ውብሸት ሙላት
በ1952 ዓ.ም. የወጣው የንግድ ሕግ ሥርዓት ካበጀላቸው ጉዳዮች መካከል የማጓጓዝና የማመላለስ ሥራ አንዱ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ በሦስተኛው ክፍሉ ኢንሹራንስን ጨምሮ ለእነዚህ ጉዳይ ደንብ ሠርቷል፡፡ በባህር ላይ የሚደረግ የማጓጓዝ ተግባርን በሚመለከት የተለየና ራሱን የቻለ በዚሁ ዓመት የወጣ ሕግ አለ፡፡ የንግድ ሕጉ ትኩረት የሰጠባቸው በየብስና በአየር የሚደረጉ የማጓጓዝና የማመላለስ አገልግሎት ነው፡፡ በየብስም ይሁን በአየር የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ የንግድ መሆን አለበት፡፡
የንግድ ትራንስፖርት አሰጣጡ በየብስም፣ በውኃም፣ በአየርም ሊሆን ይችላል፡፡ የንግድ ትራንስፖርት ሲባል በጥቅሉ የሚያመለክተው የማጓጓዝ አገልግሎቱ በምድር ላይ በሚሽከረከር፣ በውኃ ላይ በሚቀዝፍ ወይም በአየር ላይ በሚበር መሣሪያ አማካይነት በክፍያ የሚሰጡትን የሚመለከት ነው፡፡ የንግድ የአየር ትራንስፖርትም በሚባልበት ጊዜ አጓጓዡም ለሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ ይጠይቃል፡፡ ተገልጋዩም ክፍያ በመፈጸም አገልግሎቱን ያገኛል፡፡
ከአውሮፕላኑ ባለቤትነት አንፃር የመንግሥት ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ለአገልግሎት ከሚሰጠው የአከፋፈል ሥልት ሁኔታ ሲታይ በኪራይም ወይም ለበረራ ብቻ በሚደረግ ከሌሎች ጋር በመጋራት ለሚገኝ አገልግሎት በሚደረግ ክፍያ ሊሆን ይችላል፡፡ አጓጓዡ ከሚሰጠው የበረራ ፕሮግራም አንፃር ደግሞ መደበኛ ወይም አልፎ አልፎ የሚሰጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዜግነት አኳያ ሲታይ ደግሞ የአውሮፕላኖቹ ዜግነት የኢትዮጵያ ወይም የውጭ አገር ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ አውሮፕላኖችም ዜግነት እንዳላቸው ወይም እንደሚሰጣቸው ይገነዘቧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መርከቦችም ዜግነት አላቸው፡፡
የንግድ አየር ትራንስፖርት ዓይነተኛ ተግባር መንገደኛን፣ ጭነትን ወይም ፖስታን ማጓጓዝ ነው፡፡ እንግዲህ ይኼንን ዓይነቱን የማጓጓዝ አገልግሎት በአውሮፕላን የሚሰጡ ከሆነ በሕግ አጠራር ‘የአየር አጓጓዦች’ በመባል ይታወቃሉ፡፡ አገልግሎት የሚሰጠው የአየር አጓጓዥም ደንበኞቹን ቀድሞ ባሳወቀው ወይም በተስማሙበት የበረራ ፕሮግራም መሠረት ማድረስ ይጠበቅበታል፡፡ ይሁን እንጂ ሁልጊዜ እንዳቀዱት ምንም ሳያዛንፉ ማከናወን የማይሳካበት ጊዜ መኖሩ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ባሰቡት መሠረት ላይፈጸሙ ከሚችሉት ተግባራት መካከል አንደኛው ውሉ ላይ በተገለጸው ጊዜ አጓጓዡ ራሱ አለመድረሱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ተጓዡ አሊያም ጓዙ በውሉ ላይ ባለው ጊዜ አለማድረሱ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ቀድሞ በታቀደው መሠረት ወደታቀደው ቦታ ላይደርስ ይችላል፡፡ በአውሮፕላኑ መዘግየት ወይም በጭራሽም ባለመሄዱ ምክንያት ተጓዦች ወይም ዕቃዎችና መልዕክቶች በወቅቱ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን መዘግየት ሊያጋጥም ይችላል፡፡
ለመዘግየቱ በምክንያትነት ሊነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሦስት መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ከአጓጓዡ ጥፋት ሊመነጭ የሚችለው ነው፡፡ ሁለተኛውም መነሻ አሁንም የአጓጓዡ አድራጎት ሆኖ፣ ነገር ግን ሆን ብሎ ሳይሆን ቸልተኛ በመሆን የተከሰተ ሲሆን ነው፡፡ በሦስተኛነት የሚነሳው ደግሞ ከአጓጓዡ ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ሳይሆን ከአጓጓዡ አቅም በላይ የሆኑ እንደ አየር ንብረት፣ የአየር ትራፊክ መጨናነቅ፣ መካኒካዊ ብልሽትና ጥገና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በመፈጠራቸው መዘግየት ሲከሰት በደንበኞች ላይ ጉዳት ማስከተሉ የተለመደ ነው፡፡ መዘግየት ጉዳትን፣ ጉዳትም ኪሳራን ይወልዳል እንደማለት ነው፡፡ የዚህች አጭር ጽሑፍ ቅኝትም የአየር አጓጓዥ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ መዘግየት በመፈጠሩ ደንበኞች ላይ የሚደርስ ኪሳራን የሚገዙ ሕግጋትን መዳሰስ ነው፡፡ በመሆኑም የሁለቱን ወገኖች ተነፃፃሪ መብትና ግዴታ ጠቅለል ባለ መልኩ ይቀርባል፡፡
በአየር ትራንስፖርት የሚሰጥ አገልግሎት በሚኖርበት ጊዜ የአጓጓዡንና የደንበኛውን ግንኙነት ሥርዓትና ደንብ የሰጠው በ1952 ዓ.ም. የወጣው የንግድ ሕግ እንደሆነ ከላይ ገልጸናል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ደንበኛ የሚለው ቃል ሁለት መልክ አለው፡፡ የመጀመርያው መንገደኛን ይመለከታል፡፡ መንገደኛው ደግሞ አንድም ሙሉ በሙሉ አውሮፕላን የሚከራይ ወይም የተከራየ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ከሌሎች ከሌሎች ተጓዦች ጋር አብሮ አገልግሎት የሚያገኝ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው የደንበኛ ዓይነት የዕቃና ጓዝ ተቀባይ ወይም ላኪ ሆኖ ራሱ ግን አብሮ የማይጓዝ ሊሆን ይችላሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱም ደንበኞች ናቸው፡፡
የአጓጓዡና የደንበኞች ግንኙነት መነሻው በዋናነት ውል ይሁን እንጂ፣ አልፎ አልፎ ከውል ውጪም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ከንግድ ሕጉ በተጨማሪ የፍትሐ ብሔር ሕጉም እንዲሁ ተፈጻሚነት አለው ማለት ነው፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻ ሳይቋጭ የሲቪል አቪዬሽን አዋጁ (ቁጥር 616/2001)፣ እንዲሁም ኢትዮጵያም ያፀደቀችው የ1944ቱ የቺካጎ ኮንቬንሽን እንደ ነገሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በመሆኑም ስለንግድ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በሚነሳበት ጊዜ እነዚህን ሕግጋት መመልከት ይገባል፡፡
ማንም ሰው በአየር ትራንስፖርት ለመገልገል ከአጓጓዡ ጋር ውል መፈጸም አለበት፡፡ ማንም ደንበኛ ክፍያ ፈጽሞ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ እንደሚከፍል ተስማምቶ ትኬት ከያዘ ውል አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ አጓጓዡ እንደ ውሉ የመፈጸም ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ትኬት የውል መኖርን ያስረዳልና፡፡
ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ፣ አንቀጽ 66 (1) ላይ የተገለጸውን ዋቢ በማድረግ ነገሩን ለማስረዳት ሲባል ክፍያ ፈጽሞ ትኬት መያዝን አመጣን እንጂ፣ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 604 እና 607(2) ላይ ከተገለጸው የምንረዳው በነፃም የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎትም ይሁን ትኬት ሳይሰጠው እንዲሳፈር የተፈቀደለት ሰው ቢሆን እንኳን ግንኙነታቸው ውል ላይ የተመሠረተ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም ትኬቱ ስለጠፋ ወይም ሳይሰጥ መቅረቱ ብቻውን ውል የለም እንደማያስብል ይኼው አሁን የጠቀስነው አንቀጽ ይገልጻል፡፡
ከትኬት ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም ‘ትኬት’ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ትኬት በወረቀት የሚታተምን ወይም ተቆርጦ የሚሰጠውን ብቻ የሚመለከት ነውን? ለማለት ነው፡፡ ይኼ ጥያቄ የሚነሳው በኤሌክትሮኒክ የሚደረግ ክፍያና ትኬት መቁረጥ በተለመደበት በዚህ ወቅት፣ እንዲሁም የትኬት ቁጥርም ጭምር በኤሌክትሮኒክ በሚላክበት ዘመን የትኬትን ትርጓሜ በወረቀት ብቻ መቀንበብ አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡
በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ይፈጸማል፡፡ የትኬት ቁጥርም በተንቀሳቃሽ ስልክና በሌሎች መልዕክት ማስተላለፊያ መሣሪያዎች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በምሳሌነት ብንወስድ እንኳን በዚሁ ዓይነት ሥርዓት ክፍያ በመፈጸም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ደንበኛውም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የተላከለትን ቁጥር ብቻ ይዞ በመሄድ የትራንስፖርት አገልግሎት ያገኛል፡፡
ውል ተፈጻሚ የሚባለው ትኬት በተቆረጠበት ጊዜ እንጂ፣ አውሮፕላን ጣቢያ ተገኝቶ ስለመሄዱ አጓጓዡ በሚያረጋግጥበት ጊዜ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ትኬት የሚለው ቢያንስ ከልምድና ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓትን ከሚገዛው አዋጅ አንፃር ሲታይ የኤሌክትሮኒክስ ትኬት ወይም ደረሰኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ውል መኖሩን ያመለክታል ማለት ይቻላል፡፡ ትኬትም ወረቀት ብቻ ሳይሆን ዲጂታልም ነው ማለት ነው፡፡
በኤሌክትሮኒክ የሚደረግን ውል በሚመለከት ግን አሁን በሥራ ላይ ያለው የውል ሕግ የማይሸፍናቸው አንዳንድ ክፍተቶች አሉበት፡፡ አንድ በሕግ ተቀባይነት የሚኖረውና የሚፀና ውል ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡
የውል ተዋዋዮቹ ውል የመዋዋል ችሎታ ያላቸው መሆን አንዱ ነው፡፡ ጉዳዩን በምሳሌ እንመልከተው፡፡ በመርህ ደረጃ አንድ ተዋዋይ ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመት የሞላው መሆን አለበት፡፡ አንድ የአሥር ዓመት ልጅ በኤሌክትሮኒክ የጉዞ ትኬት ቆረጠ እንበል፡፡ የአባቱን ወይም የእናቱን የባንክ ቁጥር ወይም የሞባይል የባንክ አገልግሎት በመጠቀም ትኬት ቢቆርጥ በዚህ መንገድ አንድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው የሚፈጽማቸው ውሎች ውጤታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ሕጉ ብዙም መፍትሔ አላስቀመጠም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ችግር የሚመነጨው ተዋዋይ ወገኖች ውሉ በሚፈጸምበት ጊዜ በአካል ባለመገናኘታቸው ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህና መሰል ኤሌክትሮኒክስ ላይ የተመሠረቱ ውሎችን ተከትለው የሚመጡ ልዩ ባህርያት የሚገዛ ሕግ ያስፈልጋል፡፡
ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ የትኬቱ ዓይነት የመንገደኞችም ይሁን የጓዝ፣ ቢያንስ የአጓጓዡን ስምና አድራሻ፣ የተሰጠበትን ቀን፣ መድረሻ ቦታ፣ ቀንና ሰዓት መያዝ አለበት፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 66 (2) ላይ እንደተገለጸው እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ የውል ሁኔታዎችን የያዘ ትኬት ተዘጋጅቶ በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አጓጓዡም ውል ላደረገበት ጓዝም ይሁን መንገደኛ፣ ትኬቱ በሚያመለከተው ቦታና ጊዜ የማድረስ ግዴታ አለበት፡፡ በመርህ ደረጃ በቀኑና በሰዓቱ መንገደኛውንም ሆነ ጓዙን ካላደረሰ አዘግይቷል ማለት ነው፡፡
አጓጓዡ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ደንብና አሠራር እስከሌለው ድረስ ዝቅተኛው የግዴታ መጠን በሕግ ተቀምጧል፡፡ መንገደኞችም ይሁኑ ዕቃ በመዘግየቱ ምክንያት ጉዳት ከመጣ፣ አጓጓዡ ኃላፊነት እንዳለበትም የንግድ ሕጉ አንቀጽ 633 ላይ ተደንግጓል፡፡ አጓጓዡና ተጓጓዡ ባደረጉት ውል ላይ በመዘግየት ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት አጓጓዡ ኃላፊነት እንደሌለበት አስቀድመው ከተስማማሙ አጓጓዡ ላይ ሊኖር የሚችል ኃላፊነት ቀሪ ይሆናል፡፡ በውል ኃላፊነቱ ካልቀረ ግን አጓጓዡ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ የሕግ ኃላፊነትን በውል ለማስቀረት ሕጉ ራሱ ቡራኬ ሰጥቷል፡፡
የሚጓጓዘው ነገር ጓዝ ወይም ዕቃ ከሆነና መድረስ ከሚገባበት ቀን ጀምሮ ሰባት ቀናት ካለፈው ተቀባይ የሆነው ሰው በውሉ መሠረት ካሳ መጠየቅ እንደሚችል አንቀጽ 625 ላይ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡
አጓጓዡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ አድርጎ ከሆነ አለበለዚያም መደረግ ይገባቸው የነበሩ ዕርምጃዎችን መውሰድ የማይችልበት ሁኔታ እንደነበር ካስረዳ ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አገላለጽ ደንበኞች ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ የማግኘት መብታቸውን ያጣሉ፡፡
ካላይ የተገለጸውን ጉዳይ በምሳሌ እንመልከተው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቶች ከሚሰጥባቸው የአየር ጣቢያዎች ውስጥ በተወሰኑት ዘንድ ራዳር የለም፡፡ በአውሮፕላን ጣቢያው አካባቢ ደመና በመኖሩ ምክንያት ለአብራሪው ጥርት ብሎ የማረፊያ አካባቢው ሳይታየው ሲቀር ከማረፊያ ቦታው ሳይደርስ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ወይም ወደ ሌላ ጣቢያ ሄዶ ማረፍ የተለመደ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የሚደርስን መዘግየት በአጓጓዡ ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ነውን ብለን ብንጠይቅ እንደ ሁኔታው መልሱ አዎንታዊም አሉታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ራዳር የመትከሉ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሆኖ ራዳር በአካባቢው ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ አውሮፕላኑ ማረፍ ሳይችል በመቅረቱ በፕሮግራሙ መሠረት መድረስ ስላልቻለና በመዘግየቱ ለሚደርስ ጉዳት የአጓጓዡ ጥፋት አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ የፈጸመውም ቸልተኝነት አለ አያስብልም፡፡ በዚህን ጊዜ አጓጓዡ (ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ) ኃላፊነት አይኖርበትም ማለት ነው፡፡ በመዘግየትም ቢሆን ለደረሰው ጉዳት የደንበኛው ድርሻ ካለበትም እንዲሁም ነፃ ሊሆን እንደሚችል በንግድ ሕጉ አንቀጽ 635 ላይ ተገልጿል፡፡
እንግዲህ አጓጓዡ ላይ ኃላፊነት የሚያስከትል ድርጊት ሲፈጸም የካሳው መጠን ምን ያህል ሊሆን ይችላል የሚለውን ማየት ይጠቅማል፡፡ በንግድ ሕጉ አገላለጽ ለጠፋም፣ ለተበላሸም ይሁን ለዘገየ ዕቃ ለአንድ ኪሎ እስከ 40 ብር ድረስ ካሳ መጠየቅ ይቻላል፡፡ በእርግጥ በኪሎ ዕቃው ዋጋ ከዚህ ዝቅ ካለ ይኼንኑ ይከፍላል እንጂ፣ የግድ 40 ብር ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን አገልግሎት ሰጪው ከዚህ የተሻለ ክፍያ መፈጸምን አይከለክልም፡፡ እንግዲህ ይህ የካሳ መጠን የዛሬ ስድሳ ዓመታት ገደማ የተተመነ ነው፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው የገንዘብ ዋጋ ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የትየለሌ ነው፡፡ ከአጓጓዡ አንፃር በብዙ እጥፍ በመርከሱ ሲጠቀሙ፣ ከደንበኞች አኳያ ደግሞ ጥቅማቸው አንሷል፡፡ በመሆኑም የንግድ ሕጉ ሲሻሻል ይህ ሁኔታም አብሮ ይሻሻል ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጓጓዡ እንደ ዕቅዱ ሳይደርስ በመቅረቱ ምክንያት መዘግየት ተፈጥሮ መዘግየቱ ደግሞ ጉዳት ቢያስከትል በምን መንገድ ካሳው ይሰላል የሚለው በራሱ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል፡፡ አጓጓዡ በመዘግየቱ ምክንያት ተጓዡ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት እንደማይኖርበት ቀድሞ ካላሳወቀ በስተቀር ለተጓዡ ካሳ ለመክፈል እንደሚገደድ ከላይ ዓይተናል፡፡ በሰዓቱ ባለመድረሱ ተጓዡ ላጣው ጥቅም አጓጓዡ ኃላፊነት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
ዕቃው ዘግይቶ በመድረሱ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ተቃውሞና አቤቱታ ማቅረብ የፈለገ ደንበኛ፣ ዕቃውን በተረከበ በ21 ቀናት ውስጥ ለአጓጓዡ ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት የንግድ ሕጉ አንቀጽ 645 ላይ ሠፍሯል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ ካሳ ይገባኛል የሚል ሰው ሲኖር ግን አውሮፕላኑ መድረስ ከነበረበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይገባዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ክስ ለማቅረብ የሚቻልበት የይርጋ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በመዘግየቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ተጓዥም ካሳ መጠየቅ የሚችለው በዚሁ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
ለማጠቃለል በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝቶ አገልግሎት የሚሰጥ የአየር አጓጓዥ በገባው ውል መሠረት በጊዜው መንገደኛንም ይሁን ጓዝን ካዘገየ ካሳ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ መዘግየቱ የተፈጠረው ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ወይም የደንበኛው ድርሻ ካለበት ካሳ የማግኘት መብት አይኖረውም፡፡ በእርግጥ አየር መንገዱ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ምኞት ቢሆንም ዜጎች ላይ የሚደርሱ እንግልትና ጉዳትም ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ በተለይ ራዳር ወደ ሌለባቸው የአውሮፕላን ጣቢያዎች የሚደረጉ በረራዎች ደመና በሚሆንበት ጊዜ ስለሚሰረዙ ደንበኞች ባሰቡት ጊዜ ሳይደርሱ ይቀራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ማሻሻል ደግሞ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ጭምር ነው፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡