ከሰሞኑ የወጣው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ፣ የሚያዝያ ወር የዋጋ ግሽበት 13.7 በመቶ ማስመዝገቡን ያሳያል፡፡ ይህ ስታትስቲካዊ ስሌትንና ንጽጽርን መሠረት ያደረገ አሐዝ ነው፡፡ ገበያው ግን ከተጠቀሰውም በላይ የዋጋ ለውጥ ሊያሳይ ይችላል፤ እያሳየም ነው፡፡ የኤጀንሲው መረጃ እንዳለ ሆኖ፣ በተጨባጭ የምናየው እውነታ አሳሳቢ የዋጋ ለውጥ እየታየ ስለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ዕድገት ጤናማ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ፈጣን የዋጋ ለውጦች በበርካታ ምርቶች ላይ እየታየ ነው፡፡ የድግግሞሹ መጠንና ፍጥነትን እያየለ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ለዕለታዊ ፍጆታው የሚጠቀምባቸው ምርቶች ብቻም ሳይሆኑ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን የመሳሰሉ ምርቶችም የሚያሳዩት የዋጋ ለውጥ የዋጋ ዕድገት በየአቅጣጫው እየሰፋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናትና ውጤቱ የችግሩን አሳሳቢነት ሊያሳየን ይችላል፡፡
በቅርቡ ይፋ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው፣ ብረትን ጨምሮ ሌሎች ለግንባታ ሥራዎች የሚውሉ ግብዓቶች የውጭ የምንዛሪ ለውጡ ከተደረገበት ከጥቅምት ወር ወዲህ በአማካይ የ51 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ ይህ ጥናት እስከ ጥር ወር 2010 ዓ.ም. ያለውን መረጃ ተመርኩዞ የተሠራ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ የተደረገው የዳሰሳ ጥናትም ቢሆን፣ በዘርፉ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከዚህም በላይ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ በርካታ ሰዎችን በመቅጠር የሚታወቀውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የዋጋ ጭምሪ፣ በዋጋ ንረቱ ሳቢያ እንቅስቃሴውን እንዲያቀዛቅዝ ከሚያስገድደው ደረጃ ላይ ሊደርሰው እንደሚችልም አስግቷል፡፡
እንደ ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ሁሉ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ዋጋም እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ተገቢ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች ቢኖሩም፣ በርካታ ምርቶች ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሰበብ በማድረግ ዋጋ ሲቆለልባቸው ይታያል፡፡
ምክንያቱ ተገቢነት ይኖረውም አይኑረው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ተደራራቢ የዋጋ ጭማሪ ግን መጨረሻው የአብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ህልውና እንደሚፈታተነው የታመነ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪው በቀናት ልዩነት ውስጥ መታየት መጀመሩ ብቻም ሳይሆን፣ ይብሱን እየሰፋ መምጣቱ ለከፋ የኑሮ ውድነት የሚዳርግ አካሔድ ውስጥ እየገባ ነው ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሳል፡፡
እየታዩ ያሉት የዋጋ ጭማሪዎች የሕዝብን ብሶት ሊቀሰቅሱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የዋጋ ግሽበቱ ጉዳይ ችላ መባል የለበትም እንላለን፡፡ ገበያው የተወጣጠረበት ምክንያት ምን እንደሆነና ዋጋዎች ያለማቋረጥ የሚንሩበትን መንስዔ አብጠርጥሮ በመመልከት ለማስተካከል የሚያስችል ሥራ ባለመሠራቱ ሸማቾችን ምሬት ላይ እየጣለ ነው፡፡
ምንም ዓይነት የገቢ ወይም የደመወዝ ጭማሪ ያልተደረገለት የኅብረተሰብ ክፍል እየጋለበ ካለው የዋጋ ጭማሪ ጋር መራመድ ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ግማሽ ሊትር ወተት በሁለትና በሦስት ሳምንት ልዩነት ውስጥ ወደ 15 ብር ሲያሻቅብ ለምን ይህንን ያህል ዋጋው ተወደደ ተብሎ ገበያውን ለማጣራት አልተሞከረም፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት አምስት ብር ሲሸጥ የቆየው ሻማ፣ ከሰሞኑ ሰባት ብር ገብቷል፡፡ በቀናት ልዩነት የተደረገው ጭማሪ በምን ሥሌት እንደተደረገ የጠየቀ የለም፡፡ ጎማና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለመግዛት ገበያ የሚወጡም የሚሰሙት ዋጋ ጭንቅላት የሚያዞር ሆኖባቸዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪው እስከ ታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እየነካካ ብዙኃኑን ‹‹ኧረ ወደየት እየሄድነው?›› በማሰኘት ላይ ነው፡፡
ፓስታ፣ ዱቄት፣ ሳሙናና ሌሎችም ምርቶች የዋጋ ንረት ታይቶባቸዋል፡፡ እንደ ሮኬት የተተኮሱት የሕፃናት የንጽሕና መጠበቂያ ዳይፐሮችና የዱቄት ወተት ዓይነቶች በሦስት ወር ውስጥ ምን ያህል እንደጨመሩ ለተመለከተ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ግብይት አካሄድ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ቢሠጋ ተገቢ ነው፡፡
ዳይፐር ከ100 ብር በላይ ጨምሯል፡፡ በአንድ ዕቃ ላይ 200 እና 300 ብር ጭማሪ የታከለባቸው ምርቶች ሸማቹን ፀጉር እያስነጩ ነው፡፡ እንዲህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው? ለ15 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ 50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ምን የሚሉት ነው?
መንግሥት አገር ለማረጋጋትና አንድነትን ለማጠናከር እያደረገ ያለው ጥረት ለኢኮኖሚውና ለንግድ እንቅስቃሴው የሚሰጠውን ትኩረት በመቀነሱ የኢኮኖሚው ቁስለት ከውስጥ ወደ ውጭ እያበጠ የመጣ ይመስላል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ይህንን ጉዳይ በጥልቀት በመመርመር መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል የሚለውን ጥሪ ደጋግመን ለማቅረብ እንገደዳለን፡፡
በተለይ መሠረታዊ ምርቶችና ሸቀጦች፣ ያውም በመንግሥት ይደጎማሉ የሚባሉትና እንደ ስንዴ ያሉት የምግብ ሸቀጦች በተፈለገው መጠን አለመገኘታቸው ሳይበቃ ለዋጋ ጭማሪ መባባስ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በድጎማ ይመጣል የተባለው የምግብ ዘይት ዋጋም ባልተጠበቀ ሁኔታ መጨመሩን መንግሥት አልሰማ ይሆን እንዴ የሚያሰኝ መራር ቀልድ እያስከተለ በመሆኑ፣ እንደ ፖለቲካው ሁሉ ለኢኮኖሚውም ዓይንና ጆሮ ይሰጠው ዘንድ ይጠየቃል፡፡