Monday, December 4, 2023

መቋጫ አልባው የህዳሴ ግድብ ውይይት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብና የተፋሰሱ አገሮች በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት አስመልክቶ ድርድር ማድረግ የጀመሩት የህዳሴ ግድቡ መገንባት እንደ ጀመረ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን አቋቁመው ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በውይይቱ መጀመርያ ላይ የግብፅ ትኩረት የነበረው የህዳሴ ግድቡን ለማስቆም የሚያስችሏትን አማራጮችን በሙሉ በመጠቀም ግድቡን ማስቆም ሲሆን፣ የግድቡን ግንባታ ማስቆም የማትችልበት ሁኔታ ላይ ስትደርስ ግን ስትራቴጂዋን በመቀየር ታሪካዊ የሆነውና የዓባይን ውኃ አጠቃቀም የሚያትተውን የቅኝ ግዛት ስምምነት የነበረውን እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈረመውን ውል ለማስጠበቅ ስትሠራ ቆይታለች፡፡ ይኼንንም ስምምነት ለማስጠበቅ ሱዳንም ጥረት ስታደርግ የነበረ ቢሆንም፣ ለረዥም ጊዜ ግልጽ የሆነ አቋሟ ሳይታወቅ ቆይታ፣ በሒደት የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የመቀበል አዝማሚያ እያሳየች መጥታለች፡፡

ምንም እንኳን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ተከትሎ የመጣው የሦስቱ አገሮች ውይይት ቢሆንም፣ በናይል ተፋሰስ የሚገኙ አገሮች ያልተማከለ የውኃ አጠቃቀምና ጥሩ ያልሆነ የአገሮች ግንኙነት ምሳሌዎች መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው፣ ያለውን የውኃ ሀብት ለመጠቀም የሚያስችል የውኃ አጠቃቀም የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

በዚህ የተፋሰሱ አገሮች ሁኔታ ውስጥ የመጣው የህዳሴ ግድብ፣ ለግሌ ብቻ የሚለውን አስተሳሰብ የመቀየር አቅም ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ “Declaration of Principles on the Grand Ethiopian Renaissance Dam: Some Issues of Concern” በሚል በደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) ተዘጋጅቶ በሚዛን የሕግ መጽሔት ላይ የታተመው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡ ይኼንንም ሊያስቀጥል የሚችል ሆኖ የመጣው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (Cooperative Framework Agreement) በኋላ የመጣው የመርህ ስምምነት (Declaration of Principles) ቢሆንም፣ የመርህ ስምምነቱ የራሱ የሆኑ ክፍተቶች ያሉት በመሆኑ ተስፋ ሰጪነቱ እምብዛም የሚያዛልቅ እንዳልሆነ ጥናቱ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ የናይል ተፋሰስ አገሮች ወንዙን ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ቢጠቀሙበት፣ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል አቅም እንዳለውም ይነገርለታል፡፡

ይሁንና የህዳሴ ግድቡ ከ65 በመቶ በላይ የግንባታ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም፣ በግድቡ ላይ የሚደረገው ውይይት እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሲያመጣ አልታየም፡፡

ግብፅም ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥሮ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ አገሮች በማስተባበር እ.ኤ.አ. በ2010 የተፈረመውን ስምምነት ወደ ጎን በማለት፣ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር የተፈራረመችው የመርህ ስምምነት ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ አያመዝንም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ኡጋንዳ ኢንቴቤ በስድስት የናይል ተፋሰስ አገሮች ማለትም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳና በብሩንዲ የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት፣ የዓባይን ውኃ እኩል ተጠቃሚነት የሚያትትና ለሁሉም የሚበጅ ስምምነት እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈ የህዳሴ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ሊያስከትል የሚችላቸውን ጉዳቶች ደረጃ ለማጥናት በሦስቱ አገሮች መካከል ስምምነት ተደርጎ፣ ጥናቱን የሚያከናውን ድርጅት ተመርጦ የጥናቱ ቅድመ ጥናት ሪፖርቶችን አቅርቧል፡፡ ይሁንና አጥኚው የፈረንሣይ ኩባንያ ከተሰጠው ድንበር አልፎ በሠራው ጥናት ስህተቶቹን እንዲያርም ቢነገረውም፣ ግብፅ እንቅፋት እየፈጠረች እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹አማካሪ ድርጅቱ ሥራ የተባለውን ሥራ በተሰጠው የጥናት ዳራና ቢጋር ማከናወን ባለመቻሉና ባቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ረቂቅ ላይ ያሉ ስህተቶችን እንዲያርም ተሰጥቶታል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት እየሆነች ያለችው ግብፅ ናት፡፡ ድርጅቱ ማረም መቻል አለበት፡፡ ይህ የተለመደ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፤›› ሲሉ ቃል አቀባዩ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ኢትዮጵያን በሚመለከት ለውይይቱ እንቅፋት ሆናለች በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጣቸው ተጠቅሶ ለተጠየቁት ጥያቄ፣ የሳሚ ሽኩሪ አስተያየት የሦስቱ አገሮች መሪዎች እንደ አንድ እንዲሠሩ ለሚኒስትሮቻቸው ከሰጡት መመርያ ያፈነገጠ ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ይኼንን አስተያየት ደግሞ የሰጡት ሦስቱ አገሮች በሚኒስትሮች ደረጃ ቀጣይ ስብሰባቸውን ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ለመገናኘት ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው፡፡ ‹‹የሳሚ ሽኩሪ አስተያየት በሦስቱ አገሮች መካከል እየተካሄደ ካለው ውይይት መንፈስ ጋር የማይጣጣም፣ ከሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ጋርም ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሦስትዮ ውይይቱ በመግባባት መንፈስ እንዲቀጥል አዎንታዊ ሚናዋን መጫወቷን፤›› ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን፣ የህዳሴ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ግምገማ እንዲጠና ቢአርኤል የተባለ የፈረንሣይ አማካሪ መቅጠራቸው ይታወሳል፡፡

ይሁንና የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ቡድንና የውኃ ሚኒስትሮች የሚያደርጉት ውይይት ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ፣ የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ ሳይንሳዊ አካሄዱን አጢነው ለማይወስኑ ፖለቲከኞች እንዲተላለፍ ተደርጓል ሲሉ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ግብፅ በሳይንሳዊ መንገድ ጥያቄዎች እንዳይነሱ፣ አለበለዚያም ምላሽ እንዳያገኙ ስለምትፈልግ ብዙ ጊዜ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ለማድረግ ትጥራለች ብለዋል፡፡

በሱዳን ካርቱም ለ17 ሰዓታት የተካሄደው ውይይት ያለውጤት የተጠናቀቀው በዚህ ምክንያት እንደሆነ፣ ብዙ የሚያቆዩ ጉዳዮች ሊኖሩ የሚችሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

በዚህ አካሄድም የትም የማያደርስ ውይይት እየተካሄደ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የሕግ ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡

ለዚህም ነው ግብፅ እ.ኤ.አ. የ1959 የውኃ አጠቃቀም ስምምነቷ እንዳይነካባት በማሰብ የተለያዩ ውይይቶችን ስኬታማ እንዳይሆኑ ስታደርግ የነበረው ሲሉም ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ግብፅ የሦስትዮሽ ውይይቶች የማይሳኩበትና የምትፈልገውን የማታገኝበት ሲሆን ሁልጊዜ ከስብሰባው የመውጣት ስትራቴጂዋ ነው፤›› ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ስለዚህም በተደጋጋሚ በሚደረጉ ውይይቶች ጊዜ እየባከነ ነው እንጂ ውጤት የሚታይበት ለውጥ እየመጣ እንዳልሆነ የሚያስረዱ፣ ብሎም መድረሻ አልባ ስብሰባዎችና የስብሰባ ቀጠሮዎች እየተያዙ እንዳሉ ይነገራል፡፡

የስብሰባው መርዘምና የጥናቶቹ መዘግየት ለየትኛውም የተደራዳሪ አካላት ጥቅም ይሰጣል ባይባልም፣ ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ ሆና ለመውጣት የሚያስችሏት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የመጠቀም ችግር ሲኖርባት፣ ግብፅ ደግሞ በማናቸውም ሁኔታዎች ውይይቱ እንዲቋረጥና እንዳይካሄድ ለማድረግ እንደምትሠራ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ ሱዳንን ከጎኗ በማሠለፍ ከውይይቱ በአሸናፊነት ለመውጣት የምታሳየው መለሳለስ ለውይይቱ መጓተት የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚናገሩ አሉ፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ጋር የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ውይይት ያደረጉት፣ ሁለቱ አገሮች ተመሳሳይ አቋም ላይ ለመድረስ በማሰብ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡

ፕሬዚዳንት አል በሽርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በህዳሴ ግድቡ ላይ ባደረጉት ውይይት፣ የሱዳንን አቋም በመጠኑም ቢሆን ሊያሳይ የሚችል ሐሳብ ሲንፀባረቅ መሰማቱ ምናልባትም በውይይቱ ኢትዮጵያ ጥቅሟን አስጠብቃ ልትወጣ ትችላለች የሚል ግምት እንዲሰጥ አስችሏል፡፡

የሱዳኑ መሪ ምንም እንኳን ግድቡ የኢትዮጵያ ቢሆንም፣ በገንዘብም ቢሆን የሱዳን ተሳታፊነት እንዲኖር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለጣና ፎረም ስብሰባ ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የህዳሴ ግድቡን እንደሚደግፉና ለሁለቱም አገሮች የጋራ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተደጋጋሚ ሲካሄዱ በነበሩት ውይይቶች ላይ እንደተገለጸው፣ ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ላይ በሚካሄደው ውይይት ግብፅ በዋናነት የቅኝ ግዛት ውሉ ላይ እንዲተኮር መፈለጓ ‹ውኃ ቢወቅጡት› እየሆነ እንደሆነም ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

‹‹ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለቀጣይ ድርድሮች እንቅፋት የሚሆን አካሄድ ነው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያናገራቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

የሦስቱ አገሮች ተደራዳሪዎች የግድቡ ጉዳት ሲጠና ምን ዓይነት ጉዳት እንደሆነና በምን አካሄድ እንደሚለካም መነገር አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ውይይት የበላይ ሆና ለመውጣት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

የአዲስ አበባው የሚኒስትሮች ውይይት ከመካሄዱ በፊት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሚገናኙት የቴክኒክ ቡድን አባላት ስብሰባ ለሚኒስትሮቹ የሚቀርቡትን ጉዳዮች እንደሚያዘጋጅም ታውቋል፡፡

የድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን የሚዳኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1997 የተደረገው ስምምነት ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የውኃ አካላትን ከቅኝት ውጪ (Non-navigational) ለሆኑ ጥቅሞች የማዋል ሕግ ስምምነት ነው፡፡ ይህም ሕግ፣ የውኃን የመጠቀም ሉዓላዊ መብትን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ የተፋሰስ አገሮች በድንበራቸው ክልል ውስጥ በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት ሊጠቀሙ እንደሚገባ ያትታል፡፡

ሆኖም ሕጉ እነዚህን ልማቶች የሚያከናውኑ አገሮች በሌላ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ይላል፡፡

ኢትዮጵያም በዓባይ ወንዝ ላይ የምታከናውነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ይኼንኑ መርህ ተከትሎ እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪና አዲስ የሚሾሙት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዶር በፕሬዚዳንት አል በሽር ትዕዛዝ መነሳታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -