቻውን እንዲያከናውን ማድረግ፣ የመጨረሻው አማራጭ ሌላ ኩባንያ መምረጥ የሚሉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በግብፅ አመራሮች በኩል የኢትዮጵያ ሐሳብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ምክንያት ወደ አማራጮቹ ከመግባት በፊት በቅድሚያ የፖለቲካ ውይይት መደረግ አለበት የሚል ሐሳብ በመቅረቡ፣ ወደዚሁ ውይይት ከሁለት ሳምንት በፊት ተገብቷል፡፡

የግብፅ ሥጋት የግድቡ የግንባታ ፍጥነትና አጀማመር ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ እርግጠኝነት ትፈልጋለች፡፡ የዚሁ ውይይት ማጠቃለያም ታኅሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡

ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን የግብፅ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ የጥናት ውጤቱ ሳይጠናቀቅ ግድቡን በውኃ መሙላት ላለመጀመር መስማማቷን የሚገልጹ ዘገባዎችን በስፋት አሰራጭተዋል፡፡ እነዚህ ዘገባዎችም ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሚስማሙ አልሆኑም፡፡ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ጉዳዩን ለኢትዮጵያ  የፖለቲካ ክስረት አድርገው ወስደውታል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ ላለመሙላት ፈርማለች?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ታኅሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የበጀት ዓመት ዕቅድና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የሚኒስቴሩን የመጀመርያ ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ስላለው ውይይትና ሰሞኑን ስለተደረሰው ስምምነት ገልጸዋል፡፡ በግድቡ ላይ የተመከሩ ጥናቶችን ለመጀመር ያልተቻለበትን ምክንያት ለመቅረፍ በተደረገው ድርድር፣ ከጥናት ሥራው ራሱን ባገለለው የኔዘርላንዱ ኩባንያ ዴልታሬዝ ምትክ አርቴሊያ የተባለ ኩባንያ በመምረጥ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ይዘት ጥናቱን ሁለቱ ኩባንያዎች በጥር ወር መጨረሻ ላይ በይፋ እንዲጀምሩ ማድረግን የተመለከተ ነው፡፡ የተቀሩት ጉዳዮች የሚመለከቱት ግን የሦስቱ አገሮች መረጃዎች ከዚህ ቀደም ለተስማሙባቸው የመርህ መገለጫዎች ቁርጠኝነትን በድጋሚ አገሮቹ በሚኒስትሮቻቸው የገለጹበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች የህዳሴውን ግድብ እንዲጎበኙ ኢትዮጵያ ጥሪ ማቅረቧን ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የተደረገው ኢትዮጵያ ደብቃ የምትሠራው ነገር አለመኖሩን ለማሳየትና እምነትን ለመፍጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህንን ከተነጋገርን በኋላ ቃለ ጉባዔ ተፈራረምን፡፡ አሁን ነገሩን ለመጠምዘዝ የሚፈልጉ የግብፅ ሚዲያዎች አዲስ ስምምነት እያሉ ይጽፋሉ፡፡ አዲስ የተፈራረምነው ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላ ስምምነት ተፈረመ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ላለመሙላት እንደተስማማች ተደርጎ እየተወራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሁሌ ወደ ድርድር ስንገባ ግድቡን ለመገንባት በሌለ አቅማቸው መዋጮ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችንን እያሰብን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የሕዝብ ስለሆነ ኃላፊነት የጎደለው ስምምነት ተፈርሞ ሊመጣ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ በግብፅ ባለሥልጣናት እየተነሳ ያለው ማስረጃ ግን የሦስቱ አገሮች መሪዎች በፈረሙት የመርህ መገለጫ አንቀጽ አምስት ላይ ኢትዮጵያ የጥናቱ ውጤትን እንደምትቀበልና የመጀመርያው የውኃ ሙሌትም በስምምነቱ መሠረት እንደሚከናወን በመጥቀስ ነው፡፡

ከፓርላማው ውይይት በኋላ ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ‹‹በመርህ መገለጫው ስምምነት ላይ የተስማማነው ግድቡ እየተገነባ ጥናቱ ጎን ለጎን ይካሄዳል የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ማለት ውኃ ለማጠራቀም እንጂ ‹‹የቻይና ግድብን›› ለመገንባት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የግብፅ ሚዲያዎችና አንዳንድ ባለሥልጣናት ሆን ብለው ‹‹ግንባታው ከጥናቱ ጎን ለጎን ይቀጥላል›› የሚለውን የመርህ መገለጫው አንቀጽን አንድም ቀን ጠቅሰው አያውቁም ብለዋል፡፡

ለአደናጋሪ የሚዲያ ዘገባዎች በኢትዮጵያ በኩል መልስ የመስጠት ችግር ስለመኖሩ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ነገሩ እንዳይቀጣጠል ፈልገናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ግንባታችንን እያከናወንን ነው ሥራችን ይቀድማል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ግብፆች በሚዲያዎቻቸው አማካይነት የሚሰጧቸው መግለጫዎች ሕዝባቸውን የማረጋጋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሥራዋን የጨረሰችው የመርህ መገለጫ ስምምነቱን በመረጃዎች ደረጃ በፈረመችበት ወቅት ነው የሚሉት እኚሁ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ግብፆች በዚሁ ስምምነት ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ዓባይን የማልማት ሉዓላዊ መብት እንዳላት አምነው ተቀብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከታሪካዊ ኮታቸው ወጥተው ኢትዮጵያ ውኃውን በፍትሐዊ መንገድ መጠቀም እንደምትችል ተስማምተው ፈርመዋል ብለዋል፡፡

ይህንን ስምምነት ለሕዝባቸው ነግረው ስለማያውቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁንም በእጃቸው ውስጥ መሆኑን ለማሳወቅ ሚዲያዎቻቸውን ይጠቀማሉ በማለት አስረድተዋል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -