Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በዚህ ዓመት ለውጭ የብድር ዕዳ 16 ቢሊዮን ብር እንደሚከፍል ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአጭር ጊዜ ብድር ተከለከለ

መንግሥት በዚህ ዓመት በውጭ ብድር ከሚፈለግበት ዕዳ ውስጥ 16 ቢሊዮን ብር እንደሚከፍልና እስካሁንም 11 ቢሊዮን ብር መክፈሉ ታወቀ፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የአገሪቱ የብድር ጫና እየጨመረ በመምጣት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ቢልም፣ መንግሥት ግን አልተቀበለውም፡፡

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመክተው፣ ኢትዮጵያ የተከማቸባትን ዕዳ ማቃለሉ ላይ በማተኮር በዚህ ዓመት ከሚጠበቅባት የዕዳ ክፍያ ውስጥ እስካሁን 11 ቢሊዮን ብር ከመክፈሏም ባሻገር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከፈሉና ከፍተኛ ወለድ የሚጠየቅባቸውን (Non-commercial Loans) ብድሮች መጠየቅ አቁማለች፡፡

ስለአገሪቱ የብድር ዕዳ ሁኔታ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም የመሳሰሉት የልማት ድርጅቶች የአጭር ጊዜ ብድሮችን ከመበደር እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም የአገሪቱ የብድር ዕዳ ጫና ቀስ በቀስ እያደገ በመምጣቱ ሳቢያ፣ እንዲሁም አበዳሪዎችን እምነትም ላለማጣት ጭምር መንግሥት በአጭር ጊዜ የሚከፈሉ ብድሮችን በማቋረጥ በብድር ዕዳ ክፍያ ላይ ማተኮሩን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ከአንድ ዓመት በላይ ብድር ሲያገኝ የቆየው ከዓለም ባንክ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሐጂ፣ ይህም የረዥም ጊዜ ብድርን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዓለም ባንክ ሲቀርቡ የቆዩት ብድሮችም እስከ 40 ዓመታት በሚዘልቅ ጊዜ ውስጥ የሚከፈሉና ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብባቸው፣ የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ መጠነኛ ችሮታ ወይም ዕርዳታ የሚታከልባቸው ናቸው፡፡

አይኤምኤፍ በቅርቡ ይፋ ያደረገውና ከመንግሥት ጋር በየጊዜው በቋሚነት ምክክር የሚያደርግበት ‹‹አርቲክል ፎር›› እየተባለ በሚጠራው ሪፖርት መሠረት፣ የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን በጠቅላላው ወደ 27 ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል፡፡ የአገሪቱን የብድር ጫና ከመካከለኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አድርሷል ብሎ አይኤምኤፍ የሚሟገትበት የብድር ዓይነትም ይኼው የአጭር ጊዜ ብድር ቢሆንም፣ መንግሥት ግን የአይኤምኤፍን ግምገማ አይቀበለውም፡፡

ኢትዮጵያ ያለባት የብድር ጫና ከፍተኛ በሚባለው ደረጃ ላይ አልደረሰም የሚለው መንግሥት፣ የብድር ዕዳውን ከፍ እንዲል ያደረገው የወጪ ንግዱ ደካማ መሆንና የብድር ዕዳን ለማቃለል የሚያደርገው አስተዋጽኦ ደካማ እየሆነ መምጣት እንደሆነ በመግለጽ የመንግሥት ባለሥልጣናት መከራከሪያቸውን እንዳቀረቡ፣ የአይኤምኤፍ ሪፖርት ያሳያል፡፡ 

መንግሥት ለብድር ዕዳው ማቃለያነት እንዲረዳው የወጪ ንግዱን የሚያበረታቱ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የብርን የመግዛት አቅም ከመቀነስ ባሻገር፣ የታክስ ገቢን ማሳደግና የቁጠባ መጠን እንዲጨምርና ሌሎችም ቆንጣጭ የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እንደሚወስዱ ተስማምቷል፡፡ የመንግሥት ወጪዎችን በተለይም ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ የትልልቅ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ጋብ ማድረግ ከሚጠበቁ ዕርምጃዎች ውስጥ ቢካተትም፣ የዋጋ ግሽበትን የመሳሰሉ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የመንግሥት ልጓም መላላት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የሚያዝያ ወር የዋጋ ግሽበት 13.5 በመቶ መድረሱ ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች