ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝኩ ነበርኩ፡፡ ድሬዳዋ የሄድኩበትን ጉዳይ ቶሎ አከናውኜ ወደ አዲስ አበባ የማደርገው ጉዞ የፈጠነው፣ በነጋታው ለሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ወደ ጎንደር ስለምሄድ ነበር፡፡ ከድሬዳዋ የጀመርነውን ጉዞ እያገባደድን አዋሽ አካባቢ ስንደርስ የተሳፈርንበት አውቶቡስ ጎማ ፈንድቶ ቆምን፡፡ ጎማ እስኪቀየር ድረስ ከአውቶቡሱ ወርደን እግሮቻችንን ስናንቀሳቅስ በድንገት ከአንድ የማውቀው ሰው ጋር ተያየን፡፡ ያንን ሁሉ መንገድ በአንድ አውቶቡስ ስንጓዝ ባለመተያየታችን እየገረመኝ ሰላምታ አቀረብኩለት፡፡
በድንገት ያገኘሁት ይህ ሰው ከመክሳቱና ከመጥቆሩም በላይ ከሰውነት ጎዳና ወጥቷል፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ካበቃን በኋላ ‹‹ምን ገጠመህ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ይልቅ አጠገብህ የተቀመጠው ሰው ከተባበረን እንጠይቀውና አብረን እያወራን እንጓዝ፤›› አለኝ፡፡ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምተን አጠገቤ ለተቀመጠው ወጣት ይህንኑ ነግሬው እሺ በማለቱ ከዚህ ሰው ጋር አብረን ተቀመጥን፡፡ አውቶቡሱ ጉዞ ሲጀምር የእኛም ወሬ ከቆመበት ቀጠለ፡፡
ይኼ የማውቀው ሰው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ሲሠራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን እንማር ነበር፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ በአንድ ታዋቂ አስመጪና ላኪ ድርጅት ውስጥ አብረንም ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ይኼው ሰው የዲቪ ሎተሪ ደርሶት አሜሪካ መሄዱን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ አይቼው አላውቅም፡፡ ከተለያየን ቢያንስ 15 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በሚጓዘው አውቶብስ ላይ ተገናኘን፡፡
‹‹ወንድሜ ምን አጋጠመህ? የት ነው ያለኸው?›› አልኩት፡፡ የዚህን ሰው የቀድሞ ገጽታ ለመግለጽ ያህል በጣም ቀይ፣ ቁመታም፣ ደልደል ያለ ውፍረት ያለውና በጣም ሳቂታና ተጫዋች ነበር፡፡ አሁን ግን ፊቱ ጠቁሯል፡፡ በጣም ከስቷል፡፡ ያ የፈካ ገጽታ ጠፍቶ ዓይኖቹ ቀና ብለው ለማየት አይደፍሩም፡፡ እንደ ምንም ትንፋሹን ሰብስቦ፣ ‹‹አሜሪካ ጉድ አደረገችኝ፤›› አለኝ፡፡ ይህን ሲነገረኝ አንድ ወጣት ልጅ እያየን መሳቅ ጀመረ፡፡ ለወጣቱ ሳቅ ግድ ሳልል የቀድሞውን ወዳጄን ማነጋገሬን ቀጠልኩ፡፡
በድጋሚ ‹‹እንዴት?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ አሁንም በግድ ትንፋሹን ሰብስቦ፣ ‹‹ቀን ከሌሊት የሠራሁባት አሜሪካ ገንዘቤንና ሚስቴን ነጠቀችኝ፤›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ገንዘቡንና ሚስቱን የምትነጥቅ አሜሪካ ከየት መጣች አልኩ ለራሴ በውስጤ እየተገረምኩ፣ ‹‹ከዚያስ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን ከዚያስ አለ? በቃ ሚስቴ ያለ የሌለ ገንዘቤንና ንብረቴን ዘርፋ ካንዱ ጋር ስትኮበልል፣ በእሷ ስም የተመዘገበ ዕዳ በማላውቀው ዘዴ ወደኔ በማስተላለፏ እኔ ወደ እስር ቤት አመራሁ፡፡ በእኔ ስም ያስመዘገበችውን ዕዳ መክፈል ባለመቻሌ ያለችኝን ጠራርገው ከወሰዱ በኋላ ሁለት ዓመት አሰሩኝ፡፡ ከእስር ስወጣ ኢኮኖሚዬ ደቆ ስለነበር ጎዳና ላይ ወደቅኩ፡፡ በስንት መከራ ወዲያ ወዲህ ብዬ ወደ አገሬ መጣሁ፤›› ሲለኝ ነገር ዓለሙ ዞረብኝ፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ ሰምቼም አላውቅ፡፡ ያ ወጣት አንገቱን እየነቀነቀ አሁንም ፈገል ይላል፡፡
ይህ ወዳጄ አዲስ አበባ ከመጣ አንድ ዓመት እንዳለፈው፣ በብስጭት ምክንያት የማያውቀውን መጠጥ በላይ በላዩ እየጠጣ ለሕመም መዳረጉንና በሳምባ በሽታ በመለከፉ መድኃኒት እየወሰደ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ለጊዜው ዘመዶቹ ዘንድ አርፎ ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም ቅስሙ በመሰበሩ ሥራ እንዳስጠላውም ነገረኝ፡፡ የአሜሪካው ነገር ከንክኖኝ፣ ‹‹በሚስትህ ዕዳ እንዴት አንተ ተጠያቂ ሆንክ?›› አልኩት፡፡ በንዴት እያየኝ፣ ‹‹አገሩን ብታውቀው ኖሮ እንዲህ አትልም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሚስቴ በሥራዋ አጋጣሚ ከአንድ ፖሊስ ጋር መቅበጥ በመጀመሯ ያ ሁሉ አሻጥር የመጣው በእሱ በኩል ነው፤›› አለኝ ጉራማይሌ አማርኛና እንግሊዝኛ እየደባለቀ፡፡ የሚነግረኝ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ወጣቱ ቀና ብሎ አይቶኝ አንገቱን ደፋ፡፡ ወጣቱ ምን ሆኖ ይሆን?
‹‹አሁን ምን አስበሃል?›› አልኩት፡፡ በግዴለሽነት ትከሻውን እየሰበቀ፣ ‹‹ልመንን ነው!›› ሲለኝ ገርሞኝ እያየሁት፣ ‹‹የት ነው የምትመንነው?›› ስለው እየሳቀ እያየኝ፣ ‹‹መርካቶ ምናለሽ ተራ!›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ አዲስ አበባ ደርሰን ከአውቶቡስ ስንወርድ አውቶብሱ ውስጥ እያየኝ ሳቅ የሚለው ወጣት ጠጋ ብሎኝ፣ ‹‹ያለውን በሙሉ አትመነው፡፡ የዕፅ ተጠቃሚ በመሆኑ ከአሜሪካ ተጠርዞ የመጣ ወንድሜ ነው፤›› በማለት ሲነግረኝ በቆምኩበት ደንዝዤ ቀረሁ፡፡ ለነገሩ እንኳን አሜሪካ እዚህስ ስንቱ አይደል እንዴ ከጥቅም ውጪ እየሆነ ያለው? እዚህ መሀል አዲስ አበባ ዋና ዋና በሚባሉ ሥፍራዎች በሐሺሽ የናወዙ ወጣቶች እየበዙ አይደለም እንዴ? ከእነሱ በተጨማሪ ማስቲሽ እያሸተቱ በማበድ ላይ ያሉት የጎዳና ተዳዳሪዎች ብዛት አያስደነግጥም እንዴ? ኧረ ጎበዝ ወዴት እየነጎድን ነው? ልብ ያለው ልብ ይበል አገር እየጠፋ ነው፡፡
(ኤርሚያስ ይትባረክ፣ ከፍላሚንጎ)