Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየስፖርት ማዘውተሪያዎች ከመድረክ ጫጫታ ያለፈ መፍትሔ ይሻሉ

የስፖርት ማዘውተሪያዎች ከመድረክ ጫጫታ ያለፈ መፍትሔ ይሻሉ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨዋታዎች የሚዘወተሩባቸው ቦታዎችም ሆነ ከውድድር ሜዳዎች ውጪ የሚፈጸሙ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰቶች ላይ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ስብሰባዎች እስኪያሰለቹ ድረስ ተካሂደዋል፡፡ እየተካሄዱም ናቸው፡፡ መግለጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ ማስጠንቀቂያዎችና የቅጣት ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ችግሮቹ ግን እየባሰባቸው መጥተዋል፡፡

የሚደረጉት ስብሰባዎችና ምክክሮችም የደቦ ጩኸት ከመሆን አላለፉም፡፡ የዲሲፕሊን ጥሰቶች በስብሰባዎችና ውግዘቶች ብዛት ሊቀረፉ አልቻሉም፡፡ ይህም ሆኖ ይመለከተናል በሚሉ አካላትና በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ጉባዔዎች ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የፌዴራል የስፖርቱ ኃላፊዎች፣ የክለቦች አመራሮች፣ ሙያተኞችና ሌሎችም በየመድረኩ እየተጯጯሁ፣ እየተነታረኩና እየተወቃቀሱ ቢነጋገሩም ችግሩ እየባሰበት ከመሄድ ይልቅ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ? ብዙዎች ምላሽ የሚጠብቁበት ሆኖ ይገኛል፡፡

የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች በሁሉም አቅጣጫ መነጋገሪያ ሆኖ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የውይይትና የምክክር መድረክ ሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዳማ ከረዩ ሆቴል ተከናውኗል፡፡ በመድረኩ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮች፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የክለብ አመራሮች ባለሙያዎችና ሌሎችም የስፖርቱ ባለድርሻ የሚባሉ ተሟልተው የተገኙበት ነበር፡፡ ሁሉም የችግሩ መንስኤና መፍትሔ ያለውን አንፀባርቋል፡፡ የአፈጻጸሙ ጉዳይ በሒደት የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መድረኩ ሲጠቃለልም በአቋም መግለጫ ጭምር ነበር፡፡

- Advertisement -

ስፖርታዊ ጨዋነት በአንድ አካል ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ፣ በአጠቃላይ ለስፖርቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያልተጻፉ ሕጎችን ከማክበር ጀምሮ ማሸነፍና መሸነፍን በፀጋ መቀበልን፣ መከባበርን፣ መደማመጥና መተራረምን ማዳበር ከሁሉም ወገን እንደሚጠበቅ በአቋም መግለጫው ከተካተተው ይጠቀሳል፡፡

ተሰናባቱ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንደሚገልጹት መድረኩ መደረግ የነበረበት በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከስፖርታዊ ጨዋነት ጎን ለጎን በትልቁ መነጋገሪያ ሆኖ እስካሁን የዘለቀው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ሊደረግ ባለመቻሉ፣ አሁን ደግሞ የስፖርታዊ ጨዋነቱ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት መድረኩ እንዲፈጠር ግድ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ ቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ ከሆነ፣ ውይይቱ በዋናነት ባለድርሻ አካላት በችግሩ ዙሪያ ምን ይላሉ? እንደሚነገረው ችግሩስ አለ ብለው ያምናሉ ወይ? ካመኑስ የመፍትሔው አካል ለምን አልሆኑም? የሚለውን ለማወቅና በቀጣይ ሊወሰድ ስለሚገባው የመፍትሔ አቅጣጫ የጋራ አቋም ለመያዝ መሆኑን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ተወያዮቹ የችግሩን አሳሳቢነትና የራሳቸውንም ድርሻ በመናገር ደረጃ ከሚገባው በላይ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ኃላፊውም ይህንኑ ያምናሉ፡፡

ስፖርታዊ ጨዋነትን በሚመለከት እንዲህ እንደ አሁኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲዘጋጅ የመጀመርያ ቢሆንም፣ አጀንዳው የተለመደና ብዙዎቹ ተሳታፊዎች ደግመው ደጋግመው የተነጋገሩበት መሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ እግር ኳሱ በተለይም አሁን ላይ ከመድረክ ጫጫታና ፍጆታ ያለፈ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ጭምር ያሳስባሉ፡፡

የአቋም መግለጫ አቋም ሊሆን የሚችለው ከአስፈጻሚው አካል ጀምሮ በየደረጃው የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች አፈጻጸሙን ከተከታተሉት ብቻ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይህ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሚኒስቴሩ ከተልዕኮው በመነሳት፣ እግር ኳሱም ኅብረተሰቡ በሚፈልገው መጠን ማደግ ስላለበት ብቻ ሳይሆን፣ ከሚያስፈልገው ሰላምና ፀጥታ አንጻር መከታተያና ማስፈጸሚያ ሰነድ የተዘጋጀ ስለመሆኑ በቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ ተነግሯል፡፡ ይህም ሆኖ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ በክልሎችና በክለቦች ጠንካራ የሆነ የውስጥ የዲሲፒሊን መመርያ እስከሌለ ድረስ አሁንም የሚኒስቴሩ ጥረት ብቻውን ችግሩን ማስወገድ እንደማይችል ግን አልሸሸጉም፡፡

ከአዳማው ጉባዔ በመነሳት ሚኒስቴሩ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ አጀንዳው በሁሉም ክልሎች እስከ ታች ወርዶ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልግ ከሆነም ያንን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ጊዜ ገደብ የተቀመጠለት መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ ለተሳታፊዎቹ ዕቅዱ በሲዲ ተባዝቶ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ለእንዲህ ዓይነቱ የመንግሥት አካሄድ ይሁንታ የሚሰጡት ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት ብቻ መሆኑ፣ ከዚያ ሲያልፍ ግን ‹‹የመንግሥት ጣልቃ ገብነት›› በሚል ሲያስፈራሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሚኒስቴሩ በቀጣይ ‹‹እተገብረዋለሁ›› ለሚለው አሠራር እንቅፋት አይሆንም ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ተስፋዬ መልስ አላቸው፡፡ ‹‹በዚህ ማስፈጸሚያ ሰነድ አንድም የፊፋም ሆነ የካፍ ሕገ ደንቦች አይጣሱም፡፡ ሆኖም የእግር ኳሱ ዲሲፕሊን መመርያ ደካማ ነው ተብሎ ከታመነበት በራሱ መንገድ ክፍተቱን እንዲሞላ ማድረግ ጣልቃ ገብነት አያስብልም፡፡ እንደምንመለከተው ውሳኔዎች አይከበሩም፡፡ ይህም ከራሱ ከእግር ኳሱ ጉባዔም ሆነ ከአዳማው መድረክ ሲነገር ተደምጧል፡፡ በዚህ መነሻነት ግንዛቤ እንዲወሰድ ማድረግ እገዛና ድጋፍ አድርጎ መውሰድ ከጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ነው፡፡ ሲጀመር መንግሥት በጉዳዩ እንዲገባ ያስገደደው ችግሩ ስላለ ነው፤›› ብለው እያንዳንዱ ደንብና መመርያ እንዲሻሻልም ሆነ እንዲፀድቅ የሚደረገው በእግር ኳስ በራሱ መዋቅር መሠረት ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ እስከአሁን አልተደረገም፡፡ ይህ ባልሆነበት እንደ እነዚህ የመሳሰሉ ደንብና መመርያዎች ላይ መነጋገሩ ፋይዳው ምንድነው? ለሚለው ኃላፊው ‹‹ምርጫው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በዚህ ወር ይጠናቀቃል፡፡ ከምርጫው በኋላ እነዚህን ሊያስፈጽምና ሊከታተል የሚችል አገራዊ ግብረ ኃይል ከራሱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች፣ ከዳኞች፣ ከክለቦች፣ ከማኅበራትና ከመንግሥት ተቋቁሞ ይህ ነገር በትክክለኛው መንገድ እየሄደ ነው አይደለም የሚለውን በስምምነት እንዲከታተል ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስን ጨምሮ የሁሉንም ስፖርቶች አጠቃላይ አካሄድ የሚከታተልና የሚጠይቅ አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት በ1990ዎቹ መጀመርያ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ይሁንና አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት በተለይም በአሁኑ ወቅት በእግር ኳሱ ዙሪያ እየተፈጠረ ስለሚገኘው ክስተት አንዳችም ሲል አይደመጥም፡፡ የስፖርት ምክር ቤቱ የማይሠራ፣ ነገር ግን ሕጋዊ ሆኖ ሳለ ሌላ አገራዊ ግብረ ኃይል ማዘጋጀት ጥቅሙ ምንድነው? ለሚለው አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹እንደሚታወቀው የስፖርት ምክር ቤቱ የተቋቋመው በአዋጅ ነው፡፡ የአሁኑ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ኮሚሽን እያለ በበላይነት የሚመራውና በአዋጅ ለሚኒስቴሩ የተላለፈ ተቋም ነው፡፡ የተቋቋመበት ዋናው ዓላማ ደግሞ የአገሪቱን ስፖርት ከሚኒስቴሩ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲመራ የታለመም ነው፡፡ ሆኖም ይህ ተቋም አሁን ላይ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰሰ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ያም ሆኖ አሁን እንዲቋቋም የሚደረገው ግብረ ኃይል ከስፖርት ምክር ቤቱ ይለያል፡፡ ኃላፊነቱም በዋናነት ከስፖርታዊ ጨዋነቱና በዚያ ዙሪያ የሚከሰቱ ጉዳዮችን የሚከታተልና ለመፍትሔው ከታች ጀምሮ ግብዓት የሚሰባስብ ነው፡፡ አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት ግን ሁሉንም ስፖርቶች የሚመለከት፣ የሚመራና የሚቆጣጠር አካል ነው፤›› ብለው ሕጋዊ አደረጃጀቱ በስምምነት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በእግር ኳሱ እየተፈጠረ ላለው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት እያለ ሚኒስቴሩ ታዲያ ለምን? ለሚለው ኃላፊው፣ ‹‹ይህ ጉዳይ እንደተባለው ምክር ቤቱ ከሚያያቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይሁንና ምክር ቤቱ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ሥራ ላይ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ምክር ቤት በትክክለኛው ሕጋዊ ሰውነቱ ላይ ቢሆን ኖሮ አሁን ለምንነጋገርበት ችግር መፍትሔነቱ አያጠያይቅም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይ ግን ምክር ቤቱ እንዳለው ሕጋዊ ሰውነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያምናሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...