Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየፍትሕ መጥፋት አሁንም የአገር ደዌ ነው

የፍትሕ መጥፋት አሁንም የአገር ደዌ ነው

ቀን:

በገነት ዓለሙ  

‹‹ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገር መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኬንያ በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ በኬንያው ፕሬዚዳንት ተቀባይነት ማግኘቱን›› የነገረን (ከሌሎች መካከል)፣ የኢቲቪ የሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የምሽት ዜና ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የኬንያ ጉብኝት ሰፊ ዜና ውስጥ ቀንጨብ አድርጌ ያወጣሁት ይህ ጉዳይ የተዘነጉ፣ ትኩረት የተነፈጋቸው፣ የግብር ይውጣ ሥራ የሆኑ በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን አሳሰበኝ፡፡ ብዙ አሳሳቢ ጉዳዮች ከ‹‹ጠቅላላ ዕውቀት›› ማኅደራችን ውስጥ እንኳን ጠፍተዋል፡፡ ከሕዝብ ማኅበራዊ ግንዛቤና ንቃት ውስጥ ለአንደበት ወግ ያህል እንኳን ቦታ አጥተዋል፡፡

እስቲ አንዳንዶችንና ዋና ዋናዎቹን ከአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን እያነሳን ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት በውጭ አገር የሚገኙትንና የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ስለማካተቱ፣ የእነሱንም መብትና ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታ መንግሥት ያለበት ስለመሆኑ የማያከራክር የሕዝብ ግንዛቤና ንቃት ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ጭምር ተደንግጎ የነበረ ሀቅ ነው፡፡ የተሻሻለው የ1948 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት (ማለትም ሁለተኛው የተጻፈ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት) በመጀመርያው አንቀጹ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን ይደነግጋል፡፡ አስከትሎም በዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ግዛት ‹‹ . . . ውስጥ ወይም በውጭ አገር በዜግነት የሚኖር የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤›› ይል ነበር፡፡ ዛሬ ይህንን አስረግጦ በተመሳሳይ ቋንቋና ቃላት በቀጥታ ይህንን የሚወስንና የሚደነግግ ሕገ መጥቀስ የማይቻለው ጉዳዩ የአገር ግንዛቤ በመሆኑ፣ ‹‹ሳይታለም የተፈታ›› ሀቅ ስለሆነ አይመስለኝም፡፡ ሁልጊዜም ከአዲስ የመጀመር፣ አፍርሶ የመገንባት ችግራችን አንዱ መግለጫ ነው፡፡

በ1999 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 በአንቀጽ 59/21 የምርጫ ቦርድን ሥልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀጹ፣ ‹‹በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በምርጫ የሚሳተፉበትን ሁኔታ አጥንቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ›› አደራን ለምርጫ አስፈጻሚ አካሉ ሰጥቷል፡፡ ይህ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሪፖርት አድርጎበትና ጥያቄም ቀርቦበት የማያውቅ ጉዳይ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችም ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8 ሉዓላዊነታቸውን የሚደነግግላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነባርና አሁንም ድረስ የዘለቀ ተግባር መሠረት፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ ማድረግ የመንግሥት አንዱ ግዴታ ነው፡፡ ዛሬ ሥራ ላይ ያለው ሕግም ‹‹በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብና በኢትዮጵያ ወዳጆች የተመሠረቱ ማኅበራትን ያበረታታል፣ ድጋፍ ይሰጣል፤›› ማለትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ድርሻ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ኃይልና ጡንቻ ያላቸው ሕገ መንግሥታዊ ከፍታና ቦታ የተሰጣቸው የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች አሏት፡፡ ከጥቂት አንድ ሁለት ተብለው ከሚዘረዘሩት ድንጋጌዎች በስተቀር፣ በምዕራፍ ሦስት የሕገ መንግሥቱ ክፍል ውስጥ የተካተቱት የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች ስለ ‹‹ማንኛውም ሰው›› ስለ ‹‹ሁሉም ሰዎች›› የሚናገሩ ናቸው፡፡ ስለኢትዮጵያዊ ብቻ የሚናገሩ ወይም ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተከለሉ፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆኑ ለሌሎች ማለትም ለውጭ አገር ዜጎች ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ ሰዎች ግን የተከለከሉ መብቶች በጣም የተወሰኑ ናቸው፡፡ የመምረጥ መመረጥ መብት አንዱ ነው፡፡ የንብረት መብት በከፊል ሌላው ነው፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉት ተቆጥረውና ተለይተው መዘርዘር ከሚችሉት ጥቂት መብቶች በስተቀር መብቶች ሁሉ የሁሉም ናቸው፡፡ የሰው ልጅ መብቶች ናቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም!?›› ብሎ መጮህና አቤት ማለት፣ ብሶት ማሰማትና ዕንባ ማፍሰስ፣ ቅሬታ፣ ምሬትና ቁጣ ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ በተለይ በፍትሕ ዘርፍ፡፡ የፍትሕ መብት ግን የማንኛውም ሰው ነው፡፡ እናም ያለ ሕግ ያላግባብ ላለመታሰር ለምሳሌ ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ሱዳንና ኬንያ ዜጋ መሆን አያስፈልግም፡፡ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ ወዘተ መብት በውጭ አገር ይጠበቅ ዘንድ የዜግነት አገር መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን የአገሬውም መንግሥት ግዴታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ከተደነገጉት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መካከል ማንኛውም ሰው ወይም ሰዎች ሁሉ ወይም ሁሉም ሰዎች ከማለት ይልቅ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብለው ከሚነሱት መካከል ለምሳሌ አንዱ በአንቀጽ 32 የተደነገገው የመዘዋወር ነፃነት ነው፡፡ ቃል በቃል ልጥቀሰው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው (ንዑስ አንቀጽ 1)፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ የመመለስ መብት አለው (ንዑስ አንቀጽ 2)፡፡ ይህ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነፃነት እንደ ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶችና ነፃነቶች ከላይ የሕገ መንግሥት ጥብቅ ዋስትና፣ ከታችም የዝርዝር ሕግ መቆሚያና መረማመጃ አለው፡፡

ሕገ መንግሥቱ እነዚህ መብቶችና ነፃነቶች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም አለባቸው ይላል፡፡ አሁንም ሥራ ላይ ያለውና በተለይም ደግሞ እንደ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዋጅ (2004) ባሉ ሕጎች የ‹‹ታደሰ››ው እና ‹‹የታወቀ››ው የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ዝርዝር የመኖሪያ ቦታ ድንጋጌዎች አሉት፡፡ የመኖሪያ ሥፍራን የመምረጥ ነፃነትን የሚደነግገው የፍትሐ ብሔሩ ሕግ የአንቀጽ 12 ድንጋጌ፣ ማንኛውም ሰው የመኖሪያ ሥፍራውን በሚስማማው ቦታ የመወሰንና እንደፈለገም ይህን መኖሪያ ሥፍራውን የመለወጥ ነፃነት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው የመኖሪያ ሥፍራውን በአንድ በተወሰነ ቦታ አደርጋለሁ ብሎ የሚገባው ግዴታ በፍትሐ ብሔር ሕግ አስተያየት በኩል አንዳችም ዋጋ የሌለው ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በአንድ ሥፍራ አልኖርም ወይም በአንድ በተወሰነ ሥፍራ አልደርስም ብሎ የሚገባው ግዴታ ተገቢ ለሆነ ጥቅም ምክንያት መሆኑ ካልተረጋገጠ በቀር አይፀናበትም በማለት ይደነግጋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 የተደነገገው የመዘዋወርና እንዲሁም የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነፃነት ከአንድ ቅድመ ሁኔታ በስተቀር በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 12 እንደተገለጸው የማንኛውም ሰው ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰውና የውጭ አገር ዜጋውን የሚመለከተው ‹‹ቅድመ ሁኔታ›› በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ መሆን ያለበት መሆኑ ነው፡፡ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ በሕገ መንግሥቱና በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተጠቀሱት አንቀጾች የተደነገገው የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታን የመምረጥ የማንኛውም ሰው መብትና ነፃነት፣ ኢትዮጵያ ከአሃዳዊ መንግሥት ወደ ፌዴራላዊ በመሸጋገሯ ምክንያት ሌላ ተጨማሪ ጣጣና ገደብ ይኖረው ይሆን? የፍትሐ ብሔር ሕጉ የወጣው ከሕገ መንግሥቱ በፊት መሆኑስ ለውጥ ያመጣ ይሆን? ይህን በተለይም የመጀመርያውን ብዙዎች ‹‹የቂል›› ጥያቄ ሊሉት የሚችሉትን ጥያቄ የማነሳው ማንኛውም ኢትዮጵያ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ (የግዛት ክልል ውስጥ) የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት ነፃነት አለው ብሎ የደነገገው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት መሆኑን ዘንግቼ አይደለም፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ ‹‹የፌዴራል ጉዳዮች›› ባለሥልጣናት የኢትዮጵያውያን የመዘዋወርና የመኖሪያ ሥፍራ የመመሥረት ነፃነት ‹‹ይለፍ››፣ ‹‹መሸኛ››፣ ‹‹ማስታወቅ››፣ ወዘተ ይጠይቃል ሲሉ ስለምሰማ ነው፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለ አሠራር ወይም ‹‹ውጣ ውረድ››› የደነገገ ሕግ በሌለበት አገር በአሠራር ግን ብዙ የተመዘገበ ግፍ ስላለ ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን መንግሥት ያጋጠመው የመጀመርያው በውጭ አገር የኢትዮጵያውያን የመብትና ጥቅም ጥበቃ ጥያቄ በኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ (እዚያ የተወለዱ ጭምር) ዜጎች ጉዳይ ነበር፡፡ አዲስ አገር በሆነችው ኤርትራ ውስጥ የኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም እየተረገጠ ጩኸት ሲያስተጋባ፣ በተለይም የትግራይ ተወላጆች ጥርሳቸው ሳይቀር እየተነቀለ ከኤርትራ ወደ ትግራይ ተባረሩ ሲባል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአዲሱ ጎጆ ወጪ መንግሥት ‹‹ሚዜ››ነቱ በልጦበትና አስክሮት እዚያ ሠርግና ምላሽ ውስጥ እልም ብሎ ጠፍቶ፣ የዜጎቹን አቤቱታ ሰምቶ ዳኝነት ዓይቶ ምላሽ መስጠት ቀርቶ ራሱ ተከራካሪ ሆኖ ጩኸቱን የጠላት ወሬ ነው አለ፡፡ በኤርትራ ውስጥ የኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም (ከዜግነት የመነቀልን ጉዳይ ጨምሮ) ግራ ቀኙን ያስተዋለ፣ ተባጩን ሁኔታ የመረመረና የተፈናቃዮችንም ሆነ እዚያ የታሰሩትን ዜጎች አኳኃን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምርመራና ጥናት ሳይደረግ፣ ግምገማና ውሳኔ ሳይሰጥበት ተቦትልኮ ብቻ ቀረ፡፡

በአገር ውስጥም በተለያዩ ክልሎች ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሠፍረው ባህሉን ጭምር ይዘው ይኖሩ የነበሩ የሌላ ‹‹ክልል ተወላጅ›› እና ‹‹መጤዎች›› ላይ (አማራዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች፣ ከምባታዎች፣ ሐዲያዎች) በገፍ የማፈናቀል፣ የማባረርና የመግደል ዕርምጃዎች ሲወስዱ የደነገጠና ልታረም ያለ የመንግሥት አሠራር አልነበረም፡፡ ችግሩም መደበኛ የአገር ሕመም ሆኖ ለረዥም ጊዜ ኖረ፡፡ መጀመርያ በ‹‹ነፍጠኛ ርዝራዦች›› ላይ የተወረወረ ሕገወጥ በትርና መብት ረገጣ እያሳሳቀ ሰፍቶ ለሌላውም እየተዳረሰ መጣ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሄዶ ሰቅጣጭ ግድያዎች ጭምር የተቀላቀሉበት ጎረቤት አገር ድረስ የተሻገረ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግዙፍ የግማሽ ሚሊዮን ያህል መፈናቀል መጣ፡፡

የዚህ ምክንያቱ ፌዴራሊዝም ነው ብለው የሚከሱና የሕገ መንግሥቱን በዚህ ረገድ መሻሻል የሚጠይቀ ብዙ አሉ፡፡ በእኔ በኩል ከፌዴራሊዝምና ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ የዚህ ችግር ምንጭ አሁን ያለውን አሸናሸን ለመልካም ትድድርና ለልማት ባለው ቀናነት/ቀና አለመሆን አለመመዘን፣ ከዚህ አንፃርም ካስፈለገ ሊስተካከል የሚችል አድርጎ አለመመልከት፣ ሕገ መንግሥቱ አንድ ሁለት ብሎ (አንቀጽ 47) የዘረዘራቸው ክልሎች መነካት የሌለባቸው የይዞታ ድርሻዎች አድርጎ ከማሰብ አልሻገር ያለ ብሔርተኝነት ያመጣው ጣጣ ነው፡፡

ችግሩን ያመጡትና ችግርም የሆኑት የየክልሉን የአስተዳደር ይዞታንና በዚያ ይዞታ ሥር ያለ መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን የብቻ የክልሉ የድርሻ ካርታ አድርጎ ያቃረጠ የመሰላቸው ብሔርተኞችና መሪዎች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ክልሉን ለብሔሩ የብቻ ምድሩ አድርጎ አላከፋፈለም፡፡ ብሔረሰቡን በየ‹‹መገኛ›› ሥፍራው አልገደበም፡፡ እዚያ ውስጥ የሚያጥር፣ በተከለለ ሥፍራው ውስጥ የሚያስርና የሚገንዝ አይደለም፡፡

ለተግባባ ትድድርና ለልማት ምቹ ሁኔታ ተብሎ የተወሰነውንና ያንንም እስካገለገለ ድረስ ብቻ የሚቆየውን አሸናሸን ሕገ መንግሥቱ የየብሔረሰቡ ወይም የየማኅበረሰቡ የብቻ ምድርና የድርሻ ካርታ አድርጎ ቢሸልም ኖሮ፣ የአንቀጽ 32 ዓይነት የሁለታችንም መብቶች (የማንኛውም ዜጋ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ ጭምር በመረጠው የአገሪቱ ግዛት ውስጥ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት) ባላስፈለጉም ነበር፡፡ የዜግነትና የእኩልነት መብትም እንደዚሁ፡፡ የእኩልነት መብት ማለት ማኅበረሰቦች (አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ . . . ) ባለቤትና መጤ፣ ባላገርና ባይተዋር ተባብለው የማይላተሙበት፣ በመብት የማይበላለጡበት፣ አንዱ አሽቆጥቋጭ ሌላው ተሸቆጥቋጭ አዳሪ የማይሆኑበት እኩል የዜግነት ግንኙነት እንዴት ሊኖር ይችላል?

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የባህር ዳር ንግግር ውስጥ ይህንን ጉዳይ የሚመለከተውን በሰፊው የምጠቅሰው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ . . . እኔ ከአማራም በላይ፣ ከኦሮሞም በላይ ሱዳናዊም ከመጣ፣ ጀርመናዊም ከመጣ፣ እንደ ሰው የምናከብርበትና ሰው ክቡር መሆኑን የምናስብበት ጊዜ ይምጣ ባይ ነኝ፡፡ ሰው ክብር መሆኑን ስናስብና ስናምን፣ ፍቅር እንደሚገባው ስናምንና ስናስብ፣ ከዚያ የአማራ፣ የሌላ፣ የኦሮሞ ጉዳይ እያነሰ ነው የሚሄደው፡፡ አሁን ሰው ነው ክብር ያጣው፡፡ ሰው ነው እየተባረረ ያለው፡፡

‹‹እኔ በተወለድኩበት አካባቢ ልጅ እያለሁ ትንሽ ቀደም ብሎ (በኋላም አንዳንዶቹ ነበሩ) በርካታ የመኖች ነበሩ ዳቦ ቤት ያላቸው፡፡ ግሪኮች ነበሩ፣ ጣሊያኖች ጋራዥ ቤት ያላቸው ነበሩ፡፡ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ በእኛ መንደር የሌለ ሰው የለም፡፡ አንዳንዱ ስሙን ብነግራችሁ የማታወቁት የብሔር ስም ሁሉ አለ እዚያ አካባቢ፡፡ ያው ጅማ እንደምታውቋት ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ ብዙ ሕዝብ እያየን ነው ያደግነው፡፡ አሁን ችግሩ የመንና ግሪክ ሳይሆን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ ሆነና አሳፋሪ ቦታ ላይ ደረሰ ማለት ነው፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት ሱዳን ሄጄ ነበር፡፡ ዳያስፖራ ላወያይ ሱዳን ሄጄ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ (እነሱ አንድ ሚሊዮን ነው ያሉኝ እኔ ላለማጋነን ነው መቶ ሺሕ የምለው) አንድ ሚሊዮን ገደማ ሕገወጥ፣ ፓስፖርት የሌላቸው፣ መታወቂያ የሌላቸው፣ ዕድሜያቸው አሥራ ሦስት፣ አሥራ አምስት በጣም ሕፃናት የሆኑ (በርካቶች) ኢትዮጵያውያን ሱዳን ውስጥ አሉ፡፡ በጣም ልጆች ያውም ሴቶች የሚበዙበት፡፡ እና እነሱን አነጋግሬ የሱዳን መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ስንነጋገር መታወቂያ የላቸውም፣ ፓስፖርት የላቸውም፣ አስረን ሕገወጥ ብለን እንዳንመልስ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሆኑብን፡፡ የወንድም አገር ሕዝብ ሆኑብን ሲሉ ተመለስኩና ለጓደኞቼ እዚህም ያሉ ያውቃሉ፡፡ እኛ ክፉ ሕዝቦ ነን፡፡ እንኳን በመቶ ሺሕ የሚቆጠር አሥር አሥራ አምስት ሱዳን አዲስ አበባ ላይ (ባህር ዳር አላልኩም፣ ጋምቤላ አላልኩም) አዲስ አበባ ቢመጣ ምን ነበር የምናደርገው እኛ? እነሱ ግን ሕፃናት ሰብስበው እየኖሩ ነው፡፡

‹‹ዓለም ለሁሉም ሰው መዘዋወሪያ ስትሆን ጥሩ ነው፡፡ አሜሪካ አገር ተሰደው ተቸግረው ተባረው ወይም ሥራ ፈልገው ትምህርት ፈልገው የሄዱ ኢትጵያውያን ትንሽ እንደቆዩ ዜጋ ይባላሉ፡፡ እዚህ ተወልደው እዚህ አድገው እንግሊዝኛ በቅጡ የማይናገሩ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ነህ አንተ፣ ጥቁር ነህ፣ ሳይባል ዜጋ አድርጎ አቅፎ የሚያኖር ዓለም ያለበት፣ እንዴት ኢትዮጵያውያን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ የመኖር ዋና አጀንዳ መነጋገሪያ ይሆናል? ሌላስ ቢመጣ ምናለበት? ሰላም እስካለ ድረስ በሥርዓት እስከሠራ ድረስ፣ ሕግ እስካከበረ ድረስ፣ ለሰው ክፍት መሆን አለበት፡፡ ልባችንም፣ አዕምሯችንም፡፡ መጪውን ዘራፊ መሆን የለበትም፡፡ መጪውን ሕግ የሚጥስ መሆን የለበትም፡፡ መጪው ወንድም ሆኖ የሚኖር ሕዝብ ከሆነ ያ አብሮነት ቢፈጠር ጥሩ ነው . . . ››

በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት የኢቲቪ ዜና ሁለት ቁም ነገሮች ይዟል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገር ሁሉ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሌላው በሱዳንና በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ ነው፡፡ የመጀመርያው በመደበኛነት የሚሠራ፣ በግንባር ቀደምትነት በኤምባሲዎችቻችን አማካይነት የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ የማድረግ የመንግሥት ተግባር የተሰጠው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ የዚህ የበላይ ኃላፊ ዞሮ ዞሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡

እግረ መንገዳችንን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተሰጠው በዚህ ሥልጣን ድርሻ ውስጥ የተካተተውን ሌላውን ጉዳይ ገረፍ አድርገን ዓይተን እንለፍ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብና በኢትዮጵያ ወዳጆች የተመሠረቱ ማኅበራትን የማበረታታትና ድጋፍ የመስጠት ሥልጣን ጭምር አለው፡፡ ከዚህ ማዕዘን ሲታይ አገር ውስጥ ያለነው ዜጎች ማኅበር የማቋቋም መብታችን ራሱ ይገርመኛል፡፡ በተለይም ደግሞ የኬንያውያን ወዳጆች ማኅበር፣ የሱዳናውያን ወዳጆ ማኅበር፣ ወዘተ ብሎ ማቋቋም ‹‹ይሞከር›› እንደሁ ሳስብ ይበልጥ ይገርመኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመርያ በሱዳን ቀጥሎም በኬንያ እስረኞች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ ነገር ግን ተወዝፎ የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ውስጥም፣ በየክልሉና በየቦታው በውጭ አገርም ቢሆን ያላግባብና ያለሕግ አለመታሰራቸውን፣ የታሰሩትም እንዲፈቱ መታገልና መከላከል ጭምር የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ መንግሥት እስረኞችን የመፍታት የካቲት አካባቢ የጀመረውንና ከሁለት ወር የበለጠ ጊዜ አይወስድብኝም ያለውን ቃሉን አጠናክሮ ሊገፋበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያረጋግጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህም አገር የሱዳን፣ የኬንያ፣ የእንግሊዝ፣ ወዘተ ዜጋ የሆኑ እስረኞች አሉ፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያበሰሩት የፍቅር፣ የይቅርታና የምሕረት ዘመን ይህንን ሁሉ ማጠቃለለልና ማካተት አለበት፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ከተጠናወተው ችግር መላቀቀና በአዲስ ሙሽት ሥራውን መጀመር አለበት፡፡ በኢትየጵያ ውስጥ የታወጁ ሕገ መንግሥቶች ሁሉ ማንኛውም ሰው በወንጀል ቢጠረጠርም፣ ቢከሰስም ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ካልተረጋገጠ በስተቀር እንደ ጥፋተኛ አይቆጠርም ይላሉ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 20(3) ይህንኑ ይደነግጋል፡፡ እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት በሕግ በተደነገጉትና ለሕገ መንግሥቱ በገበሩ ልዩ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር ቅድመ ፍርድ እስራትን፣ የዋስ መብት መንፈግን፣ የተፈረደበትና ቅጣት የተወሰነበትም ሰው እንኳን ቢሆን ይግባኙን አሟጥጦ እስኪጨርስ ድረስ ማሰረን ይከለክላል፡፡ ፀንቶ የቆመውን ሕግ ጥሶ ብርቱ ጥፋት/ወንጀል በመሥራት ላይ ካልተገኘ በቀር ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አይታሰርም ማለት ሁልጊዜም የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሕግ ሆኖ ቢኖርም፣ የዋስትና ሕግ ሕገ መንግሥታዊ ቦታ ቢሰጠውም፣ ሀቀኛና ትክክለኛ ዳኝነት የማግኘት መብት የሰው ልጆ መብት ቢሆንም፣ የፍትሕ ዕጦት የኢትዮጵያ ሕመም ሆኖ አሁንም አለ፡፡ የግፍ ውንጀላ፣ የግፍ እስራትና የስቃይ ምርመራ ጭምር የማስወገድ ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት ሳይደረግ በተለይም በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ መንግሥታዊ በደልና ግፍ ሕግና ፍትሕን ዱላ አድርጎ መጠቀምን የሚያጋልጥና የሚያስቆም ምዕራፍ ሳይጀመር፣ የእስረኞችና የእስር ቤቶች ሁኔታ ባለበት አሳፋሪ ይዞታና ገጽታው ይቀጥላል፡፡      

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...