Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማዕድን ሚኒስቴር በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለጉዳይ በፍጥነት እንደማያስተናገድ አመነ
  • የማዕድን ስርቆት እንዳለ ተገለጸ
  • መሬት ይዘው የሚቀመጡ ባለሀብቶች ጉዳይ እየተጣራ ነው
  • የጌጣጌጥና የከበሩ ማዕድናት ንግድ ተዳክሟል

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያሉበትን ችግሮች ገምግሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱን የመሩት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔርና ዶ/ር ዋጋሪ ፉሪ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ሁሉንም የማዕድንና ፔትሮሊየም ኩባንያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምክክር መድረኩ እንዲካፈሉ የጋበዘ ቢሆንም፣ ውስን ቁጥር ያላቸው ኩባንያዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ ታዋቂ የሆኑ የማዕድን ኩባንያዎችና ቅሬታዎችን የሚያሰሙ የኩባንያ ተወካዮች በስብሰባው ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያሉበትን ችግሮች ገምግሞ፣ ‹‹የማዕድን ዘርፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔዎችና የንቅናቄ ማቀጣጠያ ዕቀድ›› የሚል ሰነድ ለውይይት አቅርቧል፡፡

ሰነዱን ለውይይት ያቀረቡት አቶ ቶሎሳ የገዘፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአገሪቱ እየታዩ እንደሆነ ገልጸው፣ ያሉትን ችግሮች ይዞ የልማት ዕቅዶችን ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ በልማት ውጤት ተጠቃሚ ካልሆነ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ቶሎሳ ሚኒስቴሩ አሠራሩን ፈትሾ የክህሎት ችግር፣ የአቅርቦት፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ማነቆዎችን ነቅሶ አውጥቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀየሱን አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሩ የመሥሪያ ቤታቸውን ጠንካራ ጎን በመተው በደካማ ጎኖች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሰነድ ከፍተኛው አመራር የተሟላ ቁመና ያለው የለውጥ ሠራዊት በመገንባት ሒደት የነበረው ቁርጠኝነት አናሳ መሆን፣ የሪፎርምና የልማታዊ መልካም አስተዳደር ሥራዎችን በመተግበር ቀጣይነትና ወጥነት ባለው መልኩ ክትትል አለመደረግ፣ ከሕዝብ ክንፍና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚካሄዱ መድረኮች መቆራረጥ ከተዘረዘሩ በርካታ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በፈጻሚው አካል በኩል ከታዩ ችግሮች መካከል ተልዕኮውን ለይቶና መሠረት አድርጎ ለተግባራዊነቱ የተሟላ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ችግር መታየት፣ ከአገልጋይነት ይልቅ የተገልጋይነት ስሜት መታየትና የአድርባይነት ስሜት መንፀባረቁ በስፋት ተዘርዝሯል፡፡

ባለጉዳዮች በተቀላጠፈ ሁኔታ አለመስተናገዳቸው፣ በተለይም በጂኦሎጂካል ላቦራቶሪና የቁፋሮ አገልግሎት አሰጣጥ በኩል ትልቅ ተግዳሮት መኖሩን ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ በሰጡት ማብራሪያ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያሉ ችግሮች በየደረጃው ካልተፈቱ መንግሥት በተያያዘው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጎዳና መቀጠል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ መንግሥት መልካም አስተዳደር ማስፈን የሞት ሽረት ጉዳይ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን አምኖ መቀበሉን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ በማዕድን ዘርፍ ውስጥ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ካልተፈቱ ከዘርፉ የሚጠበቀው የሥራ ዕድል፣ የውጭ ምንዛሪና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሊገኙ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ይህን ካሉ በኋላ የኩባንያ ተወካዮች ያለምንም መሸማቀቅ በድፍረት በሚኒስቴሩ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲጠቁሙ መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ዝምታን የመረጡ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ስለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሠራር ችግር ሳይሆን በመስኩ ስለሚታዩ ስንክሳሮች መናገር መርጠዋል፡፡ ለወትሮ ለመገናኛ ብዙኃን ስለሚኒስቴሩ ሮሮ የሚያሰሙት ኩባንያዎች በስብሰባው ላይ ሳይናገሩ ቀርተዋል፣ ወይም ከነአካቴው አልተገኙም፡፡

አንዳንድ ታዳሚዎች በበኩላቸው በዘርፉ ስላሉ ችግሮች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የጋያ አሶሲየሽን ተወካይ ድርጅታቸው ለትርፍ ያልተቋቋመ የኤታኖል ምርት ለምግብ ማብሰያነት እንዲውል የሚያስተዋውቅ መሆኑን ተናግረው፣ ከፍተኛ የኤታኖል አቅርቦት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ኤታኖል በስፋት ጥቅም ላይ ቢውል ነጭ ጋዝን ሙሉ ለሙሉ መተካት እንደሚችልና በኤሌክትሪክ ፍጆታ ላይ ያለውን ጫና እንደሚቀንስ አስረድተው፣ ያሉት የስኳር ፋብሪካዎች አስተማማኝ የሆነ ኤታኖል ማቅረብ ባለመቻላቸው ድርጅታቸው የማስተዋወቅ ሥራውን ለመሥራት መቸገሩን፣ ባለሀብቶቹም ወደዚህ ሥራ ሊሳቡ እንዳልቻሉ ጠቅሰው ሚኒስቴሩ ለባዮፊውል ልማት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ከአፍሪካ ፓወር ኢኒሼቲቭ የመጡት አቶ ዮናስ ኃይለ ማርያም ድርጅታቸው በትግራይ ክልል በባዮፊውል ልማት ላይ መሰማራቱንና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ጠቁመው፣ እሳቸውም ሚኒስቴሩ ለባዮፊውል ልማት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ከአፋር ጨው አምራቾች ማኅበር የመጡት ተወካይም በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል በቅንጅት የመሥራት ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴርና የክልል ቢሮዎች ተቀናጅቶና ተናቦ የመሥራት ችግር አለና ይህ እንዴት ሊፈታ ይችላል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በጌጣጌጥና የከበሩ ድንጋዮች ኤክስፖርት ንግድ የተሰማራው የሮሃ ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ታደሰ መረሳ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ከታክስ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በጌጣጌጥና በከበሩ ድንጋዮች ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከፍተኛ የኤክሳይስ ታክስ ክፍያ እንደሚጠየቁ፣ ሽያጭን እንደ ትርፍ የማየት ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሮያሊቲ ክፍያ የወርቅ አምራቹ እንጂ አዘዋዋሪው ሊጠየቅ አይገባም፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ የጌጣጌጥና የከበሩ ድንጋዮች ነጋዴዎች ተማረው ሱቆቻቸውን በመዝጋት ወደ ሌሎች የሥራ ዘርፎች እየተሰማሩ መሆኑን በምሬት ተናግረዋል፡፡ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የጥሬ ወርቅ መጠን መቀነሱን አስረድተዋል፡፡

የሪያን ኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገስጥ ጥላሁን በበኩላቸው፣ የማዕድን ዘረፋ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያቸው የወርቅ ምርመራ ሥራ አካሂዶ የወርቅ አለኝታ አለ ብሎ ለቁፋሮ የመረጣቸው ቦታዎች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ትላልቅ ጉድጓዶች ቆፍረው አፈሩን ዝቀው መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህንን አዳራሽ የሚያካክል እስከ 20 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶች ተቆፍረው አግኝተናል፡፡ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማነው እንዲህ ያደረገው ብለን ስንጠይቅ ከሌላ ቦታ የመጡ ዶዘርና ኤክስካቬተር ይዘው መጥተው ቆፍረው መውሰዳቸውን ነግረውናል፤›› ያሉት አቶ ገስጥ፣ ሚኒስቴሩ ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጂኦሎጂካል ላቦራቶሪ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ፣ በዚህ ምክንያት በአገር ውስጥ ሊሠራ የሚችል የናሙና ምርመራ በውጭ ምንዛሪ በውጭ አገር ለማሠራት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የቁፋሮ አገልግሎት ለኩባንያዎች መስጠት እንደተሳነውም ተናግረዋል፡፡

በማዕድን በበለፀጉ ቦታዎች ይዞታን አስፍቶ በመያዝ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ሳያደርጉ ይዞ የመቆየት ችግር እንዳለ ተነስቷል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእምነበረድ ክምችት ባለባቸው ቦታዎች ደላላ ግለሰቦችና ኩባንያዎች መሬቱን ያለምንም ሥራ ታቅፈው እንደተቀመጡ አቶ ገስጥ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚሠሩ ኩባንያዎች እንዳይገቡ ቦታዎቹ በደላላ ግለሰቦች ተይዘዋል፡፡ ለሽያጭ ሲጠየቁ ብዙ ሚሊዮን ብር ይጠይቃሉ፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን እንዴት ይመለከተዋል?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ለባዮፊውል ልማትና ለነዳጅ ሥርጭት ተገቢው ትኩረት ይሰጥ የሚለውን ሐሳብ ሚኒስቴሩ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለው ተናግረዋል፡፡ የነዳጅ ተቋማት ደረጃ ማስጠበቅ ዳይሬክቶሬትና የባዮፊውል ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ወደ ማዕድን ሚኒስቴር በቅርቡ መዛወሩን ጠቅሰው በእነዚህ መስኮች ትልቅ ሥራ መሥራት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

የጌጣጌጥና የከበሩ ድንጋዮች ንግድ አስመልክቶ ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ የሰጡት ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ቴዎድሮስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለጌጣጌጥ አምራቾች ጥሬ ዕቃ እንዲያቀርብ በአዋጅ የተደነገገ ቢሆንም ጌጣጌጥ አምራቾች ከባንኩ ወርቅ እየገዙ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባንኩ ጥሬ ዕቃውን ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆንም ለመግዛት የቀረበ የለም እያለ ነው፡፡ የታክስ ጉዳይን በተመለከተ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ተነጋግረናል፡፡ ባለሥልጣኑ እየጠየቀ ያለው ጌጣጌጥ አምራቾች ወርቁን ከየት ነው ያመጡት እያለ ነው፡፡ ጌጣጌጥ አምራቾች ወርቁ የመጣበትን ምንጭ ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ባለሥልጣኑ ወደ ሕጋዊ መስመር ግቡ እያለ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ወርቅ ነው ወይ ለኅብረተሰቡ እየቀረበ ያለው? በምርቶች ላይ ዓርማችሁን አድርጉ ተብሏል፡፡ ይህ እየተደረገ ነው? ተጠያቂነት መኖር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የሮያሊቲ ክፍያን በወረዳ መክፈል እንደሚቻል፣ ጥሬ ማዕድናት በሚገዛበት ወቅት ሮያሊቲ የተከፈለበት መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በጌጣጌጥና የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ የግብይት አዋጁን በመገምገም ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አዋጁ የበለጠ አሠሪ እንዲሆን በአዋጁ ላይ ያሉትን ውስንነቶች እያየን ነው፡፡ የሕግ ክፍላችንም በየክልሉ እየተዘዋወረ ይህንኑ እያጠና ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመሬት ሽሚያን በተመለከተ የተነሳው አስተያየት እውነትነት እንዳለው ገልጸው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ ማን በትክክል እየሠራ እንደሆነ፣ ማን ያለሥራ መሬት ታቅፎ እንደተቀመጠ የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጀመርን እንጂ አልጨረስንም፡፡ ከሠራነው ገና ያልሠራነው የሚቀረን ሥራ ይበልጣል፡፡ በዚህ ላይ ከክልሎች ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከክልሎች ጋር በቅንጅት የመሥራት ችግር እንዳለ አምነው ይህን ለመፍታት ሚኒስቴሩ እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የጂኦሎጂካል ሰርቬይ የላቦራቶሪና የቁፋሮ አገልግሎትን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ቶሎሳ፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት ጉዳይ ለሚኒስቴሩ ሕመም መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገብረ ሥላሴ ምላሽ እንዲሰጡ ዕድል ሰጥተዋቸዋል፡፡

አቶ ማስረሻ የጂኦሎጂካል ላቦራቶሪው ከፍተኛ የኬሚካል እጥረት እንደገጠመው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የነበረን ኬሚካል በማለቁና የአቅርቦት ችግር ስለነበረብን ሥራ እስከማቆም ደርሰን ነበር፤›› ያሉት አቶ ማስረሻ፣ ላቦራቶሪው የሰው ኃይል እጥረት እንዳለበት፣ በርካታ መሣሪያዎች ቢኖሩትም ያረጁ በመሆናቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ ያሉት ባለሙያዎቹም በጥቅማ ጥቅም ክፍያ ደስተኛ አለመሆናቸውን ጠቁመው፣ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በቁፋሮ በኩል ያረጁ የቁፋሮ ማሽኖችን ይዞ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ያረጁትን መሣሪያዎች በአዲስ መተካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ያሉትን ችግሮች ቀርፈን አይኤስኦ ሠርተፊኬት ለማግኘት ሩጫ ላይ ነን፤›› ብለዋል አቶ ማስረሻ፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ታደሰ መሰሉ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድን ሚኒስቴር እንቅስቃሴዎችን በቅርበት እንደሚከታተል አስረድተው፣ ሚኒስቴሩ ለወቀሳ በሩን ክፍት ያደረገ ቢሆንም ኩባንያዎች በግልጽ ቅሬታዎቻቸውን ለመናገር ድፍረት ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች