Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቂሊንጦ ቃጠሎ ምክንያት ተከሰው የነበሩትን ጨምሮ የ62 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ

በቂሊንጦ ቃጠሎ ምክንያት ተከሰው የነበሩትን ጨምሮ የ62 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ

ቀን:

ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው ከነበሩት ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች መካከል፣ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተከሳሾች ክስ ዓርብ ግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቋረጠ፡፡

ክሱን ያቋረጠው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ክሱ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ የሰጡት በቅርቡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆነው የተሾሙት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በቂሊንጦ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የ23 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ጠቅሶ፣ ዓቃቤ ሕግ ከ100 በላይ በሚሆኑ ተከሳሾችና ፍርደኞች ላይ ክስ መመሥረቱ ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙና በተደጋጋሚ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹እኛ እንዴት ወንድሞቻችንን እንገድላለን? የእሳቱ ቃጠሎ በደረሰበት ወቅት ግማሾቻችን ዝዋይ ማረሚያ ቤት ነበርን፡፡ ግማሾቻችን ደግሞ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ነበርን፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከ15 ቀናትና ከአንድ ወር በኋላ ከያለንበት ተሰብስበን በኃይል እየተገረፍንና ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመብን ክስ እንዲመሠረትብን መደረጉ አግባብ አይደለም፤›› በማለት ሲከራከሩ ከርመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ ባረቀበው ክስና አቤቱታ፣ ‹‹ዱርዬው ቡድን›› የሚል አደረጃጀት ፈጥረው ድርጊቱን መፈጸማቸውን የሚያስረዱለት የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቀርባለሁ ብሎ ለፍርድ ቤቱ በመንገሩ፣ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ፈቅዶለት ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ በፈቀደለት መሠረት ጥቂት ምስክሮችን ያሰማ ሲሆን፣ ቀሪ ምስክሮችን ለማሰማት በተደጋጋሚ ለአምስት ጊዜ ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆንም፣ ምስክሮቹ ቀርበው ሊመሰክሩ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ሳይሰማ አልፏቸዋል፡፡

ከተከሳሾቹ መካከል 16 የሚሆኑት በማረሚያ ቤት እያሉ ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ በማመልከታቸው፣ ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ተከሳሾቹ የተናገሩት ድርጊት እውነት መሆኑን ኮሚሽኑ አጣርቶ ሪፖርት አቅርቦ ነበር፡፡

የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ሪፖርት ፍርድ ቤቱ መርምሮ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን ሰጥቷል፡፡ በሰጠው ብይንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ያላቸውን ተከሳሾች በነፃ አሰናብቷል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና ሌሎች ተከሳሾች የተከሰሱበትን የወንጀል ሕግ በመቀየር እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ የተወሰኑ ተከሳሾችን ደግሞ በማቃጠልና በግድያው በቀጥታ ተሳትፈዋል በማለት እንዲከላከሉ ብይን ሲሰጥ፣ ‹‹ወንድሞቻችንን እኛ እንዴት እንገድላለን?›› የሚል ጩኸት በማሰማት ችሎቱን የሚያስችሉትን ዳኞች በመሳደብና ለድብድብ ሲጋበዙ አጃቢ የፖሊስ አባላት መሣሪያ በማቀባበል ጭምር የነበረውን ረብሻና ሁከት የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በዕለቱ ቀጣዩ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ መናገር ሳይችሉ ዳኞች ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡  

ተከሳሾቹ በከፍተኛ ሁከት ወደ ማረሚያ ቤት የተመለሱ ሲሆን፣ ከአምስት ቀናት ቆይታ በኋላ ምክንያቱ በብይኑ ይሁን በሌላ ማወቅ ያልተቻለ ቢሆንም፣ ክሳቸው እንዲቋረጥና ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ በሰው ግድያ ክስ የተመሠረተባቸው ግን ክሳቸው ይቀጥላል ተብሏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...