Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉፈልጎ ማግኘቱ ከባድ የሆነብን ኢትዮጵያዊነት

ፈልጎ ማግኘቱ ከባድ የሆነብን ኢትዮጵያዊነት

ቀን:

በሳሙኤል አረጋ 

 በየትም ቦታና ጊዜ ያለፈው ዘመን የደስታና የሐዘን መጪው ጊዜ የተስፋና የሥጋት መሆኑ ይነገራል፡፡ በአገራችን ሁኔታ አሁን መጪው ጊዜ ከሥጋት ይልቅ የተስፋ ዘመን መስሎ ይታያል፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህ በተፈጠረው ያለመግባባትና ያለመረጋጋት ብዙ ጥፋት በመድረሱ፣ የደስታ ሳይሆን የሐዘን ወቅትን አስተናግደናል፡፡ ቂም ዘርተን በቀል አጭደናል፡፡ ተፈጥሮ የነበረው ያለመግባባት በመሪዎቻችን ድርጅት ውስጥም የነበረ በመሆኑ፣ በመላው አገሪቱ ጥፋት አንዣቦ ነበር፡፡ የአደጋው ፍንዳታ በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ የሚችልና የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ተዓምር በሚመስል ሁኔታ ያ ሁሉ የተፈራው አደጋና ሥጋት በአንድ ሌሊት ተለውጦ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ጀመርን፡፡ የረገጥነው ፈንጂ ባለመፈንዳቱ ከጥፋት ዘመን ተርፈናል፡፡ ለመትረፋችን ምክንያቱ ኢሕአዴግ በመጨረሻ ላይ የወሰነው የድርጅቱ ሊቀመንበር ምርጫ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ዓመቱን ሙሉ በውስጡ በተፈጠረው የመፈረካከስ አደጋ ተጠምዶ ነው ያሳለፈው፡፡ በርካታ ቀናትን የፈጀ የግምገማ ወቅት ነው፡፡ በአራቱም ድርጅቶች አመራር ሲካሄድ የነበረው ግምገማ እንደ ወትሮው በግለሰቦች ወሳኝነት የሚካሄድ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች ፈጠው የወጡበት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ ኦሕዴድ ሕዝቡ ባሳደረበት ከፍተኛ ጫና ከተለመደው የኢሕአዴግ መስመር ወጥቶ ሕዝባዊ አቋም ይዞ ቀረበ፡፡

በመጨረሻው የምክር ቤት ስብሰባ ኢሕአዴግ ማንን በሊቀመንበርነት እንደሚመርጥና የኢትዮጵያ ቀጣይ ተስፋ የሚወሰንበትን ደቂቃ ሕዝቡ በጭንቀት ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ዶ/ር ዓብይን መረጠ፡፡ የምርጫውን ውጤት ሕዝቡ ሲሰማ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ፣ በቀትር ፀሐይ ቀጥ ያለ ዳገት በብዙ ድካም ወጥቶ ሜዳ ላይ ከጥላ ሥር ተንጋሎ ሲያርፍ የሚሰማው ዓይነት የዕፎይታ ስሜት ነበር፡፡ የደስታና የዕፎይታ ስሜትን ያመጣው የዶ/ር ዓብይ መመረጥ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ከጥፋት የመዳን ተስፋ ነው፡፡ ሕዝቡ ዶ/ር ዓብይን በብሔራቸው፣ በድርጅታቸው፣ በዕውቀታቸው ወይም በወጣትነታቸው አይደለም የደገፋቸው፡፡ ኢሕአዴግ ከሕዝብ ጋር እልህ ተጋብቶ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል መንፈስ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ በመሆኑ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ደግሞ በኢሕአዴግ ውስጥ ከተፈጠሩት ይኼን አካሄድ ከሚቃወሙ ተራማጅ አስተሳሰብ ካላቸው ወገን ውስጥ ስለነበሩ ነው፡፡ የተቀሩት ተወዳዳሪዎች ነባሩን የኢሕአዴግ አካሄድ የሚደግፉ ስለሆነ ቢመረጡ ሕዝቡ እንደማይቀበላቸውና በቀላሉ ሊቆም ወደማይችል ሁከት መግባቱ አይቀሬ ስለሆነ ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቦታቸው ቢቀጥሉም የጥፋት ዘመኑ ተረግዞ ስለነበር መወለዱ አይቀርም ነበር፡፡

ከዚህ አደጋ ለመትረፋችን መንገዱን ወደ ቀጭኗ የሰላም መንገድ የመለሷት ሁሉ በቅድሚያ ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ በመጀመርያ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለአገሪቱ ችግር የመፍትሔ አካል እሆናለሁ ብለው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ በእርግጥም የመፍትሔ አካል ሆነዋል፡፡

ኢሕአዴግም ከያዘው አባዜ አይላቀቅም፣ በሕዝቡ ፍላጎት ሳይሆን እሱ የሚፈልገውን ብቻ ነው የሚያስቀምጠው የሚል ግምት ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በ27 ዓመታት ዕድሜው አድርጎት የማያውቀውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መቀበሉ ያስመሠግነዋል፡፡

ከዚህ በላይ ምሥጋና ያቀረብኩላቸው አካላት ሁሉ ተዓምር ሠርተው ወይም ማድረግ ከሚገባቸው በላይ አድርገው አይደለም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በመሆናቸው ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ማድረግ የሚገባቸውን ሳያደርጉ ቆይተው ይህች ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገችው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አገሪቱን ከጥፋት መልሳለች፡፡ እስከ ዛሬ ሁሉን ነገር በዚህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አሠራር ተግብረን ቢሆን ኖሮ የት በደረስን ነበር፡፡ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ ማለት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚዘልቅ እንጂ፣ ውስጥ ውስጡን የራሱን ወገን ጭምር ያሳምፃል፡፡

አሁን ማን ይሙት ኢሕአዴግ ፓርላማው ከእኔ ፍላጎት ውጪ ሰፊ ተቃውሞ ያቀርብብኛል ብሎ አስቦ ያውቃል? የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚስ ከቁጥጥሬ ይወጣል ብሎ ገምቶ ያውቃል? እንግዲህ እነዚህ የራሱ የሆኑ የቅርብ አካላቱ ይኼን ያህል ከተቃወሙት በሕዝቡ ውስጥ ያለ ስሜትን መገመት አይከብደውም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ሕዝቡ ተረጋግቷል ማለት ይቻላል፡፡ ምድሪቱም ረግታለች፡፡ አንፃራዊ ሰላምም ሰፍኗል፡፡ ይኼ ሰላም እስከ መጨረሻው ይዘልቃል ለማለት ድፍረት አላገኘንም፡፡ ለሰላሙ ዘላቂነት በመጀመርያ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሙሉ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው፡፡ ተወደደም ተጠላ የኢሕአዴግን አብላጫ ድምፅ አግኝተው የተወከሉ ስለሆነ፣ በምርጫው ላይ ተቃውሞ ያቀረቡባቸውም ሆነ ድምፅ የነፈጉዋቸው አሁን ሙሉ ድጋፍ ሊሰጡዋቸው ይገባል፡፡ ይኼ የዴሞክራሲ ዋና መርህ ከመሆኑም በላይ ኢሕአዴግን ከውድቀት የሚያድን ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ አሁን በሆነ ኩርፊያ ወይም ተቃውሞ ችግር ቢፈጠር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሄደን መውጫው እንደሚጠፋብን አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ አሁን እየተሄደበት ያለው የዶ/ር ዓብይ መንገድ እንዳስፈላጊነቱ እየተገመገመ የአገሪቱን አንድነት ጠብቆ መሄድ ለነገ የማይባል የኢሕአዴግ የቤት ሥራ ነው፡፡ የጨዋ አገር ሕዝቦች የአገራቸውን ብርቱ ችግር በራሳቸው ፈቱ መባል አለብን፡፡ ወጣቶቻችንም ብልህ፣ አስተዋይና አገራቸውን ከማንኛውም ሁከት መጠበቅ የሚችሉ ተብለው ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን አለባቸው፡፡

የወደፊቱን የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ሥራ እጅግ ከባድና የተወሳሰበ ነው፡፡ አሁን በመሪያችንም ሆነ በበርካታ ሕዝብ እየተቀነቀነ ያለውን አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ አስርፆ ሁሉም ለአገሪቱ አንድነት እንዲተጋ ለማድረግ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ አወዛጋቢና አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ የሚሰጥም ተስፋ የሚያስቆርጥም አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉዋቸው የክልል ጉብኝቶች ከሕዝቡ የወጣው ጥያቄም ሆነ ተቆርቋሪነት በሁሉም ክልሎች አንድ ዓይነት ነው፡፡ ካለፈው ተምረናልና ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን በጋራ ገንብተን፣ የጋራ አገራችን አድርገን፣ በጋራ እንጠብቃት የሚል ጠንካራ ሐሳብ አልቀረበም፡፡ ይቅር የመባባል ስሜትን አላየንም፡፡ ሁሉም ያለፈው ቁስሉን እያነካካ ከአንድ ከሆነ ተዓምራዊ አካል ካሳ የሚፈልግ ይመስላል፡፡ ሁሉም ሲያነሳ የነበረው የየራሱን ክልል መበደል፣ የየራሱን ብሔር ጥቅም መጓደል ነው በእልህና በቁጭት ሲናገር የነበረው፡፡ ተጎራባች ክልሎች የኢትዮጵያ አንድ አካል እንዳልሆኑ አንድ ጋት መሬት ከእኔ ክልል ወደ ሌላው ገብቶ ቢገኝ፣ ለሱዳን ወይም ለኬንያ ግዛታችን ተቆርሶ እንደተሰጣቸው በሚመስል ስሜት ነው ሲስተጋባ የነበረው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ነው ጣቱን ሲቀስር የነበረው፡፡ ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም የጋራ ስሜትና የጋራ ፕሮጀክትን በመደገፍ ሐሳብ አልቀረበም፡፡ የአንድም ብሔር ተናጋሪ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተነስቶ በሌሎች ብሔሮች ወይም በመላ አገሪቱ ላይ ስለደረሰ በደል አንስቶ ሲናገር አልተሰማም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይኼን ሁሉ ለማስተካከል ነው በግልጽ እየተናገሩ ያለው፡፡ ይኼንን አደገኛ አዝማሚያ እየተከተልን እንዴት ነው አንዲት ኢትዮጵያን በጋራ የምንገነባው? በዚህ ሒደት ውስጥ ነው በአፍ የምንዘምርላትን ኢትዮጵያ ፈልጌ ከሰው ልቦና ውስጥ ያጣኋት፡፡

አንዳንድ ጊዜ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የምንዘምርላት፣ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር የሚለው መፈክር ሁሉ በምናባችን ከላይ በጠቀስነው ሁኔታ ለምንታገልላት ክልላችን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ይጭርብኛል፡፡ ለዶ/ር ዓብይ መንግሥት ትልቁ፣ እጅግ ፈታኙና ከባዱ ሥራቸው ይኼ የተመሰቃቀለ በሕዝቡ ውስጥ ጥልቅ መሠረት የያዘ ክልላዊነት ወደ ኢትዮጵያዊነት የመቀየሩ ሥራ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ ሌሎች የመንግሥት አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሐሳብ አላወቅንም፡፡ ሲደግፉዋቸውም አልሰማንም፡፡ ይኼ ትችት ኦቦ ለማ መገርሳን አይመለከትም፡፡ ፈር ቀዳጅ ናቸውና፡፡

ከዚህ ቀደም የአገራችን ሁኔታ እንዳሁኑ ስለኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን፣ ስለብሔር ብሔረሰብ መብት በመንግሥት ጭምር ቅድሚያ ተሰጥቶት ሲቀነቀን ስለኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት በተደጋጋሚ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አቅርቤያለሁ፡፡ በተለይ ሰኔ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ‹እኔ እምለው› በሚባለው ዓምድ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ አሁን ያለንበትን ሁኔታ የሚመጥንና መደረግ ስለነበረባቸው ግን ያልተደረጉ ነገሮችና የሚያስከትሉት ውጤት ጽፌያለሁ፡፡ ይኼ ጽሑፍ የቀረበው የአገራችን ሁኔታ አሁን በምናየው ሁኔታ ባልነበረበትና በበርካታ አካላት ኢትዮጵያዊነት ብዙ ትኩረት ባልነበረው ወቅት በመሆኑ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ፈቃዱ ቢሆንና ይኼንን ጽሑፍ በድጋሚ ቢያቀርበው ከልቤ አመሠግናለሁ፡፡

ዶ/ር ዓብይ ተፎካካሪ የሚሏቸው እኔ ደግሞ ተቃዋሚ የምላቸው ፓርቲዎች ምን እያሰቡ ነው? ብሎ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ተቃዋሚዎች ዞሮ ዞሮ የዶ/ር ዓብይንና የፓርቲያቸውን ፕሮግራምና ሐሳብ በመቃወም አማራጭ ሐሳቦችን ይዘው ሥልጣናቸውን ለመረከብ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ይኼ የፖለቲካ አካሄድ የተለመደ በመሆኑ ሐሳባቸውን ማጣጣላቸው የሚገርም አይደለም፡፡ አሁን ለጊዜው ዋናው ጉዳይ ከሥልጣን በመለስ ያለው የአገር ህልውና ጉዳይ ስለሆነ ነው የተቸገርነው፡፡ ሁሉም ተቃዋሚዎች ተጋግዘው ሰላምን ለመመለስ መጣር አለባቸው፡፡ ያኔ ነው ተወዳድሮ በማሸነፍ ሥልጣን መያዝ የሚመጣው፡፡ ያለበለዚያ እንኳን ሥልጣን ይዘን የምናስተዳድረው፣ በተራ ዜግነት የምንኖርበትን አገር ሳይሆን ቀበሌም እናጣለን፡፡

አሁን አሁን ምሁሩም፣ ነጋዴውም፣ አርቲስቱም፣ ወዘተ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ በወቅቱ ሁኔታ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ገና ሩቅ ሆነን ሐሳባቸውን ለምንሰማ ተራ ዜጎች የሚገርመን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ ካማረ ንግግር በስተቀር ምንም የተጨበጠ ሥራ አልሠሩም፣ ወደፊትም ቢሆን ንግግራቸው የተለመደ የኢሕአዴግ የማዘናጊያ ድራማ ከመሆን እንደማይዘል የሚነግሩን አሉ፡፡ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንም በብዛት ይኼን ሐሳብ ነው የሚያስተጋቡት፡፡ ይኼ አስተሳሰብ በምንም መሥፈርት ጤነኛ አይደለም፡፡ የዚህ ሐሳብ አራማጆች ከዚህ በፊት በዋናነት ቅድሚያ ሰጥተን እንታገልለታለን ሲሉ የነበረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላልቷል፣ ሕዝቡም በብሔር ተከፋፍሏል፣ መንግሥትም የዚህ ድርጊት ዋና ተዋናይ ነው በማለት እንታገለዋለን ሲሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ በዝርዝር ቢታይ ውስብስብ ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንድምናስበው ይኼን ዓላማ ከውጭም ከውስጥም ቅዱስ ነው ብለው የሚቀበሉት ሁሉም አይደሉም፡፡ ብዙ ፅንፈኞች እንዳሉ መርሳት የለብንም፡፡ እስካሁን የነበሩት መሪዎችም ደፍረው ወደዚህ አጀንዳ ያስገቡት ምክንያት ቢኖራቸው ነው፣ ወይም በሁኔታው አምነውበት ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ግን ከበዓለ ሲመታቸው እራት ጀምሮ በተገኙበት መድረክ ሁሉ ቅድሚያ አጀንዳቸው አድርገው ይህን ለነገ የማይባል ችግር ሕዝቡን አሳምነው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ተሳክቶላቸዋል ለማለትም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን የሕዝብ መነቃቃት በማየት መመስከር ይቻላል፡፡ ይኼ አንዱና ዋናው የተግባር እንቅስቃሴያቸው መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ያለበለዚያ ይኼ ጉዳይ እንደ መድኃኒት በእንክብል መልክ አይሰጥም፡፡

በሌላ በኩል ሁሉም ተቃዋሚዎችና የሲቪል ማኅበራት በአገራችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አልተከበሩም በማለት ሲሞግቱ ኖረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም በአገራችን መንግሥት ተቀባይነት ስላጡና ወደ አገር ውስጥ ገብተውም ችግራችንን ለዓለም ሕዝብ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ሰፊ ስሞታና ተማዕፅኖ አገሪቱ ውስጥ ላሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ ግን ይኼን የቆየ የመንግሥት አቋም ወደ ጎን ገፍተው የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርን ወደ አገራችን ጠርተው ከሚፈልጉት የኅብረተሰብ ክፍልና ተቋም ጋር እንዲወያዩ አድርገዋል፡፡ ነገሩ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን፣ በዘላቂነትም ቢሮአቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ በአገራችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ከማስከበር የተሻለ ምን ተግባር አለ? ሌሎችም ተግባራት አሉ፡፡ ለነገሩማ መሪ ብዙውን ነገር የሚሠራው በአመራር፣ በንግግርና በሐሳብ ነው፡፡ ዛሬ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ለመገመት በሐሳብም ቢሆን ራስን በእሳቸው ጫማ ውስጥ አድርጎ በንፁህ ህሊና ማየት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ከስድስት ወራት በኋላ ምን እንጠይቅ ይሆን? የዚያ ሰው ይበለን ጉዱን ያሳየን፡፡

በ1966 ዓ.ም. የአብዮት ወቅት እንዳልካቸው መኮንን የሚባሉ ዕውቅ ምሁር በአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር፡፡ ወቅቱ የአብዮት ጊዜ ከመሆኑም በላይ እንቅስቃሴውን በማዕከል የሚመራ ባለመኖሩ፣ በየዕለቱ በሰላማዊ ሠልፍ የምትናጠው አዲስ አበባ ማለቂያ የሌለውና ያልተደራጁ ጥያቄዎችን በየቀኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው ታዥጎድጉዳለች፡፡ እንዳልካቸው መኮንን በጣም የተረጋጉና የበሰሉ ምሁር ነበሩ፡፡ በወቅቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነትም ታጭተው ነበር፡፡ ለቀረቡላቸው በርካታ ውስብስብ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ‹‹ፋታ ስጡኝ›› የሚል ተማፅንኦ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም በየፊናው የሚመስለውን ማድረግ ስለጀመረ፣ እንኳን ፋታ አፍታም ሳይሰጣቸው የተወሰነ የመዘጋጃ ጊዜ ከልክለናቸው ለእስርና ለሞት ዳረግናቸው፡፡ እሳቸውንም ለሞት የዳረገው አብዮት የወታደራዊ አገዛዝ ሳንጃ ወድሮ ወጣቱን አሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ በመፍጀቱ አንድ ትውልድ ጨረሰ፡፡ ኢትዮጵያም አቅጣጫዋን ስታ ዕድገቷ በፍጥነት ወደኋላ ተንሸራተተ፡፡ ምንጊዜም አዲስ ያልተረጋጋ መንግሥት ሲፈጠር ሕዝቡ በስሜት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በአብዛኛው የተቃውሞ ሐሳብ ይዞ ነው የሚቀርበው፡፡ እንዳልካቸው መኮንን የጠየቀንና የከለከልነው ፋታ ማን እጅ እንደጣለን፣ ወዴት አቅጣጫ እንደመራንና ምን እንዳሳጣን አንርሳ፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚባለውን አባባል እንፍራ፡፡ የ1960ዎቹ አብዮታውያን ወጣቶች ይኼን ድርጊትና ሌሎች ብዙዎችን ፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ ነው የአሁኑ ትውልድ እነዚህን የቀድሞ ወጣቶችና የዛሬ አረጋውያን ፖለቲከኞችን የማይፈቅደው፡፡

የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርና አጋሮቻቸው በቀድሞው የኢሕአዴግ መስመር ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ አንርሳ፡፡ ሮማን በአንድ ቀን ለመገንባት አንሞክር፡፡ ችግርን ከሌለበት ቦታ ፈልገን ለማግኘት አንድከም፡፡ ይችን ሁለት ዓመት እንያቸው፡፡ ይኼ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ለማየት ለእኛም አይረዝምም፡፡ ለእሳቸውም አያጥርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡                                                                         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...