Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የመንግሥት ኃላፊዎች ስለግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት መናገር ቢያቆሙም ስትራቴጂውን ግን ከወደቀበት በማንሳት መተግበር አለባቸው››

ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፣ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ

ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፣ በኢኮኖሚና በግብርና ሳይንስ መስክ ለዓመታት የካበተ የፊልድም፣ የስኮላርም ልምድ አላቸው፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በተመድ ውስጥ አገልግለዋል፡፡ ጡረታ እስከወጡበት እስካለፈው ዓመት እንኳ በተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የቻይና ዳይሬክተርና የፕሮግራሙ ተወካይ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በቻይና ቆይታቸውም ለተቋሙ የልቀት ማዕከል እንዲከፈትለት አድርገዋል፡፡ በላይቤሪያም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተርና ተወካይ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በደቡባዊ አፍሪካ፣ በመካከለኛውና በግሬት ሌክስ አገሮች ውስጥም በተለያዩ ኃላፊነቶች መሥራታቸውን ግለ ታሪካቸው ይዘክራል፡፡ በሱዳን የፕሮግራም አማካሪ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በመካከኛው አውሮፓና በዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤት የአጋርነትና አቅም ግንባታ ልማት አገልግሎት መስኮች በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ኬር ኢትዮጵያ እንዲሁም ኬር ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት ባልደረባም ነበሩ፡፡ ከአለማያ እስከ ጀርመንና እንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀዳ የትምህርት ዝግጅታቸው ታክሎበት፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የምርምር ውጤቶችን በግብርና ዙሪያ አሳትመዋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያተኮረ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ቅኝቱን ያሳየ መጽሐፍ ያሳተሙት እ.ኤ.አ. በ1995 ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ የጻፉትና ‹‹Overcoming Agricultural and Food Crises in Ethiopia›› የተሰኘው መጽሐፍ በመጪው ሳምንት ይመረቃል፡፡ በመጽሐፉ ያሰፈሯቸውን አንኳር አንኳር የኢትዮጵያ ግብርና ችግሮችን በማስመልከት ብርሃኑ ፈቃደ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ ያጠነጠነውን መጽሐፍ ለምንድነው የጻፉት? ለመጻፍ ያነሳሳዎትስ ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- መጽሐፉን የጻፍኩት ከቁጭት በመነሳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ጥንት በኒዮሊቲክ ዘመን ከነበሩ አሠራሮች አኳያ ሲታይ ብዙም ለውጥ አለማሳየቱ ያስቆጫል፡፡ በዓለም ዙሪያ የመጓዝ ዕድሉን በማግኘቴና በቅርቡ እንኳ በተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የቻይና ወኪል በመሆን በሠራሁባቸው ጊዜያት ግብርናቸው እንዴት እንዳደገ፣ እንዴት የአነስተኛ ይዞታ ግብርናን እንደለወጡት ለማመን ይከብዳል፡፡ በዘመናዊው የግብርና ታሪክ ውስጥ አዲስ ነገር ነው ያሳዩት፡፡ በላቲን አሜሪካ አገሮች በተለይ በኤኳዶር፣ በፔሩ፣ በብራዚልና በሌሎችም አገሮች ውስጥ የሚታየው ግብርና በእጅጉ የተራመደ በመሆኑ ኢትዮጵያን ስታስባት ያስለቅስሃል፡፡ ወደ አገር ቤት ስንመለስ ግብርናችን የጥንት የግብርና መሣሪያዎች ማሳያ ሙዚየም ነው የሚመስለው፡፡ በመሆኑም እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ለእኔ ቁልፉ ጥያቄ የለውጥ ቀስቃሽ በመሆን ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ገበሬውን፣ አስተማሪውን፣ አጥኚውንና ሌላውንም ወገን በማሳሰብ ከአሥር ሺሕ ዓመታት በፊት ከነበረው የግብርና ዘዴ ለምን ስንዝር መራመድ እንዳልቻልን በመጎትጎት ለለውጥ እንዲነሱ ማስተጋባት ነው፡፡ በግብርናው ላይ ለምን ጥገናዊ አሠራር ብቻ እንከተላለን? ለምንድነው ሰው በሕይወት እንዲቆይ ብቻ የሚያደርግ አሠራር ላይ የምናተኩረው? እነዚህ ጉዳዮች ናቸው ይህንን መጽሐፍ እንድጽፍ ያነሳሱኝና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በግብርናው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ በማሰብ ጭምር ነው የጻፍኩት፡፡   

ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ የትውልድ መንደርዎ ዶሻ የተገለጸችበት መንገድ ቀልብ ቢስብም፣ ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ በተለይም የጭላሎ ግብርና ልማት፣ እንዲሁም ኋላ የአርሲ ገጠር ግብርና ልማት ፕሮግራሞችና የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ቀድመው ከተተገበሩባቸው አካባቢዎች አንዷ በመሆን የሜካናይዝድ ግብርና ቢጀመርባትም፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ብዙም ለውጥ እንዳላሳየች ጠቅሰዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የነበረው ችግር ምን ቢሆን ነው ለውጥ ሊታይ ያልቻለው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ይህ የመጽሐፉ ዓምድ የሆኑትን ጉዳዮችና ኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ ለምን ግብርናዋ ለውጥ ማሳየት እንዳልቻለ እንዳብራራ የሚጋብዝ ጥያቄ ነው፡፡ ዶሻ እነዚህን ነጥቦች በምሳሌነት ታሳያለች፡፡ ግብርና ሳይንስ ነው፡፡ ሆኖም የሰዎች ምልክታና ትዝብትም አይጠፋውም፡፡ በመጽሐፉ ሦስት ወሳኝ ነገሮችን አንድ ላይ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ አንደኛው ጊዜ ወይም የለውጥ ሒደት ብዬ ያልኩት ነው፡፡ ሁለተኛው በመዋቅር ላይ በማተኮር ተቋማት በጊዜ ሒደት ያሳዩትን ለውጥ መመልከት ነው፡፡ ሦስተኛው ነጥብ አፈጻጸም ወይም ትግበራ ነው፡፡ ይህም ጥሩ የኑሮ ደረጃን የሚመለከት ነው፡፡ ዶሻ እነዚህን ሁሉ በምሳሌነት ትወክላለች፡፡ በዚያን ጊዜ የአርሲ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ጋር በቅርብ ርቀት ላይ ትገኝ ስለነበር የጭላሎ ግብርና ልማት፣ እንዲሁም ኋላ ላይ የአርሲ ገጠር ግብርና ልማት ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የመጀመሪያ ተጠቃሚዋ ዶሻ ነበረች፡፡ የቀበሌ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማግኘት ከቻሉ የዚያን ጊዜ አካባቢዎች የመጀመርያዋ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ ይሁንና ይህ ሁሉ ተደርጎም የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት አልተሻሻለም፡፡ ጥሩ የኑሮ ደረጃ ስለሚባለውና የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት ከነበረው ለምን እንዳልተለወጠ እንመለከታለን፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪ ቤተሰቦች ብዛት በሦስት እጥፍ ጨምሯል ማለት ይቻላል፡፡ አካባቢው፣ የደኑ ይዞታ፣ የዱር እንስሳቱ በሙሉ ሙልጭ ብለው ጠፍተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመሬት እጥረት ትልቁና ዋናው ፈተና ነው፡፡ ወጣቶች ወደ ከተማ አካባቢ ለትምህርትና ለሥራ ፍለጋ ይሰደዳሉ፡፡ ነዋሪዎች የባንቧ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በማሳቸው ያመረቱትን በአህያ፣ በፈረስ፣ ሲከፋም በትከሻቸው ተሸክመው ወደ ገበያ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያን ቁልፉ ጥያቄ የሚሆነው በእንዲህ ያለው ሁኔታ እስከ መቼ እንቀጥጣለን? የሚለው ነው፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ መንደሮች አኳያ ስትታይ ዶሻ የምግብ እጥረት ላይታይባት ይችላል፡፡ ይህ በአዎንታዊነት ሊታይ ቢችልም ድህነቱ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ሕዝቡ ወደ ዕርዳታ ተቀባይነት እያዘገመ መሆኑ ነው፡፡ የሰብል ምርት ችግር ውስጥ ከገባ ዶሻ የእህል ዕርዳታ መፈለጓ አይቀሬ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሜካናይዜሽን ከተነሳ አይቀር በኢትዮጵያ ያለው የትራክተር ሥርጭት በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በካናዳና በአሜሪካ ካለው አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለ1,000 ሕዝብ 0.04 ትራክተር መሠራጨቱን የሚያሳይ አኃዝ በመጽሐፍዎ ተጠቅሷል፡፡ ይህ የሆነውና እየሆነ ያለው ለምንድነው ይላሉ?  

ዶ/ር ጌታቸው፡- ይህ ትልቁን ትንታኔ እንድንመለከት ይጋብዛል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ነበር የግብርና ሜካናይዜሽን የተጀመረው፡፡ በጣም ጠቃሚ በሆነ መንገድ የሜካናይዝድ ግብርና መነሳት ጀምሮ ነበር፡፡ የመሬት ባላባቶችም በትራክተር ማረስ እንደሚቻል አውቀው ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያ በመካከኛው ሸዋ፣ በአርሲ፣ በባሌና በሌሎችም አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎችን ማፈናቀል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በቅድመ አብዮት ዘመን በተለይም ‹‹መሬት ላራሹ›› ከሚለው መፈክር ጅማሬ የትራክተር ጉዳይ እያበቃለት መጥቷል፡፡ አዲሱ መንግሥት የመሬት ሪፎርም በማካሄድና የግል እርሻዎችን በመውረስ የመንግሥት እርሻዎችን ማስፋፋት ሲጀምር፣ የሜካናይዜሽን ጉዳይ መዳፈን ጀመረ፡፡ የመንግሥት እርሻዎች እንደተጠበቀው ውጤት አላመጡም፡፡ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥትንም ስናይ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረው አካሄድ በአነስተኛ ገበሬው ላይ ያነጣጠረ የለውጥ አጀንዳ ይዞ ብቅ በማለቱ ነገሩ ሁሉ ተለወጠ፡፡ ሜካናይዜሽን በዚህ ሒደት ውስጥ አነስተኛ ይዘት ያለው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህም አካሄድ ለውጥ አላመጣም፡፡ የገበሬው ይዞታ በየጊዜው እያነሰ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት የአብዛኛው ገበሬ የመሬት ይዞታ ግማሽ ሔክታር ሆኗል፡፡ ሰባት ሚሊዮን አባወራዎች ከግማሽ ሔክታር ባነሰ መሬት ይተዳደራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የትኛውንም ዓይነት የግብርና ሜካናይዜሽን ለመተግበር የሚያበቃ መሬት አይደለም፡፡ ሌሎች አራት ሚሊዮን አባወራዎችም ከግማሽ እስከ አንድ ሔክታር መሬት በማረስ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በድምሩ 63 በመቶውን የአገሪቱን ገበሬ የሚወክሉት እነዚህ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ናቸው፡፡ የሜካናይዝድ ግብርናም ሆነ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲህ በተበጣጠሰና በተበታተነ የመሬት ሥሪት ላይ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይህ አንዱ ኢትዮጵያን ያጋጠማት ትልቅ ፈተና ነው፡፡

ጥያቄህ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች አገሮች አኳያ የምትገኝበትን ደረጃ ለማየት የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእጅ ማረሻ በስፋት የምትገለገል አገር በመሆኗ፣ ከትራክተር አኳያ ከመጨረሻዎቹ ተርታ ላይ ከሚገኙ አገሮች በቀዳሚነት ትቀመጣለች፡፡ የእጅ ማረሻ፣ የኒዎሊቲክ ግብርና ከአሥር ሺሕ ዓመታት በፊት የቴክኖሎጂ ለውጥ ያሳየባቸው መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በበሬ የሚጠመድ ሞፈርና ቀንበር ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት ከሰባት ሺሕ ዓመታት በፊት ነው፡፡ በዚያን ወቅት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የተደረሰባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከሰባት ሺሕ እስከ አሥር ሺሕ ዓመታት በፊት በነበሩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተንጠላጥላ ትገኛለች፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች ናቸው እንግዲህ ምርት አምርተው 100 ሚሊዮን ሕዝብ ለመመገብ ሥራ ላይ እየዋሉ ያሉት፡፡ በዚህ ዘመን ከሚታየው የለውጥና የቴክኖሎጂ ግስጋሴ አኳያ በኢትዮጵያ የሚታየው ነገር ልብ ይሰብራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ 12 የሜካናይዜሽን ደረጃዎች አሉ፡፡ አገሮች ባለሁለት እግር አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ካለው ትራክተር በመውጣት እጅግ ውስብሰብ የሚባሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ከኢንዱስትሪ ለውጥና ከዲጂታል አብዮት ጋር አዋህደውና አዛምደው መገስገስ ችለዋል፡፡ እኛ ከዚህ ውጪ ነን፡፡ ከታችኛው ግርጌ ሥር እንገኛለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የቀደምት የግብርና ሥልጣኔ ምልክት የሆኑ አሠራሮችንና መሣሪያዎችን በመጠቀም ረገድ ህያው ሙዚየም እንደሆነች በመግለጽ የግብርና ዘርፏን ኋላቀርነት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ይህ ወደፊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊለወጥ ይችላል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ይህ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ግብርናዋን ከመቀየር ውጪ ሌላ ምርጫ የላትም፡፡ ከቋጥኙ አፋፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ ሕዝቧን መመገብ ከባድ ሊሆንባት የሚችልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በመሠረቱ ግብርና ገበሬውን ይመግባል፡፡ ይህ መሠረታዊው ነገር ነው፡፡ ገበሬው ትርፍ ካመረተ ግን አንተንና እኔን ይመግባል፡፡ ይህ ግን አሁን የተገላቢጦሽ ሆኖ፣ አብዛኛው ገበሬ ራሱን እንኳ መመገብ አልቻለም፡፡ ራስን መመገብ መቻል ማለት ደግሞ ምግብ ማግኘት መቻል ብቻ አይደለም፡፡ መመልከት የሚገባን አራት ደረጃዎች አሉ፡፡ አንደኛው ግብርና ለጥሩ ኑሮ የሚያበቃ ነገር ማቅረብ መቻል አለበት የሚል ነው፡፡ ለገበሬው ምግብ ማስገኘት አለበት፡፡ ለአገሪቱም ትርፍ በማምረት አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ ይህ ወሳኝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን ወሳኝ የግብርና ተግባር እያጣነው ነው፡፡ ሁለተኛ ግብርናው ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚውል የፍጆታ ወጪን መሸፈኛ ማስገኘት አለበት፡፡ ሦስተኛ ግብርና ልማዳዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ለመተካት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ ለግብዓት፣ ለማዳበሪያ፣ ለዘር የሚውል ገቢ ማስገኘት አለበት፡፡ አራተኛውና ግብርና የኢኮኖሚው ቁልፍ ምሰሶ የሚያኘው ነገር ሥጋትን ለመሸከም የሚያስችል አቅም መፍጠር ሲችል ነው፡፡ ከአሥር ሺሕ ዓመታት ጀምሮ ግብርና ለሥጋት የተጋለጠ ዘርፍ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በሥጋት የተሞላ ነው፡፡ በመሆኑም ኪሳራን ለመሸፈን ብዙ ማምረትና የተመረተውን ትርፍ ምርት በማከማቸትም ቀውስ ሲያጋጥም መጠቀም ድሮም የነበረ አሠራር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ግን ይህን ሊያደርግ ባለመቻሉ ሥጋትን ለመሸከም አላስቻለም፡፡ ግብርና ሀብት መፍጠር መቻል አለበት፡፡ ይሁንና ፖለቲከኞቻችንና ጥቂት ምሁራን ሰዎች በሕይወት ስለቆዩና በረሃብ ስላልሞቱ የሚኩራሩ ይመስላሉ፡፡ ይህንን ደረጃ ግን ማለፍ ነበረብን፡፡

በግብርናው መስክ የትራንስፎርሜሽን ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የልማት ፍልስፍናችንን ደግመን ልንቃኘውና ዳግመኛ ልናስብበት ይገባናል፡፡ የተቋማት ፍልስፍናችንን፣ ባህላችንን፣ እሴቶቻችንና ልማዶቻችንን ልንመለከታቸው ይገባናል፡፡ የወጣቶች አመፅና ሌሎችም መንግሥት ላይ የተጋረጡት ፈተናዎች በእርግማን የመጡ አይደሉም፡፡ ወጣቱ ሥራ ባገኝ፣ ጥሩ ኑሮ ባገኝ እያለ ከገጠሩ ክፍል እየተሰደደ ነው፡፡ ከግብርናው ኢኮኖሚ የሚሰደዱት ወጣቶች ግን ባሉበት ሆነው ውጤታማ እንዲሆኑ መደረግ ነበረባቸው፡፡ ግብርናው እንደ ስፖንጅ በመሆን ብዙዎች ሥራ እንዲያገኙ ማስቻል ነበረበት፡፡ የቱንም ያህል አድካሚም ቢሆን ወጣቱ ከዚህ ቀደም ለመኖር የሚያስችለውን ሥራ ከግብርና ያገኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መሬት አልባ በመሆኑ ሠርቶ መኖር አልቻለም፡፡ የሰብል ምርት በአብዛኞቹ ትንንሽ ማሳያዎች የመክሰም ሥጋት እያሳደረ ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቶቹ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሥራ ለማግኘት ወደ ከተማ መፍለስ ነው፡፡ ይህ ለህልውና ሲባል በኢትዮጵያ የሚታይ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ግልጽና ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ መንግሥት ለሁሉም የአገሪቱ ወጣቶች ሥራ መስጠት አይችልም፡፡ ሆኖም ለውጣቱ ሥራ ማግኘት የሚረዳው አንዱ የአገልግሎት ኢንዱስትሪው ነው፡፡ ሌላው የገጠሩ ክፍል ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋበት በማድረግና የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት መንግሥት የሥራ ዕድል ማመቻቸት ይችላል፡፡ ይህ ነው በኢትዮጵያ ሰላም የሚያመጣው፡፡  

ሪፖርተር፡- በመንደር የማሰባሰብ አሠራርን በተመለከተም በመጽሐፍዎ እንደተጠቀሰው፣ በደርግ መንግሥት ወቅት 12 ሚሊዮን ሰዎች በመንደር ተሰባስበው ነበር፡፡ ይህ አሠራር ግን በዚህ መንግሥትም አለ፡፡ ከዚህ አኳያ በቀደመውና በአሁኑ መንግሥት መካከል የተካሄደው የመንደር ማሰባሰብ አካሄድ አንድነቱና ልዩነቱ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጌታቸው፡- በመንደር የማሰበሳብ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ፖለቲካዊ ቅኝት ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ የዚህ አሠራር ትልቁ መገለጫው የሕዝቦች ፍልሰት ነው፡፡ ከታሪክ እንደምንገነዘበው ለዘመናት ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ኖረዋል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመነ መሳፍት ፍፃሜን ተከትሎ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ መውደቂያው ሲፍገመገም የነበረው በምግብ እጥረት ሳቢያ ነበር፡፡ ሆኖም ከወሎ፣ ከጎንደርና ከሌሎችም አካባቢዎች ሕዝቡ ወደ አርሲ፣ ባሌና ወደ ደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍሎች በመሰደዱ የግብርና ምርት መስፋፋት ከመቻሉም በላይ፣ ቡና ወደ ውጭ መላክ የጀመረውም በዚህ ወቅት ነበር፡፡ በአንድ ጎኑ የሰዎች መሰደድ አዎንታዊ ጥቅም ቢኖረውም በሌላ ጎኑ ግን ጉዳት ነበረው፡፡ ብዙም ያልታረሰው፣ በአብዛኛው በእንስሳት ሀብቱና በሥራ ሥር ተክሎች የሚተዳደረው ማኅበረሰብ ደን መመንጠርን ተሰደው ከመጡት ሕዝቦች ተምሯል፡፡ ከፍተኛ የመሬት ጉዳት ከደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሰደው የመጡ ሰዎች መሬት ማዘጋጀትንና እርሻን በማስተማር ለከፍተኛ የደን መመንጠር አስተዋጽኦ ያደረገ ልማድ አስርፀዋል፡፡ በመንደር መሰባሰብን ከከተሜነት መስፋፋት አንፃር መመልከት አለብን፡፡ ይህ መንግሥት የተከተለው የመንደር ማሰባሰብ ሥርዓት በደርግ መንግሥት ይተገበር ከነበረው በመውሰድ ነው፡፡ ሰዎችን ለእርሻ ተስማሚ ወደ ሆነ ቦታ በመውሰድ ማስፈር ነው፡፡ በቅንነት ካየነው አብዛኛው ሕዝብ በገጠር የሚኖር እንደ መሆኑ መጠን፣ ኢትዮጵያ ሥርዓት ባለው አኳኋን ከተሜነትን ማስፋፋት አለባት፡፡ ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌሎች ከተሞች የሚሰደደው ወጣት ብዙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሠረታዊ አቅርቦቶችንና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ በፍጥነት ለሚጨምረው የሕዝብ ብዛት ማዳረስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም ወሳኝ የከተሜነት ስትራቴጂ እንዲቀየስ ያስገድዳል፡፡ በአጭሩ ለጥያቄው መልስ በመንደር ማሰባሰብ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንደር ማሰባሰቡ ግን የሚመከር አሠራር ነው ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ጌታቸው፡- በሚገባ፡፡ መታየት ያለበት የገጠሩን ክፍል ወደ ከተሜነት ለመቀየር ከሚያስችል ዕይታ ነው፡፡ አገልግሎቶችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ የመሬት አጠቃቀምንና ሌሎችንም ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ማስገባትን ይጠይቃል፡፡ መሬት ያላቸው አካላት በመሬቱ ላይ እሴት ሊጨምሩበት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ጥቅም ሳይሰጥ የተቀመጠውን ካፒታል ወደ ኢንቨስትመንት ካፒታል መቀየር የሚቻለው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እያደገ የመጣ የመሬት አልባነት ችግር እንዳለ ሲጠቅሱም፣ በሕዝብ ብዛት ሳቢያ በአሁኑ ወቅት አሥር ሚሊዮን ያህል ሕዝብ መሬት አልባ እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ጌታቸው፡- የመሬት ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ከ0.1 ሔክታር የማይበልጥ መሬት አላቸው፡፡ በተግባር ሲታይ እነዚህ ሰዎች በዚህች ትንሽ የመሬት ይዞታቸው ምክንያት ምንም የሚረባ ነገር መሥራት ያልቻሉና መሬት እንደ ሌላቸው የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እንኳንና በ0.1 ሔክታር መሬት፣ በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ እንኳ አምስት አባላት ያሉትን አንድ ቤተሰብ መመገብ አትችልም፡፡ መሬት አልባነት በጣም ሥር የሰደደ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡ ወጣቱ ከመሬት ባለቤትነት እየተገፋ በብዛት ለስደት እየተዳረገ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ይቁጠሩት፡፡ እርስዎ ለሚያቀርቧቸው ችግሮች የእነሱ ምላሽ ‹‹የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን እያስፋፋን ነው፡፡ በዚህን ያህል ጊዜ ውስጥ ምርትና ምርታማነትን እየጨመርን መጥተናል፡፡ የግብርና ግብዓቶችም ለገበሬዎች ማዳረስ ችለናል፡፡ ምርት በመጨመር ብዙዎችን መመገብ ችለናል፡፡ የሕዝብ ብዛት ግን ፈተና ሆኖብናል፡፡ እሱንም እንቀርፋለን . . .›› የሚሉ መከራከሪያዎችን ቢያቀርቡልዎ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- እውነት ነው፣ ትክክል ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ብዙ ሠርቷል፡፡ በመጽሐፌ የጠቅስኳቸው ችግሮች እነሱ የሠሩትን ለማሳነስ ተፈልገው የቀረቡ አይደሉም፡፡ መጽሐፉ የተሠሩትን ሥራዎች በሚገባ ያሳያል፡፡ ከሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ጥቂቱን ልጥቀስ፡፡ በተቋም ምሥረታ ደረጃ ካየን የግብርና ሚኒስቴር ከተቋቋመት ከ110 ዓመታት ጀምሮ፣ የግብርና ሳይንስም ከተጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ ወዲህ አሜሪካኖቹ ‹‹ፖይንት ፎር›› ብለው በሚጠሩት ፕሮግራም ዕገዛ ከሠራውም ይልቅ፣ ይህ መንግሥት በገጠር መሠረተ ልማት መስክ ብዙ ሠርቷል፡፡ ተቋማትን መሥርቷል፡፡ ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩትን የ22 ተቋማት ብዛት ወደ 145 አሳድጓል፡፡ ይኼ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ይሁንና ረሃቡ አልቆመም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ራሱን ማታለል የለበትም፡፡ ታሪክ ስለሠሩት ሥራ ወደፊት ይዘክራቸዋል፡፡ ሆኖም አብዛኛው የተሠራው ሥራ ግን በቂ አይደለም፡፡ ካለው ፍላጎት አኳያም ሥራው ብዙ ይቀረዋል፡፡ የአክሱም ሥልጣኔ ለመውደቁ አንዱ ምክንያት የግብርናው መዳከም፣ የሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ በተጨማሪም በቀይ ባህር በኩል ይደረግ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በኦቶማን ቱርኮች መያዙ ያመጣው የንግድ መቀዛቀዝ ጭምር ነው፡፡ የመንግሥት መውደቅ በኢትዮጵያ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ የአሁኑ የወጣቶች አመፅ ግን ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ሳያቋርጥ ከውጭ እየገባ ያለው የጥራጥሬ ግዥ ከፍተኛ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባው ጥራጥሬ ዘጠኝ በመቶ የአገሪቱን ብሔራዊ ምርት የሚሸፍን ነው፡፡ በዕርዳታ የሚገባውም የአገሪቱን ስድስት በመቶ ብሔራዊ የጥራጥሬ ምርት የሚሸፍን ነው፡፡ በመሆኑም ከውጭ በሚገባ የ15 በመቶ የምግብ አቅርቦት ተኩራርተህ ልትቀመጥ አትችልም፡፡ በፖለቲካው ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን መሰሎቼ ሊረዱት የሚገባቸው ነገር ቢኖር ጊዜው እያመለጠን መሆኑን ነው፡፡ ድህነትና ረሃብ ጊዜ አይሰጡም፡፡ የተራበ ነገን አይጠብቅም፡፡ ይህ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እውነታ ነው መጽሐፉን እንድጽፍ የገፋፋኝ፡፡ በነገራችን ላይ አንድ አገር እንድትወድቅ ምክንያት የሚሆኑ አራት ጉዳዮችን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ አንደኛው ፖለቲከኞች ሥራቸውን እንደሠሩ ማሰብ ሲጀምሩ ነው፡፡ ‹በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን› ማለት ከጀመሩ፣ በሚገባ ማሰብ የሚኖርባቸው ያን ጊዜ ነው፡፡ ዕውቀት የሚጀምረው አለማወቅን ከማወቅ ነው፡፡ ነባራዊውን ችግር ካለመረዳትና እየመጣ ያለው ችግር ምን እንደሆነ ካለመገንዘብ የተነሳ መንግሥታት ለውድቀት ይዳረጋሉ፡፡ ‹ትልቅ ሥራ ሠርተናል›፣ ‹አንድ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ የምግብ እጥረት ቀውሱን ተከላክለናል›፣ ወዘተ. እያሉ በትንሹ ሥራ መኩራራት ገዳይ ነው፡፡ እንዲህ እየሆነ ባለበት ወቅት ከተኛንበት ስንነቃ ጊዜው እንዳይረፍድብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የመጽሐፍዎን ማዕከላዊ ጭብጥና ትንታኔን በሚቃኘው ምዕራፍ ስምንት ውስጥ ስለቀረቡት ጉዳዮች እንነጋገር፡፡ በዚህ ትንታኔ ውስጥ የኢትዮጵያን አነስተኛ ገበሬዎች በቀውስ ውስጥ የሚገኙ፣ ለመኖር የሚጣጣሩ፣ ማገገም የሚችሉና ሀብታም በሚባሉ ደረጃዎች ከፋፍለዋቸዋል፡፡ ገበሬዎቹንና የኑሮ ደረጃቸውን እርስዎ ባስቀመጡት ልክ ከፋፍሎ ለማስቀመጥ ስለፈለጉባቸውና እነዚህ ምደባዎች ከእውነታው አኳያ ምን ማለት እንደሆኑ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ጌታቸው፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲኖር መጀመርያ ግብርና ምን ማድረግ እንደሚችልና ምን ማድረግ እንዳለበት መረዳት ይኖርብናል፡፡ ቀደም ብዬ አምስት ቁልፍ የግብርናው ዘርፍ መለኪያዎችን ገልጫለሁ፡፡ ከ110 ዓመታት የግብርና ተቋማት ሒደት በኋላ የታዩትን ለውጦች የሚለኩት እነዚህ መመዘኛዎች ናቸው፡፡ ግብርናችን መሠረታዊ የምግብ ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻለም፡፡ ግብርናችን ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎችም ማኅበራዊ ፍላጎቶቻችን የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ለመሸፈን አላስቻለም፡፡ ለግብርና ግብዓት የሆኑትን ለማቅረብም ሆነ የግብርና መሣሪያዎችን ለመቀየር አላስቻለም፡፡ ከእነዚህ መለኪያዎች በመነሳት አራት የግብርናና አራት የፍጆታ ማሳያዎችን አቅርቤያለሁ፡፡ መሠረታዊ የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት ያልቻሉትን ቤተሰቦች ቀውስ ውስጥ የሚገኙ በማለት የገለጽኳቸው ሲሆኑ፣ ጥሩ ምርት በሚገኝ ጊዜ በትንሹም ቢሆን ፍጆታቸውን ማሟላት የቻሉትን ደግሞ ዛሬን ለመኖር ይንገታገታሉ ያልኳቸው ናቸው፡፡ ጥሩ ማምረት የሚችሉ ወይም ‹ሪኒዋል› የተባሉት ደግሞ በቂ የሚያመርቱና ለፍጆታቸው ማሟላት የሚችሉ፣ አልፎ አልፎም ለዘርና ለማዳበሪያ የሚውል ገንዘብ የሚያገኙት ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ የአገሪቱን 1.2 በመቶ ገበሬ የሚወክሉ ሀብታም ወይም ‹ኢንተርፕራይዝ› ገበሬዎች የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ሰብሎች የሚያመርቱና የሜካናይዝድ እርሻን መተግበር የሚችሉ፣ እንዲሁም ግብዓቶችን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ጥቂት ሀብታም ገበሬዎች ነው ፖለቲከኞች ስለኢትዮጵያ ግብርና ስኬታማነት አብዝተው የሚናገሩት፡፡ ይህንንም ማጣጣሌ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቀውስ ውስጥ ያሉትና ለመኖር የሚጣጣሩት ቤተሰቦች ጠቅላላ ድምር ሲታይ 86 በመቶው የገጠር ቤተሰብ በችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ቤቱ እየተቃጠለ እንደሆነ የሚያመላክት አኃዝ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት አብዛኛው ሕዝብ በአስከፊ ድህነትና ረሃብ ውስጥ በሚገኝበት ሁኔታ እንዴት ነው በጥቂቶች መኩራራት የሚቻለው? ለአንባቢያን ግልጽ እንዲሆን ተጨማሪ ነጥብ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ይኼውም የገጠር አባወራዎች ኢንተርፕራይዞች እንደሆኑ ጭምር ነው፡፡ አምራቾችም ሸማቾችም ናቸው፡፡ እንደ አምራች አራሹን ገበሬ ይወክላሉ፡፡ እንደ ሸማችም ለፍጆታ የሚሆናቸውን ይሸምታሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከትንታኔዎ መረዳት እንደሚቻለው ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለምግብ ዕርዳታ መዳረጉን ነው፡፡ ትክክል ነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- አዎን ትክክል ነው፡፡ እንደምናውቀው ‹‹ደህና በሚባለው አማካይ ዓመት›› ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ ለአስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደሚዳረግ ነው፡፡ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብም በመደበኛነት በማኅበራዊ ሴፍቲኔት አማካይነት በቋሚነት የምግብ ዕርዳታ ያገኛል፡፡ ልብ በል እነዚህ ሰዎች ገበሬዎች ናቸው፡፡ ዓመት በመጣ ቁጥር ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን የሚመግብ አቅም ከየት እንደሚመጣ ልብ በል፡፡ እነዚህ ሲደማመሩ በአማካይ 20 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ በሚፈልገው ምድብ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ሰው በዕርዳታ መመገብ አትችልም፡፡ የዓለም ለጋሽ ማኅበተሰቡም ሁሌም ዕርዳታ ማቅረብ እየሰለቸው መጥቷል፡፡ የዕርዳታ ወጪው አገሪቱን የልመና ገጽታ በመፍጠር ብቻ የሚቆም አልሆነም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ በማጣት ለአዕምሮ ዕድገትና ለመቀንጨር የሚዳረጉ ሕፃናት በርካታ ናቸው፡፡ በተወለዱ በመጀመርያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ ተመጣጣኝ የምግብ አቅርቦት የማያገኙ ሕፃናት ለመቀንጨር ብሎም በወደፊት የአዕምሮ ዕድገታቸው፣ በትምህርት ቤትም ደካማ ውጤት እንዲያሳዩ፣ በወደፊት ኑሯቸው ላይም ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ለሚሰቃዩ ሕፃናት የጤና ክብካቤ ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢትዮጵያ ወጪ እንደምታደርግ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የምግብ እጥረት ወጪ ከዚህም ባሻገር የሚገለጽ ነው፡፡ የግብርናው ደካማ መሆን ኢትዮጵያን በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እህል እንድትገዛ እያስገደዳት ነው፡፡ ይኼ ከፍተኛ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የምግብ ዘይትና ሌላውም የምግብ እህል ሲታከልበት ጫናው ምን ያህል ከባድ እየሆነ እንደመጣ ያሳያል፡፡ የረሃብ ወጪ፣ እንዲሁም የማይሠራ ግብርና እየተከተሉ የመኖር ወጪው በአፋጣኝ ካልተገታ አገሪቱን ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚከታት ጥርጥር የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ለመንግሥት ባቀረቧቸው የፖሊሲ መፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ አንድ ለየት ያለ ነገር አካተዋል፡፡ ይውም ማኅበራዊ ዋስትና ላይ ያተኮረ ባንክ ይቋቋም፣ ገበሬዎችም ለባንኩ ምሥረታ አስተዋጽኦ ያደርጉ ያሉት ነው፡፡ ይህንን ማድረጉ ምን ያህል የሚሳካ ነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- እዚህ ላይ ከሌሎች ካደጉ አገሮች ራዕይ ያለው፣ በፈጠራና በአስተሳሰብ የተሞላ ሥራ ለመሥራት የሚችልበትን መንገድ መቀየስ የሚቻለው እየተማርን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ለኢትዮጵያ የሚስማማ ሥርዓት መፍጠር እንችላለን፡፡ ለማኅበራዊ ዋስትና ጥበቃ የሚረዳውን አጀንዳ በመጽሐፉ ካሰፈርኩት የመፍትሔ ሐሳብ በመነሳት ሰፋ አድርጌ ላብራራ፡፡ ኢትዮጵያ አራት ተመጋጋቢ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባታል፡፡ አንደኛው የግብርና ሜካናይዜሽንን መተግበር ነው፡፡ የግብርና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ነው፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ ሌሎች ላይ ለመድረስ በፍጥነት መሮጥ አለብን፡፡ ለእኛ ትናንትና ነገ የለንም፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያ ለቃሏ ታማኝ መሆን አለባት፡፡ የግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ የገጠሩን የግብርና ልማት ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር ታስቦበት የተወጠነ ነበር፡፡ ይህ ስትራቴጂ ጭርሱኑ ሳይተገበር መቆየቱ፣ ገጠሩም ኢንዱስትሪውም ሳይገናኙ መቆየታቸው ግን መለወጥ አለበት፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ስለግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት መናገር አቁመዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ስትራቴጂ ከወደቀበት በማንሳት መተግበር አለባቸው፡፡ ስትራቴጂው ትልቅ ሐሳቦችን የያዘና እኔም የገጠር ኢንዱስትሪ ብዬ የምጠራውን ዓይነት አካሄድ የሚከተል ነው፡፡ እስቲ እንመልከት፡፡ ለአንድ እንቁላል ስንት እንከፍላለን? አንድ ሊትር ወተት በስንት ብር ነው የምንገዛው? አንድ ኪሎ ሥጋስ? ዶሮስ በስንት ነው የሚሸጠው? የገጠሩን ግብርና ትራንስፎርም ማድረግ ማለት እንዲህ ያሉትን ምርቶች በገፍ ማምረት ወደሚያስችል የኢኮኖሚ መዋቅርነት መለወጥ መቻል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ከላይ እንደተነጋገርነው የከተማ መስፋፋትና ከተሜነት ላይ መሥራት አለበት፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ላለፉት በርካታ ዓመታት የከተሜነትን ጉዳይ ሲያጣጥለው ቆይቷል፡፡ ሕዝቡን በገጠሩ አካባቢ ማቆየት ይፈልጋል፡፡ ሕዝቡ ግን ወደ ከተማ እየጎረፈ ነው፡፡ አራተኛው ቁልፍ ነጥብ የአገልግሎት አቅርቦት ነው፡፡ የገጠሩን ሕዝብ አምራች፣ ሸማች፣ ምርት አቀነባባሪና ሌላውንም ሥራ የሚሠራ ማኅበረሰብ እንዲሆን በማድረግ ገበያ መር ኢኮኖሚ መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህ ሲደረግ የአገልግሎት ኢኮኖሚው ይስፋፋል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆን የመሬት ይዞታ መሻሻል አለበት፡፡ በግማሽና ከዚያ ባነሰ መሬት ላይ ሜካናይዜሽን ማካሄድ ስለማይቻል፣ ያለውን መሬት ማጣመርና አንዱን ከሌላው በማዋሀድ ሰፊ የእርሻ መሬት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የመሬትና የንብረት ባለቤትነትን ጨምሮ ሌሎችም መብቶች በዚህ ሒደት ውስጥ መካተትና መከበር ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አካሄድ መሬት እንዲሰባሰብ በሚደረግበት የትራንስፎርሜሽን ሒደት ሊጎዱ የሚችሉና ሊጠቀሙ የሚችሉ አካላት ይኖራሉ፡፡ የሚጎዱ ሰዎች እንደሚኖሩ ማሳያው አሜሪካ፣ ብራዚል፣ የ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ እንግሊዝና ሌላውም የአውሮፓ ክፍል ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ግብርናው ሲዘምን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የሚያካክስ የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት የሚሰጥ ብሔራዊ አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ካለም መልሶ ማየቱ ይጠቅማል፡፡

ኢትዮጵያ በአብዛኛው የምትከተለው የማኅበራዊ ድጋፍ ላይ ያተኮረ የሴፍቲኔት አሠራር ነው፡፡ ለገጠሩ ነዋሪ  ይሰጥ ከነበረው ድጋፍ በተጨማሪ ለከተማውም ይህ ፕሮግራም መተግበር ጀምሯል፡፡ ይህ ዕርዳታ ለማግኘት ታስቦ የተነደፈ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ግን መቀጠል አይቻልም፡፡ የሚያስፈልገው የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ መመሥረት ነው፡፡ ይህ ባንክ አቅሙ ያላቸው ኢንተርፕራይዝ ገበሬዎች የሚቆጥቡበትን ባንክ ማቋቋም ተገቢ ነው፡፡ ገበሬዎቹ የምርት ችግር እንደሚገጥማቸው ሥጋት ሲያድርባቸው ይህንን ለመቋቋም የሚችሉበትን ቁጠባ የሚያስተናግድ ባንክ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ለማይችሉትና በቀውስ ውስጥ ለመኖር በመጭርጨር ላይ ላሉት ገበሬዎች መንግሥት መዋጮ በማድረግ በባንኩ ተጠቃሚ እንደሆኑ ማገዝ አለበት፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ለመነሻ የሚሆን ድጋፍ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ለማለት የምፈልፈው በምግብ አቅርቦትና በዕርዳታ ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ ድጋፍ ዘላቂነት የለውም ነው፡፡ መለወጥ አለበት፡፡ ዕድር፣ ዕቁብና መሰል ተቋማት አሉን፡፡ እነዚህን መጠቀም አለብን፡፡ ሌላው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ድርጅት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ ይህም የመሬቱን፣ የማኅበራዊ ዋስትናውን ጉዳይና ሌሎችም በለውጥ ሒደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ግጭቶችን የሚያረግብ መሆን አለበት፡፡ አሁን ያለው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤንጀሲ አወቃቀርና አሠራር በቂ አይደለም፡፡ እንዲሠራ የተፈለገው ሌላ ነገር ሆኖ ሳለ እየሠራ ያለው ግን የማይገናኘውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊና ራዕይ ያለው የለውጥ ስትራቴጂ ያስፈልጋታል፡፡ ይህንንም የሚመራ የመዋቅር ቅርፅ ልትፈጥር ይገባታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....