Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች ዳይሬክተሮች አዲስ ማኅበር መሠረቱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮችን በቦርድ ዳይሬክተርነት የሚመሩ ኃላፊዎች ‹‹የኢትዮጵያ ባንኮች የቦርድ ዳይሬክተሮች የምክክር መድረክ›› በመባል የሚጠራ ማኅበር መሠረቱ፡፡ ማኅበሩን ለማስመዝገብ ሙግት ውስጥ ገብተዋል፡፡

የባንክ ፕሬዚዳንቶች የሚመካከሩበትና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በመባል ከሚታወቀው ውጪ፣ የባንክ ዳይሬክተሮች መድረክ የተባለውን ማኅበር ለማቋቋም ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተው፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ከየባንኮቹ የተውጣጡ 40 የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢዎችና የቦርድ አባላት በተካተቱበት አኳኋን ማኅበሩን በይፋ መመሥረታቸው ታውቋል፡፡ ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝም በዕለቱ የተመረጡ ሰባት የሥራ አመራሮች ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ማመልከቻ አስገብተዋል፡፡

ከ120 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን የሚወክሉት የባንኮች ቦርድ አባላት፣ የራሳቸው አዲስ ማኅበር እንደሚያስፈልጋቸው በማመን ያቋቋሙት ስለመሆኑ ከማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

መድረኩ ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል በንግድ ባንኮች ውስጥ መልካም የአስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ማድረግ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ ማስቻል የሚሉት በዋናነት ተቀምጠዋል፡፡ ክህሎትና ዕውቀት እንዲያዳብሩ የሚያግዙ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት፣ የቦርዶች ሥልጣን፣ ኃላፊነት፣ መብትና ግዴታ ላይ የቦርድ አባላት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግም ከዓላማዎቹ ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ አባላቱ ያሉባቸውን ችግሮች እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉ የጋራ መድረኮችን በመፍጠር ዘላቂ መፍትሔዎችን ማፈላለግ፣ አባላቱ በተሟላ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ ከባንክ ሥራ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለአባላቱ ማሠራጨት የሚሉትም ተካተዋል፡፡

 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀትም ስለባንኮች የጋራ ችግሮች እየተወያዩ መፍትሔ መለፈግና ለዘርፉ ዕድገት አስተዋፅኦ ማድረግ የማኅበሩ ዓላማ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ዳይሬክተሮች በግልና በጋራ የሚወስዱትን ኃላፊነትና የሚጣልባቸው ግዴታ ሙሉ በሙሉ አለመውጣታቸው ለሚያስከትልባቸው የሕግ ተጠያቂነትም የመድን ሽፋን እንዲያገኙ የማድረግም ዓላማም ይዟል፡፡ ዳይሬክተሮች ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች የሚመጥን የአገልግሎት ክፍያ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ የቦርድ አባላትን ሕጋዊ መብት ማስጠበቅም የአዲሱ ማኅበር ተልዕኮዎች ይሆናሉ፡፡ በዚህ ማኅበር ውስጥ በአባልነት መመዝገብ የሚችሉት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የመንግሥትና የግል ባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሆኑና ከዚህ ቀደም በቦርድ አባልነት ያገለገሉ ሰዎች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በስድስት የቦርድ ዳይሬክተሮችና አባላት ተጠንስሶ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በይፋ ለተቋቋመው አዲሱ ማኅበር፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በመሆን  የሰባት ባንኮች የቦርድ ሰብሳቢዎች መመረጣቸውም ታውቋል፡፡ ማኅበሩን በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት የዳሸን፣ የአዋሽ፣ የኅብረት፣ የእናት፣ የአቢሲኒያ፣ የዘመን፣ የንብ፣ እንዲሁም የእናት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡ የመድረኩ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከኅብረት ባንክ ሲመረጡ፣ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን አቶ ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ  ከንብ ባንክ ተመርጠዋል፡፡

የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢየሱስ ወርቅ እንደሚገልጹት፣ የቦርድ አመራሮቹ በባለአክሲዮኖች የተመረጡ እንደራሴዎች በመሆናቸው፣ ኃላፊነታቸውም በዚያው ልክ እንደሚበዛና ይህንን ኃላፊነትም በአግባቡ እንዲወጡ ለማገዝ የማኅበሩ መመሥረት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የባንኮች የዳይሬክተር ቦርድ አባላት በንግድ ሕጉ፣ በባንክ ሥራ አዋጅና ብሔራዊ ባንክ ባወጣቸው የኩባንያ መልካም አስተዳደር መመርያ መሠረት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ሳቢያ፣ የሚመጣባቸውን ተጠያቂነት ለማስተናገድ ዋስትና እንዲያገኙ ማኅበሩ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡ በባንክ ሥራ ውስጥ ካላቸው ሚና፣ ሥልጣንና ኃላፊነት አንፃር ለዘርፉ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያግዙ የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ የምክክር መድረክ መኖሩ አስፈላጊቱ ታምኖበት ማኅበሩ እንደተመሠረተ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ገልጸዋል፡፡

የየባንኮቹ ዳይሬክተሮች በተለይም የባንክ ማቋቋሚያ አዋጁን ተከትለው የወጡ በርካታ መመርያዎችን አገናዝበው፣ ከእነዚህ መመርያዎች ውስጥ በአንዱ የባንክ ዳይሬክተሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ግዴታቸውን ሳይወጡ የቀሩ እንደሆነ፣ የ100 ሺሕ ብር ቅጣትና 15 ዓመታት እስራት እንደሚጠብቃቸው የሚደነገግ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለውን አስገዳጅ ሕግ አክብሮ ለመሥራት ማኅበሩ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሚደርስበት የአሠራር ክፍተት ሳቢያ ማንኛውንም የባንክ ዳይሬክተር፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊያም ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ከሥራ ከማባረር ጀምሮ እስከማገድ የሚደርስ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚችል ስለመደንገጉም አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውሰዋል፡፡

የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅን ለመተግበር ሲባል የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችና ተጠሪዎች በቅን ልቦና በፈጸሙት ጥፋት በሕግ እንደማይቀጡ የተቀመጠ ድንጋጌ ቢኖርም፣ የባንኮች የቦርድ ዳይሬክተሮች ግን ለበርካታ የአሠራር ክፍተቶችና ግድፈቶች የተጋለጡ በመሆናቸው፣ መብታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ እንዲህ ያለውን ማኅበር ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

ይህ ይባል እንጂ አዲሱ ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ለበጎ አድራጎትና ማኅበራት ምዝገባ ኤጀንሲ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ምዝገባውን ለማካሄድ ግን ማኅበሩ የሙያ ወይም የተራድኦ ተቋም መሆን አለበት የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ምዝገባውን ለማከናወን በቂ የሆነ ሕግ ድጋፍ ያለው በመሆኑና ይህንኑ ሕግ በመከተል የጀመሩትን የምሥረታ ሒደት እንደሚገፉበት የማኅበሩ አደራጆች አስታውቀዋል፡፡ ምዝገባውም በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ምዝገባ ቁጥር 621/2009 አንቀጽ 55 መሠረት ማኅበሩን ላልተወሰነ ዘመን እንዳቋቋሙት መሥራቾቹ በመተዳደሪያ ደንባቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች