Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ የግል ኩባንያ ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሌሎች ስምንት ኩባንያዎችም ለአገልግሎቱ ተመዝግበዋል  

ከእንግሊዝና ከአሜሪካ በመጡ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ጂቱጂ ክላሪቲ አይቲ ሶሉሽንስ የተሰኘ የአክሲዮን ኩባንያ፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ይቀርብ የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት በኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት አማካይነት ለደንበኞች የሚያቀርብ ኩባንያ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኩባንያው መሥራቾች ዓርብ፣ ግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ ኩባንያው የኢትዮ ቴሌኮምን ዋናውን የኔትወርክ መስመርና የዳታ ማዕከል በመጠቀም የራሱን የፋይበር ኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሞገስ እንዳስታወቁት፣ የኢንተርኔት ሽያጭ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ከሚቀርብበት ዋጋ ለጊዜው በሚቆይ የቅናሽ ዋጋ መሠረት ለተጠቃሚዎች ይቀርባል፡፡ በመሆኑም በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ለአንድ ሜጋ ባይት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚከፈለው 1,960 ብር ገንዘብ፣ ለግለሰብ ተጠቃሚዎች እስከ 50 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበት ይቀርባል፡፡ ለድርጅት ተጠቃሚዎችም ከአምስት እስከ 20 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ አቶ ብሩክ አስታውቀዋል፡፡

የኩባንያው ቺፍ የቴክኖሎጂ ኦፊሰር አቶ ቴዎድሮስ መሀሪ በበኩላቸው የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለማቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ የአጋርነት ስምምነት መሠረት በአዲስ አበባ በተመረጡ ሰባት አካባቢዎች ላይ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችና ለኢንተርኔት አገልግሎት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ተከላ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው የሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት በፋይበር ኦፕቲክ መስመር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ፍጥነትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያስችለው የኩባንያው መሥራቾች ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ደንበኞችን የሚያማርሩት የኔትወርክ መቆራረጥና የጥራት ችግሮች በኩባንያው በኩል በሚቀርበው አገልግሎት እንደማያጋጥሙ አስታውቀዋል፡፡

‹‹Value Added Service›› በሚባለው የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፈቃድ ያገኘው ይህ ኩባንያ፣ ከቨርቹዋል የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢነት ባሻገር፣ በጥሪ ማዕከል አገልግሎት፣ በመዝናኛና በመረጃ አገልግሎት፣ የእንቅስቃሴ ክትትል ማድረጊያ አገልግሎት፣ የክፍያና የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትን ጨምሮ የአጭር መልዕክት አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡  

የቨርቹዋል ኢንተርኔት አገልግሎቱን ከቴሌ የኢንተርኔት መስመሮች አማካይነት ለመጨረሻው ተጠቃሚ የሚውሉ አገልግሎቶች የሚቀርቡበት ሲሆን፣ ጂቱጂ ክላሪቲ በአሁኑ ወቅት ቦሌ፣ ሃያ ሁለትና ሲኤምሲን ጨምሮ ሰባት ቦታዎች ላይ ከተከላቸው የቴሌኮም መሣርዎችና የኔትወርክ ሳጥኖች ባሻገር ከውጭ እያስገባቸው የሚገኙ መሣሪያዎችም አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ እንደሚያስችሉት ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምን በመወከል ማብራሪያ የሰጡት ኢንዳይሬክት ፓርትነር ማናጀር በሚል ኃላፊነት የተጠቀሱት አቶ ሙሴ ደስታ በበኩላቸው፣ ይህ አገልግሎት በግል ኩባንያዎች በኩል እንዲሰጥ የማድረጉ ሒደት ረዥም ጊዜ መውሰዱን ተናግረው፣ ቨርቹዋል የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡት ኩባንያዎች ኢትዮ ቴሌኮም ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የገዛውን ዋና የኢንተርኔት መስመር በመጠቀም እንደሚሠሩ አብራርተዋል፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡት ኩባንያዎች በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የተዘረጋውን ኔትወርክ ይጠቀማሉ እንጂ በራሳቸው ከውጭ ኔትወርክ መግዛትና አገልግሎቱን መስጠት እንደማይችሉ፣ ይህም ለኢትዮ ቴሌኮም ብቻ የተተወ የሥራ መስክ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ 

  በአሁኑ ወቅት በጠቅላላው 16.8 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቢኖርም፣ በኬብል መስመር ከተዘረጋው የኢንተርኔት አገልግሎት የሚጠቀመው ግን ዝቅተኛ በመሆኑ የኩባንያዎቹ መምጣት ይህንን ለማሻሻል እንደሚረዳ አቶ ሙሴ አስታውቀዋል፡፡ ከጂቱጂ ኩባንያ ባሻገር ሌሎች ስምንት ኩባንያዎችም በተመሳሳይ የአገልግሎት መስክ ለመሰማራት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት መፈጸማቸውን አቶ ሙሴ ጠቅሰዋል፡፡

ጂቱጂ ከሁለት ዓመት በፊት በአሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ የአክሲዮን ማኅበር ሲሆን፣ በሶፍትዌር ማበልጸግ፣ በማኑፋክቸሪንግ መስክ፣ በአገልግሎትና በግንባታ ሥራዎችና በሌሎችም መስኮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እህት ኩባንያዎች እንዳሉትም ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች